በዚህ Channel ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ ፤ ቀኖና እና ትውፊት የጠበቁ ትምህርቶች ይተላለፉበታል፡፡ ለአስተያየት: ጥቆማና ጥያቄ በዚህ ያግኙን ☞ @Ethiopian_Orthodox_bot Buy ads: https://telega.io/c/Ethiopian_Orthodox
🔔 ዛሬ ምን ይቀደሳል?
የነሐሴ ፫(3) ግጻዌ
መልእክታት
1. ፩(1)ኛ ተሰሎ ፫(3) ፥ ፩(1) እስከ ፍጻሜ
2. ፩(1)ኛ ጴጥ ፫(3) ፥ ፲(10) - ፲፭(15)
3. ግብ ሐዋ ፲፬(14) ፥ ፳(20) እስከ ፍጻሜ
ምስባክ
መዝ ፵፬(44) ፥ ፲፪(12) - ፲፫(13)
"ወይሰግዳ ሎቱ አዋልደ ጢሮስ በአምኃ ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኵሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር ኵሉ ክብራ ለወለተ ንጉሠ ሐሴቦን"
ወንጌል
ሉቃስ ፲፰(18) ፥ ፱(9) - ፲፰(18)
" ⁹ ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥
¹⁰ እንዲህ ሲል፦ ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ።
¹¹ ፈሪሳዊም ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ፦ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤
¹² በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ።
¹³ ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን፦ አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።
¹⁴ እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል።
¹⁵ እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ደግሞ ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም አይተው ገሠጹአቸው።
¹⁶ ኢየሱስ ግን ሕፃናትን ወደ እርሱ ጠርቶ፦ ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው አትከልክሉአቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና።
¹⁷ እውነት እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አለ።
¹⁸ ከአለቆችም አንዱ፦ ቸር መምህር፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው።"
ቅዳሴ
ዘእግዝእትነ(ጐሥዓ)
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
የማይቻለውን ቻልሽ፡፡ ምንም ምን የሚወስነው የሌለውን ወሰንሽ፡፡ ምልዕተ ክብር ሆይ! በክብረ ወሊድ ላይ ክብረ ድንግልናን ደርበሽ ብትገኚ ላንቺ የተሰጠሸ ክብር ፍጹም ነው፡፡ የአካላዊ ቃል ማደሪያ ኹነሻልና፣ ምዕመናንን ሰብስባ የያዘቻቸውና ለሥላሴ ሰጊድን የምታስተምሪላቸው (አንድነት ሦስትነት በጐላ በተረዳ ነገር የታወቀብሽ) ጴጥሮስ በናሕሰ ኢዮጴ ያያት የቤተ ወንጌል ሰፊ መጋጃ አንቺ ነሽ /ሐዋ.፲፡፱-፲፮/፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫም፡- “ሰላም ለኪ መንጦላዕተ ገርዜን - የበፍታ መጋረጃ ሰላምታ ለአንቺ ይገባል” ብሏል /የአባ ጊዮርጊሥ የሰባቱ ጊዜያት የሃይማኖትና የጸሎት መጽሐፍ ትርጓሜ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ፣ ገጽ ፻፷/፡፡
ሙሴ ያየውን ዓምደ እሳት የተሸከምሽ አንቺ ነሽ /ዘጸ.፲፫፡፳፪/፡፡ ይኸውም ዓምደ እሳት ያልኩት ሰው ኹኖ በማኅፀንሽ ያደረው ወልደ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰማይና ምድር ለፈጠረ ለእርሱ ማደሪያ ኾንሽው፡፡ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀንሽ ቻልሽው፡፡ ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ለመወሰን የታመንሽ ነሽ፡፡ ከምድር ወደ ሰማይ ለመውጣት መሰላል ኾንሽ፡፡ በመሰላል የላዩ ወደ ታች ይወርዱበታል፤ የታቹ ወደ ላይ ይወጡበታል፡፡ የላዩ ወደታች እንዲወርዱበት መለኮትም ከአንቺ ትስብእትን ተዋሕዷል፤ የታቹ ወደ ላይ እንዲወጡበትም ትስብእት ከመለኮት ጋራ ለመዋሐዱ ምክንያት ኾነሻል፡፡ ድንግል ሆይ! ክብርሽ ከፀሐይ ብርሃን ይበልጣል፡፡ ቅዱሳን፣ ሰብአ ሰገል /ማቴ.፪፡፪/፣ እነ በለዓም /ዘኅ.፳፬፡፲፯/፣ ሐዋርያት ደስ ብሏቸው ያዩት ኮከብ ካንቺ የተወለደ ምሥራቅ አንቺ ነሽ፡፡ ይኸውም በፃር፣ በጋር፣ በምጥ ትወልድ ዘንድ በሔዋን የፈረደባት ነው፡፡ አንቺ ግን ምልዕተ ክብር ሆይ! ደስ ይበልሽ የሚል ድምፅ ሰማሽ /ሉቃ.፩፡፳፰/፡፡ ሔዋን “በሕማም ለዲ” የሚል ድምፅ ሰምታ /ዘፍ.፫፡፲፮/ ምክንያተ ሞት ቃየልን አስገኘች /ዘፍ.፬፡፩-፰/፡፡ አንቺ ግን “ተፈሥሒ ኦ ምልዕተ ጸጋ” የሚል ደምፅ ሰምተሸ ፍጥረትን ኹሉ የሚገዛ ንጉሥን ወለድሽልን /ሉቃ.፩፡፴፩/፡፡ ሄሬኔዎስ የተባለ ሊቅም ይህንን አንቀጽ በረጐመበት ድርሳኑ እንዲህ ብሏል፡- “እነሆ ጌታ የራሱ ወደኾኑት በግልጥ (በለቢሰ ሥጋ) መጣ፡፡ ትእዛዙን ተላልፎ በዕፅ የሞተውን አዳም በዕፅ (በመስቀል) ላይ ታዝዞና ካሣውን ከፍሎ፣ ወደ ጥንተ ተፈጥሮው ይመልሰው ዘንድ በራሱ ጥበብ ከፍጥረቱ ተወለደ፡፡ ለአንድ ወንድ የታጨችው ድንግል በምክረ ከይሲ ያመጣችውን ያለመታዘዝ ኃይል የእውነት መልአክ ለአንድ ወንድ ለታጨችው ድንግል ባበሠራት ጊዜ ፈራረሰ፡፡ ቀዳማይቱ ሔዋን ከእግዚአብሔር እንድትርቅና ቃሉን እንድትቃወም በክፉ መልአክ እንደተታለለች ኹሉ፣ ዳግማይቱ ሔዋን ቅድስት ድንግል ማርያምም ደጉ መልአክ ይዞት የመጣው መልካሙን ዜና እንድትቀበለውና እግዚአብሔርን በከዊነ ቃሉ እንደምትወልደው አመነች፡፡ ቀዳማይቱ ሔዋን እግዚአብሔርን እንዳትታዘዘው ክፉ መልአክ አታለላት፤ ወደቀችም፡፡ ዳግማይቱ ሔዋን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን እግዚአብሔርን እንድትታዘዝ ቅዱስ መልአክ አሳመናት፤ እርሷም ሔዋንን ረዳቻት፡፡ ነገደ አዳም በአንዲት ድንግል አለመታዘዝ ምክንያት ሞት ተፈረደበት፣ ኾኖም በሌላይቱ ድንግል መታዘዝ ምክንያት ዳነ፡፡ የፍጥረት በኵር የሚኾን አዳም የበደለው በደል የእግዚአብሔር በኵር በሚኾን በወልደ እግዚአብሔር መቀጣት ተፈወሰ፡፡ የእባቡ ተንኰል በርግቡ የዋኅነት ተዋጠ፤ ለሞት ሲዳርገን የነበረው ቁራኝነትም ተሰበረ፡፡”
ሰው ኾኖ ያዳነን መሐሪ ነው፤ ሰው ወዳጅ ነው፡፡ ድንግል ሆይ! በእንተዝ ንዌድስኪ - ስለዚህ ነገር መልአኩ “ቡርክት አንቲ እም አንስት” ብሎ እንዳመሰገነሽ እኛም “ተፈሥሒ ኦ ምልዕተ ጸጋ እግዚአብሔር ምስሌኪ- እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍሽ ነስቶ ካንቺ ጋራ አንድ ባሕርይ ኹኗልና (ተፈሥሒ) ደስ ይበልሽ” ብለን እናመሰግንሻለን፡፡ እንዲህ ካለ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታቸን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
ይኽን ሲጨርስ በያዘችው መስቀለ ብርሃን ባርካው ታርጋለች፡፡ እርሱም እጅ ነሥቶ ይቀራል፡፡
አነሣሥቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን፡፡
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
፮. ድንግል ማርያም በቤተ መቅደስ አሰምታ ትናገር ነበር፡፡ አረጋዊው ዮሴፍ በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደ ፀነሰች ሳያውቅ “ኦ ወለተ እስራኤል መኑ ቀረፀ አክናፈ ድንግልናኪ” ቢላት “እኔስ ምልዕተ ክብር ሆይ! እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍሽ ነፍስ ነሥቶ አንድ አካል ይኾናል ብሎ መልአኩ አክብሮ ከነገረኝ ነገር በቀር ምን ምን የማውቀው እንደ ሌለኝ እግዚአብሔር ያውቃል” ብላ አሰምታ ተናገረች፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም “ዲያተሳሮን” በተባለ የወንጌል ትርጓሜ መጽሐፉ የእመቤታችንና የዮሴፍ ግንኝነት እንዲህ በማለት በጥልቀት ተንትኖታል፡- “የመሲሑ ልደት እንዲህ ነበር፡፡ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች /ማቴ.፩፡፲፰/፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ይህንን ያለ ምክንያት አይናገረውም፡፡ አሕዛብ አማልክቶቻቸው እጅግ አሳፋሪ በኾነ ግንኝነት እኛ ከምናውቀው ተፈጥሮ ውጪ ልጅ ይወልዳሉ ብለው ስለሚያስቡ እንጂ፡፡ በመኾኑም እነዚህ አሕዛብ እንደሚያስቡት እመቤታችን ፀንሳ ተገኘች ተብሎ እንዳይታሰብ ወንጌላዊው “ሳይገናኙ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች” አለ፡፡ የተወለደው በወንድ ዘር አይደለም፡፡ ማኅተመ ድንግናዋን ሳይለውጥ ገባ፤ አከበራት፤ ነፍስና ሥጋም ከእርሷ ነሥቶ ተዋሐደ፡፡
አስቀድማ ለወንድ መታጨቷ፣ ባል (ጠባቂ) እንዳላት መደረጓ፣ ቀጥሎም መፅነሷ ልጇ ወዳጇ በዳዊት በትረ ሥልጣን ስለሚገባና የዳዊት ሥልጣንን የሚይዝ ደግሞም በእናቱ ሳይኾን በአባቱ ስም ስለሚጠራ ነው /ሉቃ.፩፡፴፪/፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ክፉዎች የፀነሰችው በሴሰኝነት ነው ብለው እንዳያስቡ ነው፡፡ እጅግ ጻድቅ ለኾነው ለዮሴፍ የመታጨቷ ምክንያት ይህ ነበር፡፡ ዮሴፍ እመቤታችንን ፀንሳ ባያት ጊዜ እስክትወልድ ድረስ ተከባከባት፡፡ ከእርሷ ጋር በቤቱ ኖረ እንጂ አላባረራትም፡፡ ከማንምና ከምንም አስቀድሞ ከእርሷ የተፀነሰው በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንጂ በዘርዐ ብእሲ እንዳልኾነ ምስክር ኾነ፡፡
እመቤታችንም ያለ ታራሽ ልጇን ወለደችው፡፡ ቀዳማይቱ ሔዋን አዳም ከማንም ጋር ሳይገናኝ እንደወለዳት አሁንም ዮሴፍና እመቤታችን በግብር ሳይተዋወቁ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ወለደች፡፡ ሔዋን ነፍሰ ገዳዩን (ቃየልን) ወለደች፤ እመቤታችን ግን ወሀቤ ሕይወትን ወለደች፡፡ ቀዳማዪቷ ሔዋን የወንድሙን ደም የሚያፈስ ልጅን ወለደች፤ ዳግማዪቱ ሔዋን ግን ስለ ወንድሞቹ ደሙን የሚያፈስ ልጅን ወለደች፡፡ የቀዳማይቱ ሔዋን ልጅ (ቃየል) ምድር ተረግማ ኃይልዋን አልሰጥ ስላለችው ኰብላይና ተቅበዥባዥ ኾነ /ዘፍ.፬፡፩-፲፬/፤ የዳግማይቱ ሔዋን ልጅ ግን ያንን ርጋማን አስወገደው በመስቀል ላይም ጠርቆ አስወገደው /ቈላ.፪፡፲፬/፡፡ የእመቤታችን ፅንስ አዳምን ያለ ወንድ ዘር ከድንግል ምድር እንደተገኘ ዳግማዊ አዳምም ያለ ዘርዐ ብእሲ በድንግሊቱ ማኅፀን እንደተገኘ ያስተምረናል፡፡ ቀዳማዊ አዳም በበደለ ጊዜ ወደ እናቱ ማኅፀን (ወደ ምድር) ተመለሰ፤ ዳግመኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ያልተመለሰው ዳግማዊ አዳም ግን ቀዳማዊውን እንደገና ከእናቱ ማኅፀን እንዲወለድ አደረገው፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተራራማው ሀገር ወደ ቤቷ በሄደች በተመለሰች ጊዜ የፀነሰችው በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደኾነ ታስረዳው ነበር፤ ነገር ግን ከኅሊናት በላይ ስለኾነበት ነገሩ ረቀቀበት፡፡ ፊቷን ሲመለከታት ምንም ዓይነት የውሸት ምልክት አይታይባትም፤ ግን ደግሞ ሆዷ ገፍቷል፡፡ በመኾኑም ደግ ነውና ሊገልጥባት አልወደደም፡፡ ከዚሁ ጐን ለጐን ግን ከሌላ ወንድ ጋር ተገናኝታለች ብሎ ስላሰበ ወደ ቤቱ ሊወስዳት አልወደደም፡፡ በእነዚህ ኹለት ሐሳቦች እየተማታ ወደቤቱ ሊወስዳት እንደማይገባ ግን ደግሞ ነገሩንም ሊገልጥባት እንደማይገባ ወሰነ፡፡ ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታየው፡፡ በጣም በሚያደንቅ መንገድ መልአኩ “ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት - የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ!” አለው፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር ለቅድመ አያቱ ለዳዊት “እስመ እምፍሬ ከርሥከ አነብር ዲበ መንበርከ- ከባሕርይህ የተከፈለ ልጅህ ክርስቶስን በዙፋንህ አስቀምጣለሁ” ብሎ የማለለትን ቃል እንዲያስተውስ ነው /መዝ.፻፴፩፡፲፩/፡፡ መልአኩ ቀጠለ፤ እንዲህም አለው “ኢትፍራህ ነሢኦታ ለማርያም ፍኅርትከ እስመ ዘይትወለድ እምኔሃ እመንፈስ ቅዱስ ውእቱ - የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ! ከካህናት እጅ እንደተቀበልህ ከእደ መንፈስ ቅዱስ መቀበልን አትፍራ፤ ከእርሷ የሚወለደው በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡ ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንድምትወልድ ከረቀቀብህ እነሆ “ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ” የሚለውን የነቢዩን ቃል አስታውስ /ኢሳ.፯፡፲፬/፡፡ ዳግመኛም ነቢዩ ዳንኤል “ተበትከ ዕብን ዓቢይ እምደብር ዘእንበለ እድ - ታላቅ ደንጊያ እጅ ሳይነካው ከተራራ ወረደ” ብሎ የተናገረውን ልብ በል /ዳን.፪፡፴፭/፡፡ ይህ የነቢዩ ዳንኤል ቃል ኢሳይያስ በአንድ ቦታ “ርእይዋ ለኰኩሕ ጽንዕት እንተ ወቀርክሙ ወአዘቅተ ዕምቅተ እንተ ከረይክሙ - ያለዘባችኋትን ጽኑ ዐለት እይዋት የቈፈራችሁትንም ጥልቅ ጕድጓድ አስተውሉ” ብሎ እንደተናገረው ያለ አይደለም ኢሳ.፶፩፡፩/፡፡ ምክንያቱም ኢሳይያስ የወንድና የሴትን ነገር አንሥቶ የተናገረ ሲኾን ነቢዩ ዳንኤል ግን “ዘእንበለ እድ - ያለ እጅ” ነው ያለው፡፡ ይኸውም ቀዳማዊ አዳም ለሔዋን አባቷም እናቷም እንደኾነ ኹሉ እመቤታችን ለጌታችን (በተዋሐደው ሥጋ) እናቱም አባቱም ነች፡፡
ዮሴፍ ጻድቅ ሰው ስለነበረ ነገሩን ሊገልጥባት አልወደደም፡፡ ደግነቱም (ጽድቁም) እንደ ሕጉ የኾነ ደግነት አይደለም፡፡ ሕጉ እንዲህ ያለ ነገርን ያደረገ ወንድ ወይም ሴት እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ተወግሮ እንዲገደል ያዝዛልና /ዘዳ.፲፯፡፭፣፯ ፤ ዘዳ.፳፪፡፳፫-፳፬/፡፡ ዮሴፍ ግን በስዉር ሊተዋት (ሊለያት) አሰበ እንጂ ሊገልጥባት አላሰበም፡፡ ዮሴፍ ይህን የሚደርገው ነገሩ ረቅቆበት፣ ከሚያውቀው የተፈጥሮ ሂደትም ውጪ ስለኾነበት ነው፡፡ በመቀጠል የኾነው ኹሉ እግዚአብሔር እንዳደረገው ተገነዘበ፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለ ነገር አይቶም ሰምቶም ስለማያውቅ ግራ ተጋባ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እመቤታችንን ላለማመን ምንም የማይቻል ነበር፡፡ ምክንያም በጣም ብዙ አስረጂ ነገሮችን አስረድታዋለችና፡፡ የዘካርያስ ዲዳ መኾን፣ የኤልሳቤጥ መፀነስ፣ የመልአኩ ብሥራት፣ የብላቴናው ዮሐንስ በሐሴት መሞላትና መዝለል፣ የቀደሙ አበው ትንቢት እና ሌሎች ዮሴፍን ለማሳመን ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይነግሩት ነበር፡፡ በመኾኑም ነገሩን ሳይገልጥባት በስዉር ሊተዋት (ሊለያት) ወሰነ፡፡ እመቤታችን የፀነሰችው በግብረ መንፈስ ቅዱስ መኾኑን ቢያውቅ ኖሮ በስውር ሊተዋት ባላሰበ ነበር፡፡
@Ethiopian_Orthodox
፩. ከሴቶች ተለይተሸ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ሌለብሽ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እያማለድሽ የምታሰጭ ነሽ /ሉቃ.፩፡፳፰/፡፡ ቤዴ የተባለ ተርጓሜ መጻሕፍት ይህን አንቀጽ ሲተረጉመው፡- “የመጀመርያው የሰው ልጆች ስሕተት ከዲያብሎስ በእባብ አማካኝነት ወደ ሴት ተላከ፡፡ ሴቲቱም በትዕቢት መንፈስ ወደቀች፡፡ ዲያብሎስ በእባብ ገላ ተሰውሮ መጣና የመጀመርያዎቹ ወላጆቻችንን አታለላቸው፡፡ ኢመዋቲው ጸጋቸውን ገፈፈው፡፡ ስለኾነም ሞት በሴት ምክንያት ገብቷልና መድኃኒትም በሴት ምክንያት ይገባ ዘንድ ይገባው ነበር፡፡ ቀዳማይቱ ሔዋን ዲያብሎስ በእባብ ገላ ተሰውሮ አታለላት፡፡ ለሰውም ኹሉ የሞትን ጣዕም አቀመሰችው፡፡ ሌላይቱ ሔዋን ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ በተላከ መልአክ የዓለም መድኃኒት የኾነው ክርስቶስን አስገኘች” በማለት እመቤታችን ከሴቶች ኹሉ የመለየቷን ምሥጢር በጥልቀት አስተምሯል፡፡
የማኅፀንሽም ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍሰ የሌለበት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ የሚላን ሊቀ ጳጳስ የነበረውና አምብሮስ የተባለው ሊቅ ይህን አንቀጽ ሲተረጕም፡- “እመቤታችን አመነች እንጂ አልተጠራጠረችም፤ በመኾኑም የእምነቷን ፍሬ አገኘች፡፡ “ወብጽዕት አንቲ እንተ ተአምኒ ከመ ይከውን ቃለ ዘነገሩኪ እም ኀበ እግዚአብሔር - ከእግዚአብሔር አግኝተው የነገሩሽን ነገር እንዲደረግ የምታምኚ አንቺ ንዕድ ክብርት ነሽ” እንዲል /ሉቃ.፩፡፵፭/፡፡ እናንተ ከእግዚአብሔር አግኝተው የነገርዋችሁን ነገር እንዲደረግ የምታምኑም ንዑዳን ክቡራን ናችሁ፡፡ የሚያምኑ ነፍሳት አካላዊ ቃልን ይፀንሱታል፤ በግብራቸውም ይወልዱታል (ይገልጡታል)፡፡ እንግዲያውስ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርጉት ዘንድ እመቤታችንን ምሰልዋት፡፡ በፈጣሪያችሁ በመድኃኒታችሁ አምናችሁ ደስ ይላችሁ ዘንድ የእመቤታችንን ልቡና ገንዘብ አድርጉ /ሉቃ.፩፡፵፮-፵፯/፡፡ ምንም እንኳን ጌታችንን በሰውነቱ የምትወልደው (የወለደችው) እመቤታችን ብቻ ብትኾንም በእምነት በኵል ግን የኹሉም አማንያን ፍሬ ነውና” በማለት ይመክረናል፡፡
አምላክን የወለድሽ ድንግል ማርያም ሆይ! የጽድቅ ፀሐይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካንቺ ተወልዶም /ሚል.፬፡፪/ በክንፈ ረድኤቱ (በሥልጣኑ) አቀረበን፡፡ በሐዲስ ተፈጥሮ፣ በጥንተ ተፈጥሮ ፈጥሮናልና፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንዲህ ይላል፡- “በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከግብርናተ ዲያብሎስ ነጻ ወጣን፡፡ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ውሉደ እግዚአብሔር ተባልን፡፡ ከምንም በላይ ግን ከኀጢአት ቀንበር ተላቅቀን በሐዲስ ተፈጥሮ ተፈጠርን፡፡ ሥርየተ ኀጢአትን ሰጠን፡፡ ከርኩሰት ኹሉ አነጻን፡፡ ከጸጋው የተነሣ ደቂቀ አዳም የነበርን መላእክት አደረገን፡፡ መላእክቱም ለእኛ በተደረገው ነገር ሐሴት አደረጉ፡፡ ወዮ! ገና ሰዎች ሳለን መላእክት መኾናችን እንደምን ይረቃል እንደምን ይደንቃል? ይህ ኹሉ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው” /Fr. Tadros Malaty, On the Book of Isaiah 40:31/፡፡ በሐዲስ ተፈጥሮ፣ በጥንተ ተፈጥሮ ከፈጠረን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፪. አምላክን የወልድሽ እመቤታችን ሆይ! ፀሐይ ዘኢየዐርብ (የማይጠልቅ ፀሐይ) የተባለው የብርሃን ክርስቶስ እናቱ ነሽና በአፍኣ በውሰጥ በሥጋ በነፍስ አንቺን ብቻሽን እናከብርሻለን፤ እናገንሻለንም፡፡ ልዑላን ከሚባሉ መላእክት አንቺ ትበልጫለሽ፤ ትሑታን ከሚባሉ ከደቂቀ አዳምም አንቺ ትበልጫለሽ፡፡ ከኀሊናት ኹሉ በላይ ነሽ (ኅሊና የአንቺን ክብር ተናግሮ መጨረስ አይቻለውም)፡፡ ክብርሽን ገናንነትሽን መናገር የሚቻለው ማነው? አንቺንስ የሚመስል ማነው? ሊቁ አባ ሕርያቆስም፡- “ይህንም ባሰብኩ ጊዜ ኅሊናዬ የልጅሽን የባሕሩ ጥልቅነት ይዋኝ ዘንድ ይወዳል፤ የወዳጅሽ የመሠወሪያው ማዕበልም ያማታዋል” ይላል /ቅዳ.ማር.ቁ.፹፬/፡፡ መላእክት ያከብሩሻል፤ ያገኑሻልም፡፡ ሱራፌልም ያመሰግኑሻል፡፡ በኪሩቤል በሱራፌል አድሮ የሚኖረው እርሱ ሰው ኹኖ በማኅፀንሽ አድሯልና፡፡ ክብር የክብር ክብር ያለው እርሱ፤ ሰውን የሚወድ ሰውም የሚወደው እርሱ የእኛን ሞት ነሥቶ የእርሱን ሕይወት ለኛ ሰጥቶ ካባቱ ጋራ አስታረቀን፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በ “በእንተ ልደት” ድርሳኑ ላይ፡- “ስለዚህ ሥጋዬን ተዋሐደ! ወንጌልን ሲያስተምር እሰማው ዘንድ ሥጋዬን በተዋሕዶ ገንዘቡ አደረገው! ሥጋዬን ወስዶም መንፈሱን ሰጠኝ፡፡ ሰጠሁ፤ ተቀበልኩም፡፡ የእኔን ወስዶ የራሱን ስለ ሰጠኝም ሕይወትን ገንዘብ አደረግሁ፡፡ እኔን ለመቀደስ ሥጋዬን ተዋሐደ፤ የሚያድነኝ መንፈስ ቅዱስንም ሰጠኝ” ብሏል፡፡ ክብር የክብር ክብር ካለው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋዉን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፫. ድንግል ሆይ! የደናግል ኹሉ መመኪያቸው አንቺ ነሽ፡፡ ከእናንተ መካከል “መመኪያነቷ እንዴት ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡-
፩ኛ) ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ሲል ይመልስልናል፡- “ወበከመ አውፅአ ብእሲ ብእሲተ ዘእንበለ ብእሲት ከማሁ አውፅአት ብእሲት ብእሴ ዘእንበለ ብእሲ ወሀሎ ዕዳ ላዕለ ትዝምደ አንስት፤ ወበእንተዝ ኮነት ፈዳዪተ ዕዳሃ ለሔዋን - ለወንዶች የሚከፈል ዕዳ በሴቶች ላይ ነበረ፤ ያለ እናት ሔዋን ተገኝታ ነበርና፡፡ ስለዚህም የሔዋንን ብድራት ለአዳም ትከፍለው ዘንድ ድንግል ያለ ዘርዐ ብእሲ (ያለ ወንድ ዘር) ክርስቶስን ወለደችው፡፡ አዳም ያለ እናት ሔዋንን ስላስገኘ እንዳይመካ ድንግል ያለ አባት ክርስቶስን ወለደችው፡፡ ድንቅ በሚኾን አንድነት ይህ አንድ የፍጥረት እኩልነት ይታወቅ ዘንድ” /ሃይ.አበ.፷፮፡፳፱/፤
፪ኛ) ቀድሞ ወንዶች ሴቶችን በእናንተ ምክንያት ከገነት ወጣን እያሉ ርስት አያካፍሏቸውም ነበር፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ብእሲ ወብእሲት አሐደ እሙንቱ በክርስቶስ - ወንድም ሴትም የለም፤ ኹላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና” ብሎ እስኪያስተምር ድረስ /ገላ.፫፡፳፰/ በሔዋን ምክንያት ከገነት ብትወጡ በእመቤታችን ምክንያት ገነት መንግሥተ ሰማያት ገብታችሁ የለምን? ብለው የሚመኩ ኹነዋልና፤
፫ኛ) ደግሞ ለደናግላን አስበ ድንግልናቸውን (የድንግልናቸውን ዋጋ) ስለምታሰጣቸው ሊቁ “ምክሆን ለደናግል” ብሏታል፡፡
🔔 ዛሬ ምን ይቀደሳል?
የነሐሴ ፪(2) ግጻዌ
መልእክታት
1. ፩(1)ኛ ጢሞ ፪(2) ፥ ፰(8) እስከ ፍጻሜ
2. ፩(1)ኛ ጴጥ ፫(3) ፥ ፩(1) - ፯(7)
3. ግብ ሐዋ ፲፮(16) ፥ ፲፫(13) - ፲፱(19)
ምስባክ
መዝ ፵፬(44) ፥ ፲፬(14) - ፲፭(15)
"ወይወስዱ ለንጉሥ ደናግለ ድኅሬሃ። ወቢጻሂ ይወስዱ ለከ። ወይወስድዎን በትፍሥሕት ወበሐሴት።"
ወንጌል
ዮሐንስ ፰(8) ፥ ፩(1) - ፲፪(12)
"¹ ኢየሱስ ግን ወደ ደብረ ዘይት ሄደ።
² ማለዳም ደግሞ ወደ መቅደስ ደረሰ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። ተቀምጦም ያስተምራቸው ነበር።
³ ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ አመጡ በመካከልም እርሱዋን አቁመው፦
⁴ መምህር ሆይ፥ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች።
⁵ ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን፤ አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ? አሉት።
⁶ የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት ይህን አሉ። ኢየሱስ ግን ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ፤
⁷ መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ግን ቀና ብሎ፦ ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት አላቸው።
⁸ ደግሞም ጐንበስ ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ጻፈ።
⁹ እነርሱም ይህን ሲሰሙ ሕሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምረው እስከ ኋለኞች አንድ አንድ እያሉ ወጡ፤ ኢየሱስም ብቻውን ቀረ ሴቲቱም በመካከል ቆማ ነበረች።
¹⁰ ኢየሱስም ቀና ብሎ ከሴቲቱ በቀር ማንንም ባላየ ጊዜ፦ አንቺ ሴት፥ እነዚያ ከሳሾችሽ ወዴት አሉ? የፈረደብሽ የለምን? አላት።
¹¹ እርስዋም፦ ጌታ ሆይ፥ አንድ ስንኳ አለች። ኢየሱስም፦ እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ አላት።
¹² ደግሞም ኢየሱስ፦ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው።"
ቅዳሴ
ዘእግዝእትነ።(ጐሥዓ)
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
፭. ተናግሮ የማያስቀር፣ ምሎ የማይከዳ እግዚአብሔር፡- “ከባሕርይህ የተከፈለ ልጅህ (ክርስቶስን) በዙፋንህ አስቀምጥልሃለሁ” ብሎ ለዳዊት በእውነት ማለለት /መዝ.፻፴፩፡፲፩/፡፡ ዳዊትም ክርስቶስ በሥጋ ከእርሱ እንዲወለድ ባመነ ጊዜ የአካላዊ ቃል ማደርያውን መርምሮ ያውቅ ዘንድ ወደደ፡፡ ቀኖናም ገባ፡፡ ከዚህም በኋላ “ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ ወረከብናሁ ውስተ ዖመ ገዳም - በኤፍራታ ተወልዶ፤ በጎል ተጥሎ፤ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግዕዘ ሕፃናት ሲያቅስ ሰማነው” አለ /መዝ.፻፴፩፡፮/፡፡ ይህቺውም እኛን ስለማዳን ይወለድባት ዘንድ የመረጣት ቤተ ልሔም፣ ቤተ ኅብስት የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ ከሰማይ የወረደው ኅብስት እርሱ ነውና /ዮሐ.፮፡፶፩/፡፡
ከነቢያት አንዱ የሚኾን ሚክያስም ዳግመኛ እንዲህ አላት፡- “አንቺም የኤፍራታ ዕፃ የምትኾኝ ቤተ ኅብስት ቤተ ልሔም እመቤታችን ሆይ! በይሁዳ ከነገሡ ነገሥታት ብትበልጭ እንጂ አታንሺም፡፡ እሥራኤል ዘነፍስን የሚጠብቅ ንጉሥ ባንቺ ይወለዳልና እንዲህ እንደኾንሽ አትቀሪም፡፡ ንጉሥ ይወለድብሻል፤ ቅዳሴ መላእክት ይሰማብሻል፤ የብርሃን ድንኳን ይተከልብሻል፤ መቶው ነገደ መላእክት ደጅ ይጠኑብሻል፡፡ አሕዛብ ይገብሩብሻል” ብሏታል /ሚክ.፭፡፪/፡፡ ጀሮም የተባለ ቅዱስ አባት ይህን አንቀጽ ሲተረጕም፡- “ከሰማይ የወረደ ኅብስት /ዮሐ.፮፡፶፩/ የተወለደብሽ ቤተ ኅብስት ሆይ! ሰላምታ ይገባሻል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደብሽ ምድረ ፍሬ፣ ምድረ ምውላድ (ኤፍራታ) ሆይ! ሰላምታ ይገባሻል፡፡ በዘመነ ብሉይ ሚክያስ ነቢይ ስለ አንቺ ሲናገር እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበርና፡- ‘ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሕቲ እም ነገሥተ ይሁዳ - አንቺም የኤፍራታ ዕፃ የምትኾኝ ቤተ ልሔም ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሺም /ማቴ.፪፡፮/፡፡ ኢይወጽእ ምስፍና ወምልክና እምአባሉ ለይሁዳ - በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም እንዲል /ዘፍ.፵፱፡፲/ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ከዲያብሎስ አስቀድሞ ቀዳማዊ የኾነ እሥራኤል ዘነፍስን የሚጠብቅ ንጉሥ ከአንቺ ይወጣል (ይወለዳልና)” ብሏል /St. Jerome, Letter 108:10/፡፡
ወዮ! ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ከአብ ከባሕርይ አባቱ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ ጋራ ክብር ይግባውና በአንድ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው የክርስቶስን ነገር የተናገሩ ሚክያስና ዳዊት የተናገሩት ነገር ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? አንድም ሚክያስና ዳዊት ለተናገሩት ነገር አንክሮ ይገባል፡፡ ከአብ ከባሕርይ አባቱ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ ጋር ክብር ከሚገባው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፮. ለእሥራኤል የነገሠ ዳዊት ኢሎፍላውያን በጠላትነት በተነሡበት ጊዜ ከቤተ ልሔም ምንጭ ውሃ ይጠጣ ዘንድ ወደደ፡፡ ዳዊት ታመመ፤ ቢታመም ዘመዶቹ ቀሳ አወጡት፡፡ ኢሎፍላውያን ይህን ሰምተው ቤተ ልሔምን አልፈው ሰፈሩ፡፡ ዳዊትም “ከቤተ ልሔም ምንጭ ውሃ ማን ባመጣልኝ?” አለ፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ስለምን ከቤተ ልሔም የተቀዳ ውሀ ይጠጣ ዘንድ ወደደ?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው ታምሞ ስለነበር የቤተ ልሔም ውሀ ደግሞ ማየ ፈውስ ናትና /፪ኛ ነገ.፳፫፡፲፭-፲፯፣ አንድምታውን ይመልከቱ/፡፡
ስለኾነም የጭፍራ አለቆች አዲኖን ኢያቡስቴ ኤልያናም አፋ አፋቸውን ታጥቀው፣ ዘገራቸውን ነጥቀው፣ ራዋታቸውን ጭነው “የማን ጌታ በውሃ ጥም ይሞታል?” ብለው ፈጥነው ተነሡ፡፡ በኢሎፍላውያን ከተማ ተዋጉለት፡፡ ይጠጣ ዘንድ የወደደውንም ውሀ አመጡለት፡፡ ብጹዕ ዳዊት ግን ስለ ርሱ ሰውታቸውን ለሞት አሳልፈው እንደ ሰጡ በየ ጊዜ የራዋቱን ውሀ አፈሰሰው፡፡ በማለፊያው ቀድተው የሰጡትን አልጠጣም፡፡ “የናንተን ደም መጠጣት ነው” ብሎ አፍሶታል፡፡ አንድም ውሀውን መሥዋዕት አድርጐ ለእግዚአብሔር አፈሰሰው፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ዳዊት ንጉሥ ሲኾን መሥዋዕት የሚኾን ላም በግ አጥቶ ነውን?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ በፍጹም! እግዚአብሔር የወደዱትን ቢተዉለት ስለሚወድ ነው እንጂ /መዝ.፶፬፡፮፣ ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ ፻፵፭/፡፡
ዳዊት የወደደውን ውሀ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ስላፈሰሰውም ጽድቅ ኾኖ ተነገረለት፡፡ አዲኖን፣ ኢያቡስቴ፣ ኤልያና ስለ ዳዊት ብለው ጣዕመ ዓለምን እንደናቁ፤ ዳዊትም ስለነርሱ አንድም ስለ እግዚአብሔር ብሎ ጣዕመ ማይን እንደናቀ ሰማዕታት ጣዕመ ዓለምን ናቁ፡፡ አዲኖን፣ ኢያቡስቴ፣ ኤልያና ዳዊትን ብለው ደማቸውን እናፍስ እንዳሉ፤ ዳዊትም ውሀውን እንዳፈሰሰ፤ ሰማዕታት ስለ እግዚአብሔር ብለው ደማቸውን አፈሰሱ፡፡ አዲኖን፣ ኢያቡስቴ፣ ኤልያና ስለ ዳዊት ብለው መራራ ሞትን እንታገሥ እንዳሉ፡ ዳዊትም ጽምዓ ማይን ልታገሥ እንዳለ ሰማዕታት መራራ ሞትን ታገሡ፡፡ ቸር አባት ሆይ! እኛስ እንደ ሰማዕታት ከዓላውያን ነገሥታት፣ ከዓላውያን መኳንንት ገብተን መከራውን ታግሠን ተቀብለን፤ እንደ ምዕመናንም ከፍትወታት ከእኩያት ኃጣውእ ተዋግተን ድል ነሥተን መዳን አይቻለንምና እንደ ቸርነትህ ብዛት ይቅር በለን፡፡ ቸርና ይቅር ባይ ከሚባል ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣ ለምኚልን፡፡
፯. ከሦስቱ አካል አንዱ አካል በእግረ አጋንንት መረገጣችንን መጠቅጠቃችንን አየና ባሕርዩን ዝቅ አድርጎ
ሰው ኹኖ በድንግል ማኅፀን አደረ /ኢሳ.፶፱፡፮/፡፡ ባሕየ መላእክትን ባሕይ አላደረገም፤ ባሕርየ ሰብእን ባሕርይ አድርጎ በድንግል ማኅፀን አደረ እንጂ /ዕብ.፪፡፲፮/፡፡ ከብቻዋ ከኃጢአት በቀርም እንደኛ ሰው ኾነ /ዕብ.፬፡፲፬/፡፡ ሚክያስና ዳዊት በቤተ ልሔም ይወለዳል ብለው እንደ ተናገሩ በቤተ ልሔም ተወለደ፡፡ “ይሙት ቤዛነ በትስብእቱ ወየሀበነ መድኃኒተ ዘከመ መለኮቱ” እንዲልም እንደ አምላክነቱ አዳነን እንደ ሰውነቱም ቤዛ ኾነን /ኤፌ.፩፡፯/፡፡ ዳግመኛም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ኾናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ኾናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል” /ኤፌ.፪፡፲፩-፲፫/ እንዲል ወገኖቹ ያልነበርን እኛን ወገኖቹ አደረገን፡፡ ወገኖቹ ካደረገን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣ ለምኚልን፡፡
ይኸን ሲጨርስ በያዘችው መስቀለ ብርሃን ባርካው ወደ ሰማይ ታርጋለች፡፡ እርሱም ተባርኮ እጅ ነሥቶ ይቀራል፡፡
አነሣሥቶ ላስጀመረን አስጀምሮም ላስጨረሰን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን!!!
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
፩. ነደ እሳት ሰፍሮባት፣ በነደ እሳት ተከባ፣ ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ሙሴ በደብረ ሲና ያያት ዕፅ ድንግል ማርያምን ትመስላለች /ዘጸ.፫፡፩-፫/፡፡ አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኹኗልና፤ ባሕርየ (እሳተ) መለኮቱም አልለወጣትምና (አላቃጠላትምና) ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ ዳግመኛም እርሱን ከወለደችው በኋላ ማኀተመ ድንግልናዋ አልተለወጠምና ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ እርሱም ምንም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ፍጹም ሰው ቢኾንም ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና እሳቱን ይመስላል፡፡ ሰውም ቢኾን ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና ሰው ኾኖ ያዳነን የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ሰው ኾኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋዉን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፪. ይቅርታሽ (ምልጃሽ) ለኹላችን ይኾን ዘንድ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ! ኹላችን እናከብርሻለን፤ እናገንሻለን፡፡ ሔዋን ባደረገችው ዐመፅ በባሕርያችን ጸንቶ የነበረ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ በእርሷ ምክንያት የጠፋልን አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም የኹላችን መመኪያ ናት፡፡ “ሔዋን ምን አደረገች?” ትለኝ እንደኾነም ዕፀ በለስን በልታለች እልሃለሁ፡፡ “ወአዘዞሙ ለኪሩቤል ወሱራፌል ዘውስተ እደዊሆሙ ሰይፈ እሳት እንተ ትትመያየጥ ከመ ይዕቀቡ ፍኖተ ዕፀ ሕይወት - ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ” እንዲል /ዘፍ.፫፡፳፬/ በሔዋን ምክንያት የገነት ደጅ ተዘጋ፡፡ “ወአግኃሦ ለሱራፊ ዘየዐቅብ ፍና ዕፀ ሕይወት፤ ወአእተተ እምእዴሁ ኵናተ እሳት - ” እንዲልም በድንግል ማርያም ምክንያት ዳግመኛ ተከፈተልን፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግም፡- “አዳምን እንዲሞት ያደረገች ያቺ ቀን ተለወጠች፡፡ እርሱም ከሞት የሚድንባት ሌላ ቀን መጣች፡፡ እባቧ ሳትኾን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ይናገር ዘንድ ተነሣ፡፡ ሔዋን ሳትኾን ድንግል ማርያምም ቃሉን ትቀበል ዘንድ ተዘጋጀች፡፡ በተንኰል የሚያስተው ሳይኾን ሕይወትን የሚያውጀው ቃል ወጣ፡፡ በሞት ዛፍ መካከል የሞት ዕዳዋን በጻፈችው ሔዋን ፈንታ ልጇ (ማርያም) የአባቷን ዕዳ ኹሉ ከፈለች፡፡ ሔዋንና እባቡ በቅድስት ድንግል ማርያምና በቅዱስ ገብርኤል ተተኩ፡፡ ያ ከመጀመርያው የተበላሸው ነገር አሁን ተስተካከለ፡፡ የሔዋን ጀሮና ቀልብ አታላዩ በሚናገርበት ጊዜ እንደምን እንዳዘነበለ አስተውሉ፤ ያ በገነት ሲመለከታቸው የነበረው መልአክ አሁን በድንግል ማርያም ጀሮ የድኅነትን ተስፋ ሲያሰርጽና የእባቡን ከፉና መርዛማ ቃል ሲያጠፋ ደግሞ አስተውሉ፡፡ ሔዋን ያፈረሰችው ሕንፃ ገብርኤል ገነባው፡፡ በዔደን ገነት ውስጥ ኹና ሔዋን ያፈረሰችውን መሠረት ዳግሚት ሔዋን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ኹና ገነባችው፡፡ ከኹለት መልእክተኞች መልእክት የተቀበሉ ኹለት ደናግላን ኹለት ትውልድን ቀጠሉ፡፡ አንዱም የአንዱ ተቃራኒ ኾነ፡፡ በእባብ ምክንያት ሰይጣን ምሥጢርን ለሔዋን ላከ፡፡ በሌላ ቅዱስ መልአክ አማካኝነት ደግሞ ጌታ የምሥራቹን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ላከ፡፡ እባብ ለሔዋን የሐሰትን ቃል ለሔዋን ስትናገር ቅዱስ ገብርኤል ግን የእውነትን ቃል ለቅድስት ድንግል ማርያም ተናገረ፡፡ እውነትን በሚናገር አንደበቱ የቀደመውን የእባብ ቃል አደሰው፡፡ እውነትን ተናገረና ሐሰቱን አስወገደው፡፡ አስቀድሞ ሐሰትን ከራሱ አንቅቶ ሰይጣን ሔዋንን በዔደን ገነት አታለላት፡፡ ይህንንም ታላቅ ስሕተት በጀሮዋ አልፎ እንዲሰማት ፈቀደች፡፡ አሁን ግን በመጀመርያዋ ድንግል ፈንታ ሌላ ድንግል ተመረጠች፡፡ በዚህች ድንግል ጀሮም ከአርያም የተላከ የእውነት ቃል ገባ፡፡ ሞት በገባበት በዚያ በር (ጀሮ) ሕይወት ገባ፡፡ ክፉው (ዲያብሎስ) ያጠበቀው ጽኑ የሞት ማሰርያም ተፈታ፡፡ ኀጢአትና ሞት ሠልጥነውበት በነበረ ቦታ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በዝቶ ታየ፡፡ … እባብ የስሕተትን ዜማ ለሔዋን ዘመረላት፤ ሐሰትንም ረጨባት፡፡ በተፈጥሮዋ ገና ድንግል በምትኾን በሔዋን ላይ ክፉ ምክርና ስሕተት አፈሰሰባት፡፡ በመርዝ የተለወሰና ደምን የተጠማ ክፉ ምክር በአዳም ቤት ውስጥ አስገባ፡፡ ኃይለ ልዑል የላከው መልአክ ግን እነዚህን የክፋት ሰይፎች ለመቆራረጥ ክንፉን እያማታ እየበረረ መጣ፡፡ ለሰው ኹሉ የሚኾን የድኅነት ሰነድ ይዞ መጥቶም ለድንግሊቱ (ለማርያም) አበሠራት፡፡ ሰገደላት፡፡ ሕይወትን በውስጧ አሰረጸ፡፡ ሰላም ዐወጀ፡፡ በፍቅር ቀረባት፡፡ የቀድሞውን የሞት ዳባ በጣጠሰው፡፡ እባብ የገነባውን የማታለል ግንብ ዳግም ላይገነባ በወልደ እግዚአብሔር እንደሚናድ ነገራት፡፡ በእባብ የታጠረው የሞት ቅጽር በወልድ መውረድ እንደሚሰባበር ቀጠሮው እንደደረሰ ነግሮ የምሥራች አላት” በማለት ከማር የጣፈጠ ትምህርቱን እያነጻጸረ አስተምሯል፡፡
ከዕፀ ሕይወትም እንበላ ዘንድ አደለን፡፡ ይኸውም እኛን ስለ መውደድ ሰው ኾኖ ያዳነን የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡
ወዮ! ሰውን የሚወድ ሰውም የሚወደው እግዚአብሔር፣ ማኅደርም ኀዳሪም ያይደለ አካላዊ ቃል፣ ሳይለወጥ ቅድመ ዓለም የነበረ እግዚአብሔር ወልድ፣ ከአብ አንድነት ሳይለይ መጥቶ ንዕድ ክብርት ከምትኾን ከእመቤታችን ሰው ኾኗልና፤ እርሱንም ከወለደችው በኋላ እንደ ቀድሞ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ ኑራለችና፤ ስለዚህም ነገር አምላክን የወለደች እንደኾነች በጎላ በተረዳ ነገር ታውቃለችና ለርሷ ድንቅ ኾኖ የሚነገረውን ነገር መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው? መስማትስ የሚቻለው ምን ጆሮ ነው? ማወቅስ የሚቻለው ምን አእምሮ ነው? የእግዚአብሔር የጥበቡ ምላት ስፋትስ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? አንድም ለእግዚአብሔር ለጥበቡ ምላት ስፋት አንክሮ ይገባል፡፡ “በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” /ዘፍ.፫፡፲፮/ ብሎ የፈረደባት ማኀፀን የሕይወት፣ የድኅነት መገኛ ኾነች፡፡ ዕንቆ ጳዝዮን የተባለ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም፡- “እስመ ቀዳሚኒ ሔዋን ኮነት ድንግል ወአስሐታ ዲያብሎስ ለማርያምሂ ድንግል አብሠራ ገብርኤል ወባሕቱ ለሔዋንሰ አስሐታ ዲያብሎስ ወወለደት ቃየልሀ ዘውእቱ ምክንያተ ሞት ወማርያምሰ ሶበ አብሠራ መልአክ ወለደት ቃለ በሥጋ ዘውእቱ መራሔ ኵሉ ኀበ ሕይወት ዘለዓለም - ቀድሞም ሔዋን ድንግል ነበረችና ዲያብሎስ አሳታት እንጂ፤ ድንግል ማርያም ግን ገብርኤል አበሠራት፡፡ ነገር ግን ሔዋንን አሳታት፤ የሞት ምክንያት የሚኾን ቃየልን ወለደች፤ ማርያም ግን መልአክ ባበሠራት ጊዜ ኹሉን ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚመራ አካላዊ ቃልን በሥጋ ወለደች፡፡ የሔዋንን ልብላ ልብላ ማለቷ ዕፀ በለስ የሞት ምክንያት እንደኾነ አስረዳ፡፡ በዚያም አዳም ተድላ ደስታ ካለበት ከገነት ወጣ፡፡ ከድንግል የተወለደ አካላዊ ቃል ግን ዕፀ መስቀል የድኅነት ምክንያት እንደኾነ ገለጠ፡፡ በዚያም መስቀል ቀማኛ ወንበዴ የነበረው ሰው ከአባቱ ከአዳምና ከቀደሙ አባቶች
የዕለተ ረቡዕ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ በድምፅ፡፡
ለማጋራት👉 /channel/Ethiopian_Orthodox/3496
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
ደስ ያለህ ባለ ምሥራች ገብርኤል ሆይ! ወደኛ የመጣ የጌታን ልደት ነግረኸናልና ላንተ የተሰጠ ክብር ፍጹም ነው፡፡ አንድም “ወነዋ ተወልደ ፍስሐ ዘይከውን ለክሙ ወለኩሉ ዓለም - እነሆ ለሕዝቡ ኹሉ የሚኾን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁ” ብለህ /ሉቃ.፪፡፲/ የጌታን ልደት ለኖሎት (ለእረኞች) ነገርኻቸዋልና ለአንተ የተሰጠ ክብር ፍጹም ነው፡፡ “እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ካንቺ ጋራ አንድ ይሆናልና ደስ ይበልሽ” ብለህ /ሉቃ.፩፡፴/ ለእመቤታችን ነግረኻታልና ለአንተ የተሰጠ ክብር ፍጹም ነው፡፡ እንዲህ ካለ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳነሣን ለምኚልን፡፡
፬. መንፈስ ቅዱስ ቢያድርብሽ፣ ኃይለ ልዑል ወልድም ሥጋሽን ቢለብስ ጸጋን አገኘሽ፡፡ መንፈሰ ቅዱስ ከሦስቱ ግብራት ቢከለክልሽ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብለው ከሚመሰገኑት ከሦስቱ አካላት አንዱን ቅዱስ ወለድሽልን፡፡ ሰውን ኹሉ የሚያድን እርሱም ሰው ኾኖ አዳነን፡፡ ሰው ኾኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፭. ቀድሞ ከነበሩት ጋር አንድ ኾኖ አንደበታችን የድንግልን ሥራ ያመሰግናል፡፡ ዛሬ ካሉት ጋር ኾኖም እመቤታችንን ያመሰግናል፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት አገር በዳዊት ባሕርይ ካርሷ ተወልዷልና፡፡ አሕዛብ ሆይ! ኑ እመቤታችንን እናመስግናት /ሃይ.አበ.፷፮፡፳/፡፡ እናትን ኹናለችና፤ ድንግልናም ደርባለችና ኑ እመቤታችንን እናመስግናት፡፡ አካላዊ ቃል ካንቺ ሰው የኾነ አደፍ ጉድፍ የሌለብሽ ድንግል ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ አደፍ ጉድፍ የሌለብሽ ንጹሕ ሽቱ ዕቃ ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ የሽቱን ዕቃ ጢስ እንዳይተንበት ትቢያ እንደይበንበት ቤት ሰፍተው፣ ሰቅለው፣ ተንከባክበው ያኖሩታል፡፡ እርሷንም “መንፈስ ቅዱስ ዐቀባ እምከርሠ እማ ከመ ኢትጌጊ - እንዳትበድል ድንግልን ከእናቷ ሆድ ጀምሮ የጠበቃት መንፈስ ቅዱስ እንዳትረክስም ያነጻት ለወልድ ዋሕድም ማደርያ ያደረጋት እርሱ ነው” ይላታልና /አርጋኖን ዘእሑድ፣ ቁ.፲፰/፡፡ ዐጤ ዘርዐ ያዕቆብም በነገረ ማርያም መጽሐፉ፡- “ንጽሕት ይእቲ እምኵሉ ትሕዝብት ወእምኵሉ ርስሐተ ኀጢአት - እርሷ (እመቤታችን) ከርስሐተ ኀጢአትና ከመጠራጠርም ኹሉ ንጽሕት ናት” ብሏል /ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን፣ ገጽ ፶፮-፶፯/፡፡
ስለ ቀደመ ሰው (ስለ አዳም) ዳግመኛ አዳም የተባለ የክርስቶስ እናቱ ነባቢት ገነት ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ ከአባቱ ዕሪና (አንድነት) ያልተለየ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው እርሱን የወሰንሺው በፍጹም ጌጥ ያጌጠች ንጹሕ የሰርግ ቤት ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ የሰርግን ቤት አስቀድመው በሐር ያንቆጠቁጡል፤ ያነጽፉታል፤ ይጎዘጉዙታል፤ ሽቱ ያረበርቡበታል፤ ሐረግ ወርድ ይሥሉበታል፡፡ እንደዚህም ኹሉ አስቀድመን እንደተናገርን መንፈስ ቅዱስ ድንግልን ከእናቷ ማኅፀን ጀምሮ ጠብቋታልና እንዳትረክስም አንጽቷታልና እንዲህ አለ፡፡ አንድም በየጊዜው የጸጋ ክብር ይጨመርላታልና፡፡
ባሕርየ መለኮቱ ያልለወጠሽ ዕፀ ጳጦስ ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ (ዕፀ ጳጦስ ማለት በሀገራችን ደደሆ፣ እንጆሪ የምንለው ነው) /ዘጸ.፫፡፩-፫/፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም የዚህን ግሩም ምሥጢር “ዲያተሳሮን” በተባለ መጽሐፉ ሲተነትነው ፡- “ፈጣሬ ዓለማት ቅዱስ እግዚአብሔር የወደቀውን ፍጥረቱ ወርዶ ያነሣው ዘንድ፣ ቆሽሾ የነበረው ሕንፃዉንም (ሰውንም) ይወለውለው ዘንድ ተገቢ ነበር፡፡ በመኾኑም ፈጣሪ ራሱ በሰው ልጆች ላይ ፈርዶት የነበረውን ፍርድ የባሕርይ ልጁ እንዲሸከመው ካደረገ (በእርግጥም አድርጐታልና) የሰው ልጅ ወደ ጥንተ ተፈጥሮው ይመለሳል ማለት ነው (በርግጥም ተመልሷል)፡፡ ይህ አካላዊ ቃል፣ በሰው መተላለፍ ምክንያት በቅለው የነበሩት እሾክንና አሜኬላን ያቃጥል ዘንድ የመጣ ነባቢ ፍሕም ነው /ዘፍ.፫፡፲፰፣ ኢሳ.፱፡፲፰/፡፡ መጥቶም በማኅፀነ ድንግል አደረ፤ አነጻው፤ የጭንቅና የርግማን ቦታ የነበረው ማኅፀን ቀደሰው /ዘፍ.፫፡፲፮/፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ ያየው ነበልባል ሐመልማሉን አላጠፋውም፤ ይልቁንም እንዲለመልም አደረገው እንጂ /ዘጸ.፫፡፪-፫/፡፡ የነጠረ ወርቅ የሚመስል አካልም ወደ ነበልባሉ ገባ፤ ኾኖም አሁንም እሳቱ አልፈጀውም፡፡ ይኸውም በዘመኑ ፍጻሜ ሊመጣ ላለው ነባቢ እሳትና የድንግልን ማኅፀን አለምልሞ ቁጥቋጦውን እንደከደነውም እንደሚከድናት የሚያስረዳ ነው” ብሏል፡፡ ዳግመኛም አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫ የእሳተ መለኮት መምጣት ምክንያቱ ሲገልጽ፡- “… (ጌታችንም) የዓለምን ኃጢአት በትከሻው ተሸክሞ ወደ ዕፀ መስቀል ወጣ፡፡… ያን ጊዜ እግዚአብሔር እሾኽና አሜኬላ ይብቀልብህ ብሎ በረገመው ጊዜ በአዳም ሥጋ የበቀለ የኃጢአት እሾኽ ተቃጠለ” ብሏል /መጽሐፈ ምሥጢር ፲፱፡፳፩/፡፡
በኪሩቤል አድሮ የሚኖረው ሰማያዊ መለኮትን በሥጋ የተሸከምሽው ማኅደርም የተባልሽ እመቤትነትን ከገረድነት፣ እናትነትን ከድንግልና ጋር አስተባብረሽ የያዝሽ ሰማይ ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ ስለዚህ ነገር፡- “አምላክ ለኾነ ለሥጋ ከሥላሴ ጋራ በአንድነት ምሥጋና ይገባዋል፤ በምድርም ዕርቅ ተወጠነ” እያልን ንጹሐን ከኾኑ መላእክት ጋር በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኝተን እናመስግን፡፡ ክብር የክብር ክብር ያለው እርሱ አንቺን ለእናትነት መርጧልና ንጹሐን ከኾኑ መላእክት ጋር በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኝተን እናመስግን /ሉቃ.፪፡፳/፡፡ አንቺን ለእናትነት ከመረጠ ልጅሽ ጽንዕት ሥርጉት በቅድስና በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳነሳን ለምኚልን፡፡
፮. ከቅዱሳን ክብር የእመቤታችን ክብር ይበልጣል፡፡ አካላዊ ቃልን ለመቀበል በቅታ ተገኝታለችና፡፡መላእከት የሚፈሩትን፣ ትጉሃን በሰማያት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማኅፀንዋ ቻለችው፡፡ እንዲህም ከኾነ ከመላእክት ትበልጣለች፤ ከሱራፌልም ትበልጣለች፤ ከሦስቱ አካል ላንዱ ማደሪያ ኾኖለችና፡፡ ኢትዮጲያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስም ይህን በኆኅተ ብርሃን መጽሐፉ ላይ ሲገልጽ “አንቲ ተዓብዪ እምኪሩቤል ወትፈደፍዲ እምሱራፌል፣ እምሱራፌል ወኪሩቤል በሠረገላ እሳት ይጸውርዎ ወበምጽንዐ እሳት ይጼንዑ መንበሮ፤ ወአንቲሰ ጾርኪዮ በከርሥኪ ወሐዘልኪዮ በዘባንኪ ወሐቀፍኪዮ በአብራክኪ ህየንተ ሠረገላ እሳተ አብራክኪ ኮነ ወህየንተ ምጽንዐቲሁ ዘእሳተ እደውኪ ኮና - ከኪሩቤል ይልቅ አንቺ ትበልጫለሽ፤ ከሱራፌልም ይልቅ አንቺ ትልቂያለሽ፤ ኪሩቤልና ሱራፌል በእሳት ሠረገላ ተሸክመውታልና፤ አንቺ ግን በማኅፀንሽ ወሰንሺው፤ በዠርባሽም አዘልሺው፤ በጉልበቶችሽም ዐቀፍሽው፤ ጉልበቶችሽም እንደ እሳት ሠረገላ ኾኑ፤ እጆችሽም እንደ እሳት አዕማድ ኾኑ” በማለት የተሰጣት ክብር ከኪሩቤል ከሱራፌል የበለጠ መኾኑን አስተምሯል፡፡
የነቢያት ሀገራቸው ኢየሩሳሌም ይህች ናት፡፡ መንግሥተ ሰማያትን የሚያወርሰን ከእርሷ በነሣው ሥጋ ምክንያት ነውና ደስ ብሏቸው የሚኖሩ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የመላእክት ማደሪያቸው ይህቺ ናት፡፡ በድንቁርና በቀቢፀ ተስፋ ለነበሩ ሰዎች ዕውቀት ተሰጣቸው፤ ክርስቶስ ተወለደላቸው /ኢሳ.፱፡፪/፡፡ ወንጌል ተጻፈላቸው /ሉቃ.፩፡፩-፬/፡፡ በቅዱሳን አድሮ የሚኖር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ሰው ኹኗዋልና በሞተ ሥጋ፣ በሞተ ነፍስ ለነበሩ ሰዎች ልጅነት ተሰጣቸው /ዮሐ.፩፡፲፫/፡፡ በኃጢአት በክሕደት ለነበሩ ሰዎች ሃይማኖት (አሚን) ተሰጣቸው /ማቴ.፬፡፲፬/፡፡ ተወዳጆች ሆይ! ይህን ድንቅ ምሥጢር ኑ እዩ፡፡ ስለ ተገለጸን ምሥጢር ምስጋና አቅርቡ፡፡ ከዚህ ቀደም ሰው ኾኖ የማያውቀው እንግዲህም ወዲህ
የረቡዕ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ
ለምስጋና ሦስተኛ፣ ለፍጥረት አራተኛ ቀን በሚኾን በዚህ ዕለት ከወትሮ ይልቅ መላእክትን አስከትላ እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ምንጻፍ ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኾናም፡- “ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም” ትለዋለች፡፡ እሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ይቆማል፡፡ ከባረከችው በኋላም ምስጋናዋን “ኵሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ ብፅዕት አንቲ…” ብሎ ይጀምራል፡፡
@Ethiopian_Orthodox
፰. የሰው ኹሉ አእምሮ በአፍአ በውስጥ በሥጋ በነፍስ ደስ ይላታል፡፡ “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ- አምላክ ለኾነ ለሥጋ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ በአንድነት ምስጋና ይገባዋል፡፡ በምድርም ዕርቅ ተወጠነ፡፡ የሰው ግዕዛኑ ይሰጠው ዘንድ” እያሉ ከመላእክት ጋራ (እንደ መላእክት) ንጉሥ ክርስቶስን ያመሰግኑታል /ሉቃ.፪፡፲፬/፡፡ አንድም “ዮም አሐደ መርዔተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመ ይሰብሕዎ ለክርስቶስ በቃለ አሚን- ” እንዲል የሰው ፍቅር አገብሮት አምላክ ሰው ቢኾን ሰውም አምላክ ቢኾን በመላእክት ዘንድ ምስጋና ተደረገ፡፡ በምድርም አንድነት ተደረገ፤ ኖሎት (እረኞች) ከመላእክት ጋራ አንድ ኾነው አመሰገኑ /ሉቃ.፪፡፳/፡፡ “ኃጢአትን አጠፋ፤ በመስቀልም ተሰቅሎ ፍዳን አጠፋ፡፡ በመቃብርም ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አጠፋ፡፡ በሲዖልም ሞተ ነፍስን አጠፋ፡፡ ሥራ በሠራበት ኹሉ ድኅነትን አደረገልን” እንዲል የቀደመ መርገመ ሥጋ መረገመ ነፍስን አጥፍቷልና ኖሎት ከመላእክት ጋራ አንድ ኾነው አመሰገኑ /ሃይ.አበ.፹፱፡፳፬/፡፡ የጸላኢ የዲያብሎስ ምክሩን አፍርሶበታልና ኖሎት ከመላእክት ጋራ አንድ ኾነው አመሰገኑ፡፡ በመቅድመ ወንጌል “ወበከመ ኮነ በጉህለት ተኀብአ ሰይጣን ውስተ ሥጋ ከይሲ ከማሁ ኮነ ድኅነትነ በተሰውሮ ቃለ እግዚአብሔር ዘመድነ- ሰይጣን በተንኰል በሥጋ ከይሲ እንደተሠወረ እኛም ከፍዳ መዳናችን ቃለ እግዚአብሔር በባሕርያችን በመሠወሩ ኾነ” እንዲል በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ ቢያስትበት በሥጋ ተሰውሮ አድኖበታልና ኖሎት ከመላእክት ጋራ አንድ ኾነው አመሰገኑ፡፡ ዲያብሎስ “ሥጋን በመቃብር ነፍስን በሲኦል ተቆራኝቼ እኖራለሁ” ብሎ ነበርና የመከረባቸውን ሥጋንና ነፍስን ተዋሕዶ አድኖበታልና ኖሎት ከመላእክት ጋራ አንድ ኾነው ንጉሥ ክርስቶስን አመሰገኑ፡፡ ይኸውም ጥበበኛው ሰሎሞን “ጠቢብ የኃያላንን ከተማ ይገባባታል፥ የሚታመኑበትንም ኃይል ያፈርሳል” እንዳለው ነው /ምሳ.፳፩፡፳፪/፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፤ የአዳምንና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤቸውን አጥፍቶላቸዋልና /ቈላ.፪፡፲፬/ “አምላክ ለኾነ ለሥጋ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ በአንድነት ምስጋና ይገባዋል፡፡ በምድርም ዕርቅ ተወጠነ፡፡ የሰው ግዕዛኑ ይሰጠው ዘንድ” እያሉ መላእክት አመሰገኑት /ሉቃ.፪፡፲፬/፡፡ ዲያብሎስ በአዳምና በሔዋን የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ ሥቃይ አጽንቶ “ስመ ግብርናት ጽፋችሁ ብትሰጡኝ አቀልላችኋለሁ” ብሏቸው አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋንም አመቱ በዲያብሎስ ብለው ጽፈው ሰጥተውት ነበር፡፡ ዲያብሎስም ያንን በእብነ ሩካም ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል ጥሎት ነበር፡፡ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ኾኖ ሲመጣ ግን ዲያብሎስ በዮርዳኖስ የጣለውን ሲጠመቅ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ እንደ ሰውነቱ ተረግጦ አጥፍቶታል፤ በሲኦል የጣለውንም በዕለተ ዐርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ አጥፍቶላቸውና መላእክት አመሰገኑት /ቈላ.፪፡፲፬/፡፡ በዳዊት ሀገር ከዳዊት ባሕርይ የተወለደ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምና ሔዋንን ነጻ አድርጓቸዋልና አመሰገኑት /መዝ.፻፴፪፡፲፩/፡፡ አዳምንና ሔዋንን ነጻ ካደረጋቸው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፱. በዚህ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ኹሉ የምታበራ (ዕውቀትን የምትገልጥ)፣ ጠፈር ደፈር የማይከለክልህ፣ መዓልትና ሌሊትም የማይፈራረቅብህ ብርሃን ዘበአማን (እውነተኛ ብርሃን) ክርስቶስ ሆይ! ስለ ሰው ፍቅር ልሙት ልሰቀል ብለህ ወደ ዓለም በመምጣትህ ፍጥረት ኹሉ ደስ አለው፡፡ አዳምን ከስሕተት፣ ሔዋንንም ከሞት ፃዕረኝነት (ከመጣባቸው ፍዳ) ነፃ አድረገኻቸዋልና ለእኛ በተደረገው ክብር መላእክት ከእኛ ጋር ደስ አላቸው /ሃይ.አበ.፷፰፡፴፪/፡፡ የሰው ፍቅር አገብሮህ ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስነህ ሲያዩህ “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር” ብለው መላእክት አመሰገኑ፡፡ ከዚህም የተነሣ በጣዕም ላይ ጣዕም በጸጋ ላይ ጸጋ ተጨምሮላቸው ደስ ብሏቸዋል፡፡ እኛም ቅብዐ ትፍስሕት የሚኾን መንፈስ ቅዱስን አንድም ሀብተ ልደትን ተቀብለን ከመላእክት ጋር ደስ አለን፤ አመሰገንንህም፡፡ እንስሳት፣ አራዊት ስንኳ ሳይቀሩ ሰው ከፈጣሪው ጋር በመታረቁ ደስ ብሏቸዋል፡፡
ጽንዕት በድንግልና ቅድስት እመቤታችን ሆይ! ብርሃን ከሚባል ልጅሽ ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
ይህንን ሲጨርስ በያዘችው መስቀለ ብርሃን ባርካው ዐረገች፤ እርሱም እጅ ነሥቶ ቀርቷል፡፡
አነሣሥቶ ላስጀመረን አስጀምሮም ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን፡፡
ለሌሎች ያካፍሉ 👉 /channel/Ethiopian_Orthodox/3486
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
“ለምኚልን” ሲልም ልክ በዚህ ምድር እንደነበረው ዓይነት ልመና ከዚያ በኋላ ኖሮባት አይደለም፡፡ ስንኳን በሷና በሌሎችም የለባቸውም፡፡ በቀደመ ልመናዋ የምታስምር ስለ ኾነ እንዲህ አለ እንጂ፡፡ ይኸውም በቃል ኪዳኗ ማለት ነው፡፡ አንድም በቁሙ ይተረጐማል፡፡ ማዘከር (ማሳሰብ) አለና፡፡
“ሰአሊ ለነ ቅድስት” የሚለው ቅዱስ ኤፍሬም የተናገረው አይደለም፡፡ “ታድያ ይህን የጨመረው ማን ነው?” በሚለው ላይም ኹለት ዓይነት አመለካከለት አለ፡፡ “ቅዱስ ያሬድ ለዜማ መከፈያ ተናግሮታል” የሚሉ አሉ፤ “የኋላ ሊቃውንት ተናግረውታል” የሚሉም አሉ፡፡
፪. ወዶም አልቀረም ዘር ምክንያት ሳይኾነው ከድንግል በሥጋ ተወለደ፡፡ “አኮ ወልደ ማርያም በመለኮቱ አላ በከመ ሥርዓተ ትሥብእቱ- በመለኮቱ የማርያም ልጅ አይደለም፤ በተዋሐደው ሥጋ ነው እንጂ” እንዲል ድርሳነ ቄርሎስ በመለኮት ሳይኾን በሥጋ ተወልዶ አዳነን፡፡
ከእናንተ መካከል፡- “ልደቱ በዘርዕ ያላደረገው እንበለ ዘርዕ ያደረገው ስለ ምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡-
· አንደኛ፡ “ልደት ቀዳማዊ ተዐውቀ በደኃራዊ” እንዲል ፭ ሺሕ ከ፭፻ ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ያለ አባት መወለዱ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት እንደ ተወለደ ለማጠየቅ፤
· ኹለተኛ ደግሞ ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን በዘርዕ በሩካቤ ተወልዶ ቢኾን ኖሮ መናፍቃን “ዕሩቅ ብእሲ ነው” ባሉት ነበርና ነው፡፡ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ ይህን ሲያብራራው፡- “ሰውም በኾነ ጊዜ እንደ ዕሩቅ ብእሲ በዘር በሩካቤ አልተወለደም፤ አምላክ ሰው ኾነ እንጂ፡፡ እንደ ዕሩቅ ብእሲ በዘር በሩካቤ ተወልዶ ቢኾንስ ብዙ ሰዎች በተሳሳቱ ነበር፤ አምላክ ሰው መኾኑንም ሐሰት ባደረጉት ነበር” ይላል /ሃይ.አበው. ፷፡፲፱/፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም፡- “እንደ እኔስ በዘር በሩካቤ ተወልዶ ቢኾን ብዙ ሰዎች ዕሩቅ ብእሲ ባሉት ነበር፤ አምላክነቱንም በካዱት ነበር” ይላል /ሃይ.አበ. ፷፮፡፴፪/፡፡
አሁንም ከእናንተ መካከል፡- “ያውስ ቢሆን ተፈትሖ ካላት ያላደረገው፣ ተፈትሖ ከሌላት ያደረገው ስለ ምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡-
· አንደኛ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች” ተብሎ የተነገረውን /ኢሳ.፯፡፲፬/ ለመፈጸም ሲኾን፤
· ኹለተኛው ደግሞ ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡ ይኸውም አዳም ከኅቱም ምድር ተገኝቷል /ዘፍ.፩፡፳፮/፤ ጌታም በኅቱም ማኅፀን ተወልዷል /ሕዝ.፵፬፡፩/፡፡ ሔዋን በኅቱም ገቦ (ጐን) ተገኝታለች /ዘፍ.፪፡፳፩/፤ ጌታም በኅቱም ማኅፀን ተወልዷል፡፡ ቤዛ ይሥሐቅ የሚኾን በግዕ ከኅቱም ጉንድ ተገኝቷል /ዘፍ.፳፪፡፲፫/፤ ቤዛ ዓለም ክርስቶስም በኅቱም ማኅፀን ተወልዷል፡፡ ጽምዐ እስራኤልን ያበረደ ውሃ ከኅቱም እብን (ዐለት) ተገኝቷል /ዘጸ.፲፯፡፮/፤ ጽምዐ ነፍሳትን ያበረደ ማየ ሕይወት ጌታም በኅቱም ማኅፀን ተገኝቷል፡፡ ጽምዐ ሶምሶንን ያበረደ ውሃ በኅቱም መንሰከ አድግ (የአህያ መንጋጋ) ተገኝቷል /መሳ.፲፭፡፲፱/፤ ጽምዐ ኃጥአንን ያበረደ ማየ ሕይወት ጌታም በኅቱም ማኅፀን ተገኝቷል፡፡ የዚህ ኹሉ ምሳሌ ፍጻሜው አንድ ነው፡፡ ይኸውም ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‘ከመ ትኩን መራሒተ ለሃይማኖት ዐባይ - ለደገኛው ሃይማኖት መሪ ትኾን ዘንድ’ /ሃይ.አበ.፷፮፡፴፪/ እንዲላት እመቤታችን ጌታን ብትወልደው ማኅተመ ደንግልናዋ እንዳልተለወጠ ኹሉ እርሱም ሰው ሲኾን አምላክነቱ ላለመለመጡ ምሳሌ ነው፡፡ ዳግመኛም እርሷ “ድንግል ወእም” ስትባል መኖሯ እርሱም “አምላክ ወሰብእ” ሲባል ለመኖሩ ምሣሌ ነው፡፡
እናም አዳምን ያድነው ዘንድ የፈቀደ አምላክ ከይሲ ዲያብሎስ ያሳታት ሔዋንን “ጻርሽን ጋርሽን ምጥሽን አበዛዋለሁ” ብሎ እግዚአብሔር ከፈረደባት በኋላ ሊቁ አባ ሕርያቆስ “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኀያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት- የሰው ፍቅር ከዙፋኑ ስቦ ጐትቶ አወረደው፤ ከሞትም አደረሰው” እንዲል /ቅዳ.ማር. ቁ. ፻፳፭/ ሰውን ወደደና ሔዋንን ነጻ አደረጋት /ገላ.፭፡፩/፡፡ ሔዋንን ነጻ ካደረገ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፫. ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ አዳምን ነጻ ያደርገው (ያድነው) ዘንድ የፈቀደ፣ ሔዋንንም ወድዶ ነጻ ያደርጋት ዘንድ ሰው የኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው /ዮሐ.፩፡፲፬/፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለው ስም የመለኮት ብቻ ወይም የትስብእት ስም ብቻ አይደለም፡፡ “ወእነግር አነሂ ከመ ኢመፍትው እስምዮ ለቃለ እግዚአብሔር ክርስቶስ ዘእንበለ ትስእብት ወኢ ለትስብእት ዘእንበለ መለኮት ክርስቶስሀ ይሰመይ ወእም ቅድመ ትሥጉት አልቦ ዘይሰምዮ በዝንቱ ስም ለቃለ እግዚአብሔር ክርስቶስ- ክርስቶስ ሲል ብትሰማ ብቻ አምላክ እንደኾነ ብቻ ሰውም እንደኾነ አታስብ፡፡ አንድ እንደ መኾኑ ሰው የኾነ አምላክ ነው እንጂ” /ሃይ.አበ.፷፰፡፵/ እንዲል ከኹለት አካል አንድ አካል ከኹለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ቢኾን የወጣለት ስም ነው እንጂ፡፡
አዳምን ነጻ ያደርገው ዘንድ ሰው የኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ ላይ አደረ /ዮሐ.፩፡፲፬/፡፡ ለአባቱ እንደ አንድ ልጅ ክብር የሚኾን ክብሩንም አየንለት፡፡ ልጅ ለአባቱ አንድ የኾነ እንደኾነ ደጃፍ የመለሰው ማጄት የጎረስው ኹሉ ገንዘቡ ነው፡፡ ለእርሱም “እስመ ኵሉ ዘቦ ለአቡየ ዚኣየ ውእቱ- ለአብ ያለው ኹሉ የእኔ ነው” /ዮሐ.፲፮፡፲፭/ እንዲል የአብ ገንዘብ ኹሉ ገንዘቡ ነውና ለአባቱ እንደ አንድ ልጅ የሚኾን ክብሩን አየንለት፡፡ “ወይሰገድ ከመዋሕድ- እንደ አባቱ ይመለካል” እንዲል ለአባቱ እንደ አንድ ልጅነቱ የሚኾን ክብሩን አየንለት፡፡ የአባቱን ጌትነት በደብረ ሲና እንዳየነ /ዘጸ.፲፱/ የእርሱንም ጌትነት በደብረ ታቦር አየንለት /ማቴ.፲፯፡፩-፰/፡፡ አባቱ በኤልያስ አድሮ አንድ ምዉት /፩ኛ ነገ.፲፯/፣ በኤልሳዕ አድሮ ኹለት ምዉት ሲያስነሣ እንዳየነው /፪ኛ ነገ. ፬/፤ እርሱም ሥጋን ተዋሕዶ የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን ሲያስነሣ አየነው /ዮሐ.፲፩/፡፡ ይህን ጠቅለል አድርጐ ቅዱስ ባስልዮስ ሲናገረው፡- “ስለ አብ የተናገርነው ኹሉ ለወልድ ገንዘቡ ነው፡፡ በመልክ ይመስለዋል፤ በባሕርይ ይተካከለዋልና፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ ለአባቱ አንድ እንደ ኾነ ልጅ ክብር ያለ ክብሩን አየን አለ” ይላል /ዮሐ.፩፡፲፬፣ ሃይ.አበ.፴፫፡፳፰/፡፡
የመጽሐፍ ልማድ ኾኖ የብሉዩን ለአብ የሐዲሱንም ለወልድ ሰጥቶ ተናገረ እንጂ ኹሉም በኹሉ አሉ፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ያውስ ቢኾን (ቅዱስ ኤፍሬም) ወዴት ነበርና ነው አየንለት የሚለው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- አየንለት የሚለው የብሉዩን የእነ ሙሴን ዐይን ዐይን አድርጎ፤ የሐዲሱን ደግሞ የእነ ጴጥሮስን ዐይን ዐይን አድርጎ መናገሩ ነው፡፡ ይኸውም አባ ሕርያቆስ የሓዋርያትን መብል መብል አደርጎ፡- “በላዕነ ወሰተይነ ምስሌሁ - ከእርሱ ጋር በላን ጠጣን” እንዳለው ማለት ነው /ቅ.ማር. ቁ.፹፮/፡፡
ይህ ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የኾነው ክብሩን ያየንለት ወዳጅ ይቅር ይለን ዘንድ ወደደ፡፡ ይቅር ይለን ዘንድ ከወደደ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና፤ እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
የሰኞ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ
ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችን ከባረከችው በኋላ ምስጋናውን የጀመረው “ፈቀደ እግዚእ…” ብሎ ነው፡፡
፩. በመቅድመ ወንጌል “ወአልቦቱ ካልእ ሕሊና ዘንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢያቱ - በኃጢአቱ ከማዘን፣ ከማልቀስ በቀር ሌላ ግዳጅ አልነበረውም” እንዲል ጌታ ፭ ሺህ ከ፭፻ ዘመን በግብርናተ ዲያብሎስ ያዝን ይተክዝ የነበረ አዳምን ነጻ ያደርገው (ያድነው) ዘንድ ወደደ፡፡ ምድራዊ ንጉሥ የተጣላውን አሽከር “ሰናፊልህን (ልብስህን) አትታጠቅ፤ እንዲህ ካለ ቦታም አትውጣ” ብሎ ወስኖ ያግዘዋል፡፡ በታረቀው ጊዜ ግን ርስቱን፣ ጉልበቱን፣ ቤቱን፣ ንብረቱን እንደሚመልስለት ኹሉ ንጉሠ ሰማይ ወምድር እግዚአብሔርም “ጥንቱንም መሬት ነህና ወደ መሬት ተመለስ” /ዘፍ.፫፡፲፱/ ብሎ ፈርዶበት የነበረ አዳምን ይቅር ብሎ ወደ ቀደመ ቦታው ወደ ገነት፣ ወደ ቀደመ ክብሩ ወደ ልጅነት ይመልሰው ዘንድ ወደደ /ሉቃ.፳፫፡፵፫/፡፡
እንኳን አደረሳችሁ!
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
ጾመ ፍልሰታ ለማርያም
ነሐሴ ፩
በነገረ ማርያም ተጽፎ እንደምናገኘው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሲሔዱ አይሁድ “እንደ ልጇ ተነሣች፤ ዐረገች እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት” ብለው በዓመፃ ተነሡ:: ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊም አጎበሩን ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጥቶታል፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ከዚህ ላይ “ስምንት ወር ሙሉ ምን ይዘው ቆይተው ነሐሴ ላይ ሱባዔ ገቡ?” የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ በእውነቱ ቅዱሳን ሐዋርያት ከስብከተ ወንጌል፣ ከጾም፣ ከጸሎት፣ ከገቢረ ተአምራት፣ ተለይተው እንደማያውቁ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ምስክር ነው፡፡
በመኾኑም እመቤታችን ካረፈችበት ቀን ከጥር ወር ጀምሮ እስከ ነሐሴ ድረስ ጥያቄያቸውንና ጸሎታቸውን ባያቋርጡም ከሰው ተለይተው ሱባዔ ገብተው ጾም ጸሎት የጀመሩት ግን ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ነው፡፡ ቀድሞስ የክብር ባለቤት የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኾነው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ተሠውራባቸው እንዴት ዝም ብለው ይቀመጣሉ? ሁለት ሱባዔ ካደረሱ በኋላም የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን ሰምቶ ነሐሴ ፲፭ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀንም እንደ ልጇ እንደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ትንሣኤ” ያሰኘውም ይህ ታሪክ ነው::
ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?” ብሎ ትንሣኤዋን ባለማየቱ ኀዘን ስለ ተሰማው ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” እንዲል፡፡ እመቤታችንም “አይዞህ አትዘን፤ ባልነጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃል” ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና ማረጓን እንዲነግራቸው አዝዛ የያዘቸውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ እርሱም ትእዛዟን ተቀብሎ በክብር ከተሰናበታት በኋላ ወደ ሐዋርያት ሔዶ እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ “የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ?” አላቸው፡፡ እነርሱም “አግኝተን ቀበርናት” ሲሉት “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይኾናል?” አላቸው::
በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠፀ ስለ እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ኹሉ መቀበል እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡ ቅዱስ ቶማስም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ ሲሰማው ቆየ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ተቈጥቶ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ሔዶ መቃብሯን ቢከፍት የእመቤታችንን ሥጋ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ ቆመ፡፡ ቅዱስ ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ” ብሎ የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንደዚሁም አባቶች ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ቀጭን ልብስና በራሳቸው የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው:: በዓመቱ ቅዱሳን ሐዋርያት “ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?” ብለው ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰባስበው ጌታችን ሥጋዋን እንዲሰጣቸው በጠየቁበት በዚሁ ወቅት ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ቢይዙ ጌታችን ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል /ትርጓሜ ውዳሴ ማርያም/፡፡
ይህንን ትምህርት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩-፲፭ ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ኾኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል /ፍት.ነገ.አን.፲፭/፡፡ ይህ ጾምም “ጾመ ማርያም (የማርያም ጾም)” ወይም “ጾመ ፍልሰታ ለማርያም (የማርያም የፍልሰቷ ጾም)” እየተባለ ይጠራል፡፡
‹ፍልሰት› የሚለው ቃልም “ፈለሰ ሔደ፤ ተሰደደ” ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡፡
‹ፍልሰታ ለማርያም› ሲልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን የሚያስረዳ መልእክት አለው፡፡ በጾመ ፍልሰታ በቤተ ክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመፀነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡
እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር በማመሣጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለተዋሕዶ በእግዚአብሔር መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡
በጾመ ፍልሰታ ባሕታውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት የሰይጣንን ፈተና ድል ለማድረግ እንዲቻላቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡፡ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ እኛም የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ በማሰብ ከልጇ ከወዳጇ የሚገኘውን ጸጋና በረከት ተስፋ በማድረግ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ፈለግ ተከትለን በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን፤ የምንችል ደግሞ አስቀድሰን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡ በተጨማሪም ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ኹላችንም ጌታችን በስሙ ሁለትም ሦስትም ኾነን ለጸሎትና ለመልካም ሥራ ብንሰባሰብ እርሱ በመካከላችን እንደሚገኝ የገባልንን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ /ማቴ.፲፰፥፳/ በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት በጌታችን፣ በእመቤታችንና
የዕለተ አርብ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ በድምፅ፡፡
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
የኾነው የተደረገው ኹሉ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ መኾኑን አውቋል፡፡ ኾኖም ግን ሌሎች በዙርያ ያሉ ሰዎች ይህን ነገር ሊያምኑት ስለማይችሉ በስውር መተው የተሻለ የጽድቅ ሥራ መስሎ ታየው፡፡ ይኸውም በግብር እንዲገናኛት ሳይኾን እንዲያገለግላት፣ እንዲጠብቃት የሰጡት ካህናት ይህን የእግዚአብሔር ሥራ ሊያምኑት እንደማይችሉ ስለሚያውቅ ነው፡፡ “የመለኮታዊው ልጅ አባት ነኝ ብል ኃጢአት ነው” በማለት በስውር ሊተዋት አሰበ፡፡ ልጇ (ክርስቶስ) በድንግልና የተፀነሰ በድንግልናም የሚወለድ መኾኑን ቢያውቅም ይህን የሚጠረጥሩ ሰዎች እንዳይኖሩ ከእርሷ ተለይቶ መኖርን ፈራ፡፡ መልአኩም መጥቶ “ኢትፍራህ ነሢኦታ ለማርያም ፍኅርትከ - ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ” አለው፡፡ ወንጌላዊው ማቴዎስም ከዚያ በኋላ በጽድቅ በንጽሕና ከእርሱ ጋር እንደኖረች ዮሴፍም እንደወሰዳት ይነግረናል፡፡ ለዚህም ነው ካህናት በኋላ ዘመን ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስን እመቤታችን ድንግል ናት ስላለ ወግረው የገደሉት፡፡ ዳግመኛም ካህኑ ዘካርያስ ጌታችን እንደተናገረው በቤተ መቅደስ ውስጥ እንዲገደል ያደረጉት፡ ሕፃናት በሄሮድስ ትዕዛዝ በሚገደሉበት ሰዓት ልጁ ዮሐንስን በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና ስለሚወለደው ክርስቶስ ምስክር እንዲሰጥ ወደ በረሐ እንዲሸሽ በማድረጉ ነው /ማቴ.፳፫፡፴፭/፡፡
አንዳንድ ልበ ስሑታን እመቤታችን ጌታን ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር በግብር ተገናኝታለች ለሚሉን እንዲህ ብለን እንመልስላቸዋለን፡- “ያቺ ማኅደረ መለኮት የኾነች ድንግል፣ ያቺ መንፈስ ቅዱስ የጸለለባት እመቤት እንደምን ሟች ከኾነ ዕሩቅ ብእሲ ጋር ተመልሳ በግብር ትገናኛለች ተብሎ ይታሰባል? እንደምንስ ዳግም በምጥ በጋር ትወልድ ዘንድ በግብር ተዋውቃለች ተብሎ ይታሰባል? እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሴቶች ኹሉ ተለይታ ንዕድ ክብርት መኾኗን መልአኩ ከተናገረ ከጥንት (ከእናቷ ማኅፀን) አንሥቶ ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ ንጽሕት ነበረች ማለት ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይኾን በምጥ በጋር ከመውለድ የተለየች ናት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እመቤታችን ዳግመኛ ከዮሴፍ ጋር በግብር ተዋውቃ በምጥ በጋር ትወልዳለች ተብሎ ፈጽሞ ሊታሰብ አይገባውም፡፡ በሰብአ ትካት ጊዜ ከኖኅ ጋር ወደ መርከብ የገቡ እንስሳት ስንኳ ከግብር የተለዩ ከነበሩ አማኑኤልን በግብር በማኅፀኗ የተሸከመች እመቤታችንማ ፈጽማ እንዲህ በግብር ተዋውቃለች ተብሎ ሊታሰብ አይገባውም፡፡ ከመርከቡ ውስጥ ከኖኅ ጋር የነበሩ እንስሳት በግብር ያልተዋወቁት ኖኅ ከልክሏቸው ነው፤ እመቤታችን ግን ከዚህ ግብር የተለየችው በፈቃዷ ነው፡፡ በንጽሕና በቅድስና እንደወለደች ኹሉ ንጽሕናዋና ቅድስናዋም እንደዚያ ኾኖ እንዲዘልቅ ፈቃዷ ነበር፡፡
የአሮን ልጆች እግዚአብሔር ያላዘዘውን እሳት በእግዚአብሔር ፊት በማቅረባቸው በሞት ከተቀጡ /ዘሌ.፲፡፩-፪/ እመቤታችንማ እንዴት? ወይንን የሚነግዱ ሰዎች በወይኑ ላይ ውኃ ቢጨምሩበት ቅጣታቸው የበዛ ከኾነ እምቤታችንማ እንዴት? አንዳንድ ሰዎች የጌታ ወንድሞች ተብለው የሚጠሩ ልጆች ስላሉ እመቤታችን የወለደቻቸው ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ጌታችንም የዮሴፍ ልጅ መባሉን ሊያስተውሉ ይገባል፡፡ ይህም አይሁድ ብቻ ሳይኾን እመቤታችንም እንዲህ አድርጋ ትናገር ነበር፡፡ “እስመ ናሁ አቡከኒ ወአነኒ ሠራሕነ እንዘ ነሐሥሠከ- እነሆ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን” እንዲል /ሉቃ.፪፡፵፰/፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ዮሴፍ እመቤታችንን ወደ ቤቱ እንዲወስዳት የነገረው አንደኛው፡ በሐሰት ሊከሷት የሚችሉትን ስዎች ጥርጣሬ እንዳይኖራቸው ለማድረግ፤ በተለይ ደግሞ ከመልአኩ ፀንሳ ተገኘች ብለው ሊገድሏት ከሚችሉ ሰዎች ሊጠብቃት ነው፡፡ በእነዚህ ሰዎች ዘንድ አንድ የተለመደ ወሬ ነበር፡፡ ይኸውም “ድንግል በድንግልና ትወልዳለች፤ ድንግሊቱ በመውለዷ ምክንያትም ከተማይቱ ትጠፋለች፤ ክህነታችን ሀብተ ትንቢታችን ኹሉ ይወገዳል” የሚል ነው፡፡ ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንድምትወልድ የተናገረው ኢሳይያስን በመጋዝ ተርትረው እንዲገደል ያደረጉት ለዚሁ ነበር /ኢሳ.፯፡፲፬/፡፡
ድንግሊቱ የበኵር ልጇን ወለደች፤ ነገር ግን ማኅተመ ድንግልናዋ አልተለወጠም፡፡ … የበኵር ልጇንም እስክትወልድ ድረስ (ዮሴፍ) በንጽሕና በቅድስና ከእርሷ ጋር ኖረ /ማቴ.፩፡፳፭/፡፡ ይህ ቃል የተነገረው ዮሴፍ እመቤታችንን ወደ ቤቱ ከወሰዳት በኋላ ነው፡፡ “ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ” ብሎ ቀጥሎም “የበኵር ልጇንም እስክትወልድ ድረስ (በግብር) አላወቃትም” እንዲል /ማቴ.፩፡፳፬-፳፭/፡፡ በሌላ አገላለጽ ወደ ቤቱ ወሰዳት፤ ነገር ግን በግብር አልተዋወቁም ማለት ነው፡፡ ወደ ቤቱ የወሰዳት ከፀነሰች በኋላም ቢኾን እጮኛዋ ስለኾነ ነው፡፡ የበኵር ልጇንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም ማለትም እንኳንስ በግብር ቀርቶ በሐሳቡም ከእመቤታችን ጋር ሌላ ነገር ለማድረግ አላሰበም ተብሎ ይተረጐማል፡፡ እስክትወልድ ድረስ ማለትም ሰዎች እመቤታችን የፀነሰችው በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንጂ በዘርዐ ብእሲ እንዳልኾነ እንደተረዱ የሚያስገነዝብ ነው፡፡
ዳግመኛም የበኵር ልጇንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም ማለት ምንም እንኳ እመቤታችንና ዮሴፍ በፈቃዳቸው በንጽሕና በቅድስና ለመኖር ቢያስቡም ጸጋ መንፈስ ቅዱስም ረድቶዋቸዋል ማለት ነው፡፡ ጌታችን ከተወለደ በኋላ ያለው ቅድስናቸው ግን የራሳቸው ነጻ ፈቃድ ነው፡፡
ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በግብር እንዳይተዋወቁ ከልክሎዋቸው እንደነበርና ጌታ ከተወለደ በኋላ ግን በራሳቸው ምርጫ በንጽሕና በቅድስና እንደኖሩ ለመግለጽ “እስከ” በሚለው ቃል ነግሮናል፡፡ የበኵር ልጇን እስክትወልድ ድረስ በንጽሕና በቅድስና አብሯት ኖሯል፡፡ እንግዲህ እስከ የሚለው ቃል ስለተጠቀሰ ዮሴፍ ከዚያ በኋላ በግብር አውቋታል ተብሎ ድምዳሜ ሊወሰድ ይችላልን? እስከ የሚለው ቃል መጨረሻ የሌለው እስከ ነው፡፡ “ጌታ ጌታዬን፡- ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው” ተብሎ ስለተጻፈ /መዝ.፻፲፡፩/ ጌታ ጠላቶቹ በእግሩ መረገጫ ከኾኑ በኋላ ይነሣል ማለት ነውን? … ከእናንተ መካከል “የጌታችን ወንድሞች እኮ ስማቸው በወንጌል የተጠቀሰ ነው!” የሚለኝ ቢኖር እኔም እንዲህ ብዬ እመልስለታለሁ “ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ሥር ለሚወደው ደቀ መዝሙር (ለዮሐንስ) የሰጣት ስለኾነ እነዚህ ልጆች ልጆቿ እንዳልኾኑ፣ ዮሴፍም ባሏ እንዳልኾነ ግልጽ ነው” /ዮሐ.፲፱፡፳፯/፡፡ እናትና አባትህን አክብር ብሎ ሕግን የሠራ ጌታ እንደምን እመቤታችንን ከልጆቿ አለያይቶ ለዮሐንስ ይሰጣታል ተብሎ ይታሰባል?” /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Tatian’s Diatesaron, pp 60-64/፡፡
ቅድመ ዓለም የነበረ እርሱ ሰው ኹኗልና (ካንቺ ተወልዷልና) የእኛን ሥጋ ነሥቶ የርሱን ሕይወት ሰጥቶ ከርሱ ጋራ አስተካከለን፡፡ በቸርነቱ ብዛት እንድንመስለው አደረገን /ፊል.፫፡፲-፲፩/፡፡ ከብዙ ሴቶች አንቺ ትበልጫለሽ፡፡ ክብር የክብር ክብር ካላቸው ከብዙ ሴቶች አንቺ ትበልጫለሽ /ሉቃ.፩፡፳፰/፡፡ ንጉሥ በከተማው እንዲኖር ዘጠኝ ወር ካምስት ቀን ማኅፀንሽን ዓለም አንድርጎ ኖሮብሽልና አምላክን የወለድሽ ድንግል ማርያም ሆይ! ልዑል እግዚአብሔር የከተመብሽ ረቂቅ ከተማ ነሽ፡፡ በኪሩቤል በሱራፌል አድሮ የሚኖረው እርሱን በማኽል እጅሽ ይዘሽዋልና ልዑል እግዚአብሔር የከተመብሽ ረቂቅ ከተማ ነሽ፡፡ በቸርነቱ ብዛት ፍጥረቱን ኹሉ በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግበው እርሱ ጡትሽን ይዞ ጠባ፡፡ አንድም ለሰውን (ለመንፈሳውያን) ኹሉ ሥጋውን ደሙን ሰጥቶ የሚመግበው እርሱ ጡትሽን ይዞ ጠባ፡፡ ይኸውም ፈጣሪያችን መድኃኒታችን ነው፡፡ እንሰግድለት እናመስግነውም ዘንድ በሐዲስ ተፈጥሮ በጥንተ ተፈጥሮ ፈጥሮናልና ለዘለዓለሙ ይጠብቀናል /ዮሐ.፮፡፴፯/፡፡ ሰጊድ (አምልኮ) ከሚገባው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
@Ethiopian_Orthodox
፬. ድንግል ማርያም ዕፍረተ ምዑዝ (መዓዛው የጣፈጠ) የተባለ ጌታችንን የወለደች ሙዳየ ዕፍረት (የሽቱ መኖርያ) /፩ኛ ሳሙ.፲፡፩ አንድምታው/፤ ዳግመኛም የማየ ሕይወት (የሕይወት ውኃ የክርስቶስ) ምንጭ ናት /መኃ. ፬፡፲፪ አንድምታው/፡፡ የማኅፀኗ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ኹሉ አድኗልና፡፡ ከእኛ መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን አጠፋልን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ኹሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና” እንዲል /ቈላ.፩፡፲፱-፳/ በመካከል ኾኖ በመስቀሉ አስታረቀን፡፡ ልዩ በኾነ ትንሣኤውም ሰውን ዳግመኛ ወደ ገነት መለሰው፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ልዩ በኾነ ትንሣኤ ሲል ምን ማለቱ ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ከእነ አልዓዛር ትንሣኤ የተለየ መኾኑን ለማሳየት ነው፡፡ ምክንያቱም፡-
፩ኛ) እነ አልዓዛር አስነሺ ይሻሉ፤ እርሱ ግን “ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ” ብሎ እንደተናገረ /ዮሐ.፲፡፲፰/ የተነሣው በገዛ ሥልጣኑ ነውና፡፡ በተለያየ ሥፍራ “አብ አንሥኦ (አብ አስነሣው)፤ መንፈስ ቅዱስ አንሥኦ (መንፈስ ቅዱስ አስነሣው)” ቢልም አንድ ነው፡፡ ምክንያቱም ዕሪናቸውን መናገር ነውና፡፡
፪ኛ) የእነ አልዓዛር ትንሣኤ በብሉይ ሥጋ ነው፤ የእርሱ ግን በሐዲስ ሥጋ ነው፡፡
፫ኛ) የእነ አልዓዛር ትንሣኤ ሞትን ያስከትላል፤ የእርሱ ግን ሞትን አያስከትልም፡፡
፬ኛ) የእነ አልዓዛር ትንሣኤ ትንሣኤ ዘጉባኤን ይጠብቃል፤ የእርሱ ግን አይጠብቅምና፡፡
አዳምን ዳግመኛ ወደ ገነት ከመለሰ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፭. አንዳንድ ተረፈ ንስጥሮሳውያን እንደሚሉት ንጽሕት ድንግል ማርያም ላቲ ስብሐትና “ወላዲተ ሰብእ” አይደለችም፤ የታመነች አምላክን የወለደች ናት እንጂ፡፡ የመናፍቃን መዶሻ የተባለው፣ በተለይም የቅድስት ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክነት የካደውን ንስጥሮስን የረታው ቅዱስ ቄርሎስ እሳተ መለኮት አምላክን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኗ የተሸከመች፣ በጀርባዋ ያዘለች፣ በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የፈጠረውን ፍጥረት የሚመግበው አማኑኤልን የድንግልና ጡቶቿን ወተት የመገበችውን የወላዲተ አምላክን ክብር ያልተረዱትን ንስጥሮሳውያን መናፍቃንን ሲወቅስ “ወለዛቲ እንተ መጠነዝ ዐባይ ጾረት መለኮተ እፎ ይከልእዋ እምክብራ ለወላዲተ አምላክ ወላዲተ አምላክኬ ቅድስት ድንግል - ይኸንን ያኽል ታላቅ ኾና መለኮትን የተሸከመችቱን የአምላክ እናት ክብርን እንደምን ይነፍጓታል፤ ይከለክሏታል፡፡ የአምላክ እናት ማለት ድንግል ማርያም ናታ” በማለት የተሰጣትን ክብር በማድነቅ አስተምሯል /ተረፈ ቄርሎስ/፡፡
እንዲህም ስለኾነ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የታመነች የምሕረት አማላጅ ናት፡፡ የዚህ ዓለም ሰዎች አማልዱኝ ቢባሉ ነገር አጽንተው ይመለሳሉ፤ እርሷ ግን “ማእምንት ሰአሊተ ምሕረት - የታመነች የምሕረት አማላጅ ናት” /ዮሐ.፪፡፩-፲፩/፡፡ ሰአሊተ ምሕረት ሆይ! ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ከልጅሽ ዘንድ አማልጅን፡፡ ኃጢአታችንን ከሚያስተሠርይልን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
የዓርብ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ
ይህ ዕለት ለምስጋና አምስተኛ ለፍጥረት ስድስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡ ከወትሮ ይልቅም ደናግልን አስከትላ መጥታለች፡፡
@Ethiopian_Orthodox
የዕለተ ሐሙስ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ በድምፅ፡፡
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
ኹሉ ጋር ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት ገባ” ብሏል /ሃይ.አበ.፷፯፡፫-፭/፡፡
ከባሕርያችን መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን የሚያጠፋልንን ጌታን ዘር ምክንያት ሳይኾናት ወለደችው፡፡ ስለዚህ ነገር “ሰውን የምትወድ ሰው የሚወድህ አቤቱ ክብር ላንተ ይገባል” እያልን እናመስግነው፡፡ “ኄር ዘበህላዌሁ ዘልማዱ ኂሩት - በባሕርይው ቸር የኾነ፤ ቸርነትን ማድረግም ልማዱ የኾነ” እያልን እናመስግነው፡፡ ኄር ዘበህላዌሁ ዘልማዱ ኂሩት ከሚባል ልጅሽ ጸንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፫. ዘር ምክንያት ሳይኾናት አምላክን የወለደች ድንግል፣ የማኅፀንዋ ሥራ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? አንድም ለድንግል ለማኅፀኗ ሥራ አንክሮ ይገባል፡፡ ለዮሴፍ የነገረው መልአክ ሳይለወጥ ሰው የኾነ አካላዊ ቃል ከርሷ የሚወለድ በግብረ መንፈስ ቅደስ እንደኾነ መስክሯልና /ማቴ.፩፡፳/፡፡ ማርያም የዚህ ደስታ ዕፅፍ ድርብ የሚኾን ጌታን ወለደችው፡፡ ሴቶች ልጅ ትወልዳላችሁ ሲባሉ ደስ ይላቸዋል፤ ይልቁንም ወንድ ትወልዳላችሁ ሲሏቸው ደስ ይላቸዋል፡፡ እመቤታችን ግን ከዚሁ ኹሉ ያለፈ አምላክን ወልዷለችና ደስታዋ ዕፅፍ ድርብ ኾነላት፡፡ መልአኩ፡- “ልጅ ትወልጃለሽ፤ ስሙም አማኑኤል ይባላል” አላት፡፡ አማኑኤልም ማለት እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ ከኛ ጋራ አንድ ባሕርይ ኾነ ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም ወገኖቹን ከኃጢአታቸው ፍዳ የሚያድናቸው መድኃኒት ይባላል አላት /ማቴ.፩፡፳፩/፡፡ በመኾኑም በክሂሎቱ (በከሃሊነቱ) ያድነን ዘንድ፣ ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ (እስከ ዕለተ ምፅአት ድረስ ክብር ይግባውና) ሰው የኾነ እርሱ አምላክ እንደኾነ በተረዳ ነገር አወቅነው፡፡ አምላክ ብቻ ቢኾን ባልታመመ ነበርና፤ ሰውም ብቻ ቢኾን ባላደነን ነበርና፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ከዚህ ጋር አያይዞ ፡- “ፍቁራን ሆይ! ምንም እንኳን ለዚህ ክብር የተገባን ኾነን ባንገኝም አባታችን በከኀሊነቱ እንዲሁ ከኀጢአታችን አድኖናልና ይህን ክብር፣ ይህን ጸጋ በፍጹም ልናክፋፋው (ልናቆሽሸው) አይገባንም፡፡ ልጅነት እንዲሁ ሳይሰጠን ለምረረ ገሃነም የተገባን የቁጣ ልጆች ከነበርን፤ ይህ ከኅሊናት በላይ የኾነ ጸጋ ከተቀበልን በኋላማ ፍዳችን እንደምን የበዛ አይኾን? ልጆቼ! ይህን የምለው እንዲሁ ለመናገር ያህል አይደለም፡፡ ዳግም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ከተወለዱ በኋላ ብዙ ክርስቲያኖች በኀጢአት፣ በስንፍና፣ ለምግባርና ለትሩፋት ሳይሽቀዳደሙ ታክተው ስለምመለከት ነው እንጂ” ሲል ይመክረናል /St. John Chrysostom, Homily on the Gospel of St. Matthew, Homily IV/፡፡
ወዮ! ንዕድ ክብርት ከምትኾን ከእመቤታችን ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? ቃልን ወሰነችው፡፡ ለልደቱም ዘርዕ ምክንያት አልኾነውም፡፡ በመወለዱም ማኅተመ ድንግልናዋን አልለወጠውም፡፡ ከአብ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ ድካም ሳይሰማው የተወለደ እርሱ ፭ ሺሕ ከአምስት መቶ ዘመን ሲፈጸምም ከድንግል ሕማም ሴቶች የሚሰማቸውን ሕማም ሳይሰማት እርሱን ሕፃናትን የሚሰማቸው ሕማም ሳይሰማው ተወለደ እንጂ፡፡
ሰብአ ሰገል ሰገዱለት፡፡
Ø አምላክ ነውና አምላክ እንደኾነ ለማጠየቅ ዕጣን አመጡለት፡፡ ንጉሥ ነውና ንጉሥ እንደ ኾነ ለማጠየቅ ወርቅ አመጡለት፡፡ ማኀየዊ የሚኾን የሞቱ ምሳሌ ከርቤንም አመጡለት፡፡
Ø አንድም “ይኸን ወርቅ እንገብርላቸው የነበሩ ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኀላፍያን ናቸው፤ አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ነህ” ሲሉ ወርቅ አመጡለት፡፡ “ይኽን ዕጣን እናጥናቸው የነበሩ ጣዖታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኃላፊያን ናቸው፤ አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ነህ” ሲሉ ዕጣን አመጡለት፡፡ “ምንም ቀድሞ ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ብትኾን በሰውነትህ መራራ ሞትን ትቀምሳለህ” ሲሉ ከርቤ አመጡለት፡፡
Ø አንድም ወርቅ ጽሩይ ነውና “ጽሩየ ባሕርይ ነህ” ሲሉ ወርቅ አመጡለት፡፡ ዕጣን ምዑዝ ነውና “አንተም ምዑዘ ባሕርይ ነህ” ሲሉ ዕጣን አመጡለት፡፡ ዳግመኛም “ከርቤ የተሰበረውን ይጠግናል፤ የተለያየውን አንድ ደርጋል፡፡ አንተም ከማኀበረ መላእክት የተለየ አዳምን አንድ ታደርገዋለህ፤ ጽንዓ ነፍስ ሰጥተህ ታጸናዋለህ” ሲሉ ከርቤ አመጡለት፡፡
Ø አንድም ወርቅ ጽሩይ ነውና “ባንተ ያመኑ ምዕመናን ጽሩያነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው” ሲሉ ወርቅ አመጡለት፡፡ ዕጣን ምዑዝ ነውና “ባንተ ያመኑ ምእመናንም ምዑዛነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው” ሲሉ ዕጣን አመጡለት፡፡ ዳግመኛም በዕለተ ሞቱ ያቀምሱታልና ከርቤ አመጡለት፡፡ ቸርና ሰው ወዳጅ የኾነ አንድ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ቸርና ሰው ወዳጅ ከኾነ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፬. ከአዳም ጎን አንድ ዐፅም መንሣቱ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? “በእምነት ዓይን ከማየት በቀር ይህ ከኅሊናት በላይ የኾነውን ድንቅ ነገር በቋንቋ መናገር አይቻለንም” /St. John Chrysostom, Homily 15 on Genesis/፡፡ ከእርሱ (ከአዳም) ሔዋንን ፈጠረ፡፡ ፍጥረትንም ኹሉ ከአዳምና ከሔዋን ፈጠረ፡፡ እንዲህም አድርጎ የአብ አካላዊ ቃል ለኵነተ ሥጋ (ለሕማም ለሞት) ተሰጠ፡፡ ከልዩ ድንግልም ሰው ኾነና አማኑኤልም ተባለ፡፡ “ኦ ለዝንቱ መንክር ልዑል ላዕለ ኵሉ ሕሊናት ብእሲት ምድራዊት ወለደቶ ለእግዚአብሔር ቃል ዘኮነ ሰብአ… - ከኅሊናት ኹሉ ለራቀ ለዚህ ድንቅ ምሥጢር አንክሮ ይገባል፤ ምድራዊት ሴት ሰው የኾነ እግዚአብሔር ቃልን ወለደችው፡፡ ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው፤ እርሱም እናቱን ፈጠረ፡፡ ከእርሷም እርሱ የፈጠረውን ሥጋ ተዋሐደ” /ሃይ.አበ.፵፯፡፪/፡፡
ስለዚህ ነገር ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ በቅዱሳን ዘንድ ቸር ናትና እርሷን እንለምን፡፡ ለሊቃነ ጳጳሳት አስበ ጵጵስናችን (የጵጵስናችን ዋጋ) ይሰጠናል ብለው ደጅ የሚጠኑትን ወልዳላቸዋለችና ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ ነቢያት አስበ ትንቢታችንን ይሰጠናል ብለው “ይወርዳል፤ ይወለዳል” ብለው ትንቢት የተናገሩለትን ወልዳላቸዋለችና ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ ሐዋርያት አስበ ሰብከታችንን ይሰጠናል ብለው “ውስተ ኵሉ ምድር ወፅአ ነገሮሙ ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ - መምህራነ ሐዲስ ሐዋርያት ለምእመናነ ሐዲስ ወረደ ተወለደ ብለው አስተማሩ” እንዲል /መዝ.፲፰፡፬/ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ዙረው ወረደ ተወለደ ብለው ያስተማሩለትን ወልዳላቸዋለችና ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ ሰማዕታ ከዓላውያን ነገሥታት፣ ከዓላውያን መኳንንት ገብተው አስበ ትዕግሥታችንን ይሰጠናል ብለው መከራውን ታግሠው የተቀበሉለትን፣ ምዕመናን አስበ ተጋድሏቸውን ይሰጠናል ብለው ከፍትወታት ከእኩያት ኃጣውእ የተዋጉለት ኢየሱስ ክርስቶስን ወልዳቸዋችና ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ ሰው ኹኖ አድኖናልና በጥበቡ እየሰፈረ የሚሰጠው፣ ዳግመኛም የጸጋው ብዛት የማይታወቅ የቸርቱን ብዛት መርምረን እንወቅ፡፡ ሰው ኹኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እዳይነሣን ለምኚልን፡፡
የሐሙስ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ
ይህ ዕለት ለምስጋና አራተኛ ለፍጥረት አምስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡ ከወትሮ ይልቅም ነቢያትንና ሐዋርያትን አስከትላ መጥታለች፡፡
@Ethiopian_Orthodox
ሰው ማይኾነው ሰው ኾኗልና ይህን ድንቅ ምሥጢር ኑ እዩ፡፡ ቃል ከሥጋ ጋር ቢዋሐድ ጥንት የሌለው መለኮት ፭ ሺሕ ከ፭፻ ዘመን ሲፈጸም ዘመን ተቀድሞት ወደ ኋላ ተገኘ፡፡ ቅድምና የሌለውም ሥጋ ቀዳማዊ አምላክ ተባለ፡፡ አንድም ጥንት (ቅድምና) የሌለው ሥጋ ቀዳማዊ አምላክ ተባለ፡፡ ዘመን የማይቆጠርለትም መለኮት ፲፪ ዓመት ኾነው /ሉቃ.፪፡፵፪/፤ ፴ ዓመት ሞላው ተብሎ ዘመን ተቆጠረለት /ሉቃ.፫፡፳፫/፡፡ አንድም አካላዊ ቃል በጎላ በተረዳ ሰው ኹኗልና በኵር ያልነበረ መለኮት በኵር ተባለ /ማቴ.፩፡፳፭/፡፡ ክብር የሌለውም ሥጋ ክቡር አምላክ ተባለ፡፡ በገዥነት የማይታወቅ ሥጋ በገዥነት ታወቀ፤ በተገዢ ሥጋ ታይቶ የማይታወቅ መለኮትም በተገዢ ሥጋ ታየ፡፡ ቅድመ ዓለም የነበረው፣ በማዕከለ ዓለም ያለው፣ መቼም መች የሚኖረው ኢየሱስ ከርስቶስ እንሰግድለትና እናመሰግነው ዘንድ ከአብ ከባሐርይ አባቱ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ ጋራ አንድ ባሕርይ ነው፡፡ ከአብ ከባሕርይ አባቱ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ ጋራ አንድ ባሕርይ ከሚኾን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንደይነሣን ለምኚልን፡፡
፯. ነቢዩ ሕዝቅኤል የእርሷን ነገር “በድንቅ ቁልፍ የተቈለፈች ደጅ በምሥራቅ አየሁ” ብሎ ተናገረ /ሕዝ.፵፬፡፩-፪/፡፡ ከእግዚኣ ኃያላን በቀር ሳይከፍታት ገብቶ ሳይከፍታት የወጣ የለም፡፡ እግዚአ ኃያላን እሱ ሳይከፍታት ገብቶ ሳይከፍታት ወጣ እንጂ፡፡ እግዚአ ኃያላን ከሚባለው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን አንዳነሣን ለምኚልን፡፡
፰. ኆኀትም (ድጅም) የተባለች መድኃኒታችንን ጌታን የወለደችልን ድንግል ናት፡፡ እሱን ከወለደችው በኋላ እንደ ቀድሞ ማኅተመ ደንግልናዋ ሳይለወጥ ኑራለቸና፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግም፡- “… አንተ መናገር የተሰጣቸውን ሠረገሎች ድምፅ የሰማህ ባለ ሞገስ ሆይ (ሕዝ.፫፡፲፫)! እንደዚሁም የክንፎቻቸውን ድምፅና የዚያን ሠረገላ ታላቅ እንቅስቃሴ የሰማህ ሆይ (ሕዝ.፲፡፭)! አንተ የኪሩቤልን መልክ መለወጥ ያየህ የበራልህ ነፍስ ሆይ! እንዲሁም እኒያ የእሳት ላንቃዎች በከፍታ ላይ የተቀመጠውን ሲያመሰግኑ የሰማህ ሕዝቅኤል ሆይ (ሕዝ.፩፡፬-፳፰) ና! አንተ የቡዝ ልጅ ሆይ (ሕዝ.፩፡፳፫) ና! የተጠቀለለውን የትንቢትህን ቃል ብራና አምጣልን፡፡ አንተ ቁምና እውነትን ተናገር፤ ሌሎቻችን ኹሉ ዝም እንበል፡፡ ካየኻቸው ራዕዮች መካከል ድንግል ማርያም ታይታህ እንደኾነ፤ ፍጥረት ኹሉ ውበቷን ያይ ዘንድ መልኳን ግለጥልን፡፡ በትንቢትህ ውስጥ የጌታህን እናት የሚመለከት አንዳች ነገር ካለ ይህ ለሚሰሙት እጅግ ውድ ስለኾነ ተነሣና አብራራልን፡፡ ይህም ያም (መናፍቅ) ከመውለዷ በኋላ ድንግል አልነበረችም በማለት ይናገራልና እውነት ድንግልናዋን አጥታ እንደኾነ እስኪ አንተ አስረዳን፡፡ ሕዝቅኤል ሆይ! ዛሬ የአንተ ተራ ነውና እስኪ ተናገር፡፡ ስለ እመቤታችን ማርያም ተናገርና ከንቱ ምርምሮችን ግታልን፡፡ እስከ አሁን በትንቢት ተነግሮ የነበረው ምን እንደነበር እንስማ፡፡ የማትመረመር ስለኾነችው ስለ ድንቅ እናታችን ይህ ነቢይ በትንቢቱ ውስጥ እንዲህ ተናግሮ ነበር፡- ‘ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም። ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል።’ አንተ የመንፈስ ነቢይ ሆይ! ይህ ቃል ምን ማለት እንደኾነ እስኪ ገልጠህ አብራራልን፡፡ በትንቢት የተነገረው የተዘጋው በር ድንግል ማርያም ናት፡፡ ምክንያቱም መሲሑ ጌታ በእርሱ በኵል ወደ ዓለም መጥቶ ዝግ አድርጎ ትቶታልና፡፡ ጌታ በዚህ በር ሲገባ እንዳልከፈተው ዕብራዊ የኾነ ሕዝቅኤል ከእኛ ጋር አብሮ ይህንኑ ይመሰክራል፡፡ እግዚአብሔር እንደወደደው በመውለድ በር ወደ ዓለም ገባ፡፡ ያንንም በር በድንግልና ዘጋው፡፡ ነቢዩ በሩ ተዘግቶ ያየው ያ ቤተ መቅደስ ስለ ድንግልናና ስለማይለወጥ ድንግልናዋ የሚያሳየን ነው፡፡ ቅዱሱ መሲሑ (ክርስቶስ) ሲኾን ቤተ መቅደሱም ማርያም ናት፡፡ የተዘጋውም በር በእርሷ የሚኖረውና ተፈትሖ የሌለበት የድንግልዋ ማኅተም ነው” ብሏል /Jacob of Serug, Homily on the Perpetual Virginity of Mary, pp VII-X/፡፡
የማኅፀንሽ ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የሚያድል ነው፡፡ ለሰው ከማያዝን ከማይራራ፤ አንድም ለእርሱ ከሥላሴ ዘንድ ምሕረት ከሌለው፤ አንድም ኃጢአቱን ሸልጎ ከማይሠራ ከዲያብሎስ እጅ ያዳነን ጌታችንን የወለድሽው ሆይ! በደንግሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ፍጽምት ነሽ፡፡ መርገም ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለብሽ /ኢሳ.፩፡፱/ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እያማለድሽ የምታሰጭ ነሽ፡፡ ጌትነቱ እንደ ነገሥታት በጉልበት፣ እንደ ካህናት በሀብት፣ እንደ ጣዖታትም በሐሰት ባይደለ በክብር ባለቤት ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሸልና በዚህ ዓለም ከሚኖሩ ሰዎች ኹሉ ይልቅ ክብር ላንቺ ይገባል፡፡ አካላዊ ቃል መጥቶ ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡ ሰው ሰውኛውንም ኖረ፡፡ መሐሪ፣ ይቅር ባይ፣ ሰው የሚወደው ሰው ወዳጅ ነውና በልዩ አመጣጡ መጥቶ አዳነን፡፡ “አኮ በተንባል ወአኮ በመልአክ አላ ለሊሁ እግዚእ መጸእ ወያድኅነነ - በአማላጅ አይደለም፤ በመልአክም አይደለም፡፡ እርሱ ራሱ፣ በራሱ ደም፣ በራሱ ሊቀ ካህንነት መጥቶ ያድናቸዋል እንጂ ” /ኢሳ.፷፫፡፱/ እንዲል እንደ ቀደመው በረድኤት ሳይኾን በኩነት (ሰው ኹኖ) መጥቶ አዳነን፡፡ አንድም አምስት ሺሕ ካምሰት መቶ ዘመን ሲፈጸም አንድ ሰዓት ስንኳ ሳያሳልፍ በጽኑ ቀጠሮው መጥሮ አዳነን፡፡ በጽኑ ቀጠሮ መጥቶ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
አነሣሥቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን፡፡
ለማጋራት👉 /channel/Ethiopian_Orthodox/3492
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
፩. ኵሉ ሠራዊተ ሰማያት ይብሉ ብፅዕት አንቲ ሰማይ ዳግሚት ዲበ ምድር - ከምድር በላይ ያለሽ ኹለተኛ ሰማይ ሆይ! በሦስቱ ሰማያት (በኢዮር፣ በራማ፣ በኤረር) ያሉ መላእክት ንዕድ ነሽ፤ ክብርት ነሽ ይላሉ፡፡ ማርያም የምሥራቅ ደጅ ናት፤ ከእርሷ የጽድቅ ፀሐይ ክርስቶስ ተገኝቷልና፡፡ ማርያም ሙሽራዋ ንጹሕ የሚኾን ንጽሕት የሠርግ ቤት ናት፡፡ በሠርግ ቤት የመርዓዊና የመርዓት (የሙሽራና የሙሽሪት) ተዋሕዶ ይደረግበታል፡፡ በእመቤታችንም እንደ መርዓዊና እንደ መርዓት ተዋሕዶ፤ ትስብእትና መለኮት አንድ ኹነዋልና፡፡ በሠርግ አዝማደ መርዓዊና አዝማደ መርዓት አንድ እንዲኾኑባት በእመቤታችንም ምክንያት ሰውና መላእክት፣ ሰውና እግዚአብሔር፣ ነፍስና ሥጋ፣ ሕዝብና አሕዛብ አንድ ኹነዋልና እመቤታችን ንጽሕት የሠርግ ቤት ናት /ኤፌ.፪፡፲፭/፡፡ አባ ሕርያቆስ “አስተንፈሰ ወአጼነወ ወኢረከበ ዘከማኪ፤ ወሠምረ መዓዛ ዚኣኪ ወአፍቀረ ሥነኪ ወፈነወ ኀቤኪ ወልዶ ዘያፈቅር” እንዲል /ቅዳ.ማር.ቁ.፳፬/ አብ ከሰማይ ኾኖ አየ፤ ነገር ግን እንዳንች ያለ ባያገኝ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን ልጁን ሰዶ ካንቺ ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡ ተቀዳሚ ተከታይ ከሌለው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት (ክብርት) በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
እዚህ ጋር አንዳንድ ወገኖች የሚያነሡትን ጥያቄ መልሰን እንለፍ፡፡ “ልመናስ ከዚያ በኋላ ስንኳን በሷ (ከበቁ በኋላ) በሌሎችም የለባቸውም፡፡ በቀደመ ልመናዋ የምታስምር ስለ ኾነ እንዲህ አለ እንጂ” ስለተባለ ምሥጢሩን ሳይረዱ “ቅዱሳን በአጸደ ነፍስ አያማልዱም” ለማለት የሚጠቅሱት ወገኖች አሉ፡፡ የዚህ ኃይለ ቃል ትርጓሜ ግን ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የዕብራውያንን መልእክት በተረጐመበት በ፲፫ኛው ድርሳኑ ላይ፡- “ጻድቃን ይረክቡ ኵሎ በአሐቲ ተምኔቶሙ በአሐቲ ስእለት - ጻድቃን አንድ ጊዜ በለመኑት ልመና የሚሹትን ኹሉ ያገኛሉ” እንዳለው /ቁ.፻፶፱/ ቅዱሳኑ በአጸደ ሥጋ ሳሉ እግዚአብሔር አንድ ጊዜ “በስምሽ/ህ ለታረዙ ያለበሰ፣ ሕሙማንን የጐበኘ፣ ዝክርሽ/ህን የዘከረ…” እያለ በገባላቸው ቃል ኪዳን መሠረት በስማቸው የዘከረ፣ በስማቸው ሕሙማንን የጐበኘ፣ የመጸወተ እንደሚምርላቸው የሚያስረዳ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር፣ ዓለምን ዳግም በንፍር ውሃ የማያጠፋትና በየዕለቱ ቀስተ ደመናን የምንመለከተው ፡- “ቃል ኪዳኔንም ለእናንተ አቆማለሁ፤ ሥጋ ያለውም ኹሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም፤ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይኾንም” ብሎ /ዘፍ.፱፡፲፩/ ለኖኅ አንድ ጊዜ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት እንጂ ኖኅ በየዕለቱ እንዲህ ስለሚለምን አይደለም፡፡ “አይለምንም” ሲባል ግን ክብሩን፣ ልዕልናውን፣ መንፈሳዊ ብቃቱን የሚያስረዳ እንጂ ማማለድ አይችልም ለማለት አይደለም፡፡ እንደውም ይህ ኃይለ ቃል ከማማለድ በላይ የኾነ ክብር እንደተሰጣቸው የሚያመለክት ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ጊዜ ለምኖ በየጊዜው የሚሹትን ማግኘት፤ ዕለት ዕለት እየለመኑ የሚሹትን ከማግኘት በላይ ልዕልናን፣ ክብርን፣ መንፈሳዊ ብቃትን ያሳያልና፡፡ አሁን ቅዱሳንን አማልዱን ስንላቸው አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ደጋግሞ እንደገለጸው ቃል ኪዳናችሁን አሳስቡልን ስንል ነው /ቅዳ.ማር. ቁ.፻፷፬-፻፸፩ ይመልከቱ/፡፡
፪. ንግባእኬ ኀበ ጥንተ ነገር - ወደ ቀደመው ነገር እንመለስ፡፡ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ! አንቺን ብቻሽን ትውልደ ሴም፣ ትውልደ ካም፣ ትውልደ ያፌት (ትውልድ ኹሉ) ያመሰግኑሻል /ሉቃ.፩፡፵፰/፡፡ ፱ ወር ከ፭ ቀን ማኅፀንሽን ዓለም አድርጐ የኖረብሽ ሀገረ እግዚአብሔር፣ መንግሥተ ሰማያት ሆይ! ነቢያት ላንቺ “ኢይትዐፀዉ አናቅጽኪ (በሮችሽ ኹል ጊዜ ይከፈታሉ - ንስሐ የሚገቡ ኃጥአንን ለመቀበል)፤ ወኢይጸልም ወርኅኪ (ጨረቃሽ አይቋረጥም)፤ ወኢየዐርብ ፀሐይኪ (ፀሐይሽ ከዚያ በኋላ አትጠልቅም - ፈጣሪሽ አያልፍም)፤ እስመ እግዚአብሔር ብርሃንኪ ለዓለም (ለዘለዓለም ብርሃንሽ እግዚአብሔር ነውና)” /ኢሳ.፷፡፲፩፣፳/፤ “ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር - የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ! ስላንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ (ልዩ) ነው” /መዝ.፹፮፡፫/ እያሉ ድንቅ ድንቅ ነገርን ተናገሩልሽ፡፡ በርግጥም ሰማይና ምድር የማይችሉትን አምላክ የአንቺን ማኅፀን ከተማ አድርጎ ፱ ወር ከ፭ ቀን መኖሩ፤ ያለ ዘር ያለ ሩካቤ አካላዊ ቃልን መፀነስሽ፤ በኅቱም ድንግልና መወለዱ፤ የድንግልና ጡቶችሽን ማጥባትሽ ድንቅ ነው፡፡
ደስ ብሏቸው የሚኖሩ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የመላእክት ማደሪያ ኹነሻልና የምድር ነገሥታት ይህን ዜናሽን ሰምተው፣ ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን ምረረ ገሃነምን ዐውቀው መንነው ይሄዳሉ፡፡ እነርሱ ብቻ አይደሉም፤ ሠራዊቶቻቸውም ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን ምረረ ገሃነምን ዐውቀው መንነው ይሄዳሉ፡፡ አንድም ብርሃን ልጅሽን አምነው ጸንተው ይኖራሉ፡፡ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን ሆይ! አንቺን ብቻሽን ትውልደ ሴም፣ ትውልደ ካም፣ ትውልደ ያፌት ያመሰግኑሻል /ሉቃ.፩፡፵፰/፤ ካንቺ ለተወለደውም ይሰግዱለታል፤ “ዐቢይ እግዚአብሔር - እግዚአብሔር ታላቅ ነው” እያሉም ያከብሩታል፤ ያገኑታልም፡፡ “ዐቢይ እግዚአብሔር” እያሉ ከሚያከብሩት ከሚያገኑት ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፫. “እንተ በአማን ንጹሕ ዝናም” የተባለ፣ የነፍሳትን ጥም ያበረደ የሕይወት ዝናም፣ የሕይወት ጠል፣ የሕይወት ውሃ ክርስቶስን ቋጥረሽ (በድንግልና ፀንሰሽ፣ በድንግልና ወልደሽ) የታየሽልን እውነተኛ ደመና አንቺ ነሽ፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫም፡- “ንዑ እንከ ከመ ናልዕላ ለዛቲ ደመና ብርሃን እንተ ጾረቶ ለማየ ዝናም ንጹሕ- ንጹሑን የዝናም ውሃ የተሸከመችውን የብርሃን ደመና ኑ ከፍ ከፍ እናድርጋት” ብሎ ጋብዞናል /አርጋኖን ዘሠሉስ ፮፡፪/፡፡ ስትወልጂው ማኅተመ ድንግልናሽ አለመለወጡ፤ አካላዊ ቃል ሰው ሲኾን አምላክነቱ ላለመለወጡ፣ ድንግል ወእም (ድንግልም እናትም) ስትባዪ መኖርሽም ልጅሽ አምላክ ወሰብእ (ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው) ሲባል ለመኖሩ ምሳሌ ነውና አብ የልጁ ምልክት አደረገሽ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ቢያድርብሽ፣ ኀይለ ልዑል ወልድም ሥጋሽን ቢለብስ፤ አንድም መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ ግብራት (ማለትም ከሩካቤ፣ ከዘር፣ ድንግልናን ከመለወጥ) ቢከለክልሽ፣ ኀይለ ልዑል ወልድም ከሦስቱ ግብራት ቢከልልሽ ለዘላለሙ የሚኖር አካላዊ ቃልን ወለድሽልን /ሃይ.አበ.፻፲፡፳፱/፡፡ እርሱም ሰው ኾኖ ከኃጢአት አንድም ከኃጢአታችን ፍዳ አዳነን፡፡
የዕለተ ሰኞ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ በድምፅ፡፡
ለሌሎች ያካፍሉ 👉 /channel/Ethiopian_Orthodox/3491
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
፬. ነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት በሚገልጽ መንፈስ ቅዱስ የአማኑኤልን ምሥጢር አየና አሰምቶ ተናገረ፡፡ አማኑኤል ማለት ሰው የኾነ አምላክ ማለት ነውና “ሕፃን ተወለደልን፤ ወልድ ለሕማም ለሞት ተሰጠልን፡፡ አንድም ወልድ ለኩነተ ሥጋ ተሰጠልን ፤ ሕጻንም ኾኖ ተወለደልን” ብሎም ጮኸ /ኢሳ.፱፡፮/፡፡ አትናቴዎስ ሐዋርያዊም “ስለ ድኅነተ ሰብእ የአዳምን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ፤ ካሣ ይከፍልልን ዘንድ ቃል ሥጋ ኾነ” ይላል /Ep. 61:3./፡፡ ወልድ ዘበላዕሉ ሕፃን ዘበታሕቱ ከሚባል ልጅሽ እመቤታችን ጽንዕት በድንግልና ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፭. ባሕርየ ዕጓለ እመሕያው (ሰው) ሆይ! እግዚአብሔር ሰውን ወዶታልና በውሰጥ በአፍአ፣ በነፍስ በሥጋ ደስ ይበልህ፡፡ “ወዶ ምን አደረገለት?” ትለኝ እንደኾነም “በእርሱ የሚያምን ኹሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” ተብሎ እንደተጻፈ /ዮሐ.፫፡፲፮/ ልጁን ለሕማም ለሞት እስከ መስጠት ደርሶ ለቤዛ ሰጥቶለታል ብዬ እመልስልሃለሁ፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ረቂቅ ክንዱን ሰደደልን /ኢሳ.፶፩፡፱፣ ፶፫፡፩/፡፡ ነገር ግን ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ የዕብራውያንን መልእክት በተረጐመበተ በ፫ኛው ድርሳኑ “ወልድ ዋሕድ እንደ መላእክት በተላከ ጊዜ ቦታውን የለቀቀ አይደለም፤ በአንድ ፈቃድ ከአባቱ ጋር እያለ ነው እንጂ” ብሎ እንደተናገረው በለቢሠ ሥጋ ነው እንጂ በመለኮት የተላከ አይደለም፡፡ ክንድ ከአካል ሳይለይ የወደቀውን ዕቃ አንሥተው ይመልሱበታል፤ የራቀውንም ያቀርቡበታል፡፡ የአብ ኃይል፣ ክንድ የሚባለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የወደቀውን አዳምን ያዳነው ከባሕርይ አባቱ፣ ከአባቱ አንድነት ሳይለይ ነው፡፡
እዱ መዝራዕቱ ከሚባለው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡
፮. ሊቁ ምስጋናውን ሲቀጥል “እምቅድመ ዓለም የነበረው፣ ዓለምን አሳልፎ የሚኖረው፣ ለኩነት ሥጋ የመጣው፣ ዳግመኛም ዓለሙን ለማሳለፍ የሚመጣው አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርሰቶስ ካንቺ ሳይለወጥ ፍጹም ሰው ኾነ” ይላል፡፡ ይኸውም በሌላ አንቀጽ “ባሕርዩን ከፍሎ አልተዋሐደም፤ ባሕርዩንም ሕፁፅ በማድረግ ኹለተኛ እንስሳ አልኾነም፡፡ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመኾን ምሉ ፍጹም ሰው ነው እንጂ፡፡ የአምላክነትን የሰውነትንም ሥራ ይሠራል፤ ይህስ ባይኾን አንዱ ተለይቶ በቀረ ነበር” ካለው ጋር ተመሳሳይ ነው /ዮሐ.፩፡፩-፲፬፣ ሃይ.አበ.ዘኤፍሬም ፵፯፡፴፪/፡፡
“ተቀዳሙ ተካታይ የሌለው ወልድ ዋሕድ በሥራው ኹሉ ከነሣው ሥጋ አልተለየም፡፡” ይህም በኹለት መልኩ ይተረጐማል፡-
፩ኛ፡- “አካላዊ ቃል አንድ ግብር፣ አንድ ባሕርይ፣ አንድ አካል ነው እንጂ” ማለት ሲኾን፤
፪ኛ፡- ደግሞ “ተቀዳሙ ተካታይ የሌለው ወልድ ዋሕድ ሰውም ቢኾን ከአብ ከባሕርይ አባቱ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ አልተለየም፡፡ አካላዊ ቃል አንድ ኅብረ መልክዕ፣ አንድ ባሕርይ፣ አንድ አገዛዝ ነው እንጂ” ማለት ነው፡፡
ሰውም ቢኾን ከአብ ከባሕርይ አባቱ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ ካልተለየ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳነሣን ለምኝል፡፡
፯. ዳግማይ አዳም (ክርስቶስ) ካንቺ ባንቺ ባሕርይ ተወልዷልና የነቢያት ሀገረ ትንቢታቸው ቤተ ኀብስት እመቤታችን ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ የቀደመ ሰው አዳምን ከሲዖል ወደ ገነት ከኀሣር ወደ ክብር ይመልሰው ዘንድ ካንቺ ባንቺ ባሕርይ ተወልዷልና የነቢያት ሀገረ ትንቢታቸው ቤተ ኀብስት እመቤታችን ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ሊቁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዳግማይ አዳም ማለቱ ከቀዳማዊ አዳም ጋር የሚያመሳስለው ምን ስላለው ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- በቀዳማዊ አዳም ምክንያት የሰው ልጅ በሙሉ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ተፈርዶበት ነበር፤ በዳግማይ አዳም በክርስቶስ ግን የጽድቅ በር ለኹሉም ተከፍቷል፡፡ ከቀዳማዊ አዳም ጋር አብረው ዕፀ በለስን ያልበሉት ስንኳ ሞት ነግሦባቸው ይኖር ነበር፤ በዳግማይ አዳም በክርስቶስ ትሩፋት ግን የሰው ልጅ በሙሉ የድኅነት መንገድ ተሰጥቶታል፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ዳግማይ አዳም ሲባል በአዳም የመጣው በደል ክርስቶስ ከሰጠው ጸጋ ጋር ወይም ደግሞ በአዳም ምክንያት የመጣው ሞትና በክርስቶስ የተሰጠው ሕይወት ለማስተካከል ሳይኾን አዳም ለሚሞቱት ኹሉ አባት እንደኾነ ኹሉ ክርስቶስ ደግሞ ትንሣኤ ሕይወት ላላቸው ኹሉ አባታቸው መኾኑን ለመግለጥ ነው /St. John Chrysostom on Romans, Hom.10/፡፡ አንድም በጥንተ ተፈጥሮ ይመስሏልና፡፡
በዕፅ ምክንያት የወደቀ (ከገነት የወጣ፣ ከክብሩ የተዋረደ) አዳም ንስሐ ቢገባም፣ ጩኸቱን ሰምተው ነቢያት ካህናት ቢነሡም እንደ እርሱ ንጽሐ ጠባይዕ አድፎባቸዋልና በግዝረታቸው በመሥዋዕታቸው አዳምን ማዳን አልቻሉም /ኢሳ.፷፬፡፮/፡፡ ነገር ግን “አንሥእ ኃይለከ፤ ፈኑ እዴከ” /ኢሳ.፶፩፡፱/ ያሉትን ልመናቸውን ሰምቶ ካንቺ ባንቺ ባሕርይ ተወለደ (ሰው ኾነ)፡፡ የአዳምን ባሕርይ ባሕርይ አድርጐ “አዳም ጥንቱንም መሬት ነህ ወደ መሬትነትህ ተመለስ” ብሎ በአዳም የፈረደበትንም የሞት ፍርድ (መከራ) ተቀብሎ ያድነው ዘንድ ካንቺ ባንቺ ባሕርይ ተወልዷልና፣ የነቢያት ሀገረ ትንቢታቸው ቤተ ኀብስት እመቤታችን ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ ብዙ ኃጢአት ካለች ዘንድ ጸጋ እግዚአብሔር ትበዛለች /ሮሜ.፭፡፳/፡፡ “በአንድ ሰው (አዳም) ምክንያት የገባች ኃጢአት ሕግ በተሰጣቸውና ባልተሰጣቸው ኹሉ እንዲህ ከነገሠች፣ በዳግማይ አዳም በአካላዊ ቃል በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠች ጸጋማ እንዴት አብልጣ አትበዛ?” /St. John Chrysostom, Ibid/፡፡ ዳግማይ አዳም ከሚባል ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳነሣን ለምኚልን፡፡
ሊቁ (ቅዱስ ኤፍሬም) በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፱ ያለውን ኃይለ ቃል ሲተረጕምም እንዲህ ይላል፡- “ቸር ወዳጅ የኾነው እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን ወዲያው እንደተሳሳቱ ፍርዱን አላስተላለፈባቸውም፤ ታገሣቸው እንጂ፡፡ ይኸውም ምኅረት ቸርነቱን ይለምኑት ዘንድ ነው፡፡ እነርሱ ግን አልለመኑትም፡፡ እግዚአብሔርም ምንም ሳይናገራቸው በገነት ውስጥ በእግር እንደሚመላለስ ሰው ኾኖ በድምፅ ብቻ መጥራቱን ቀጠለ፡፡ አዳምና ሔዋን ግን አሁንም አልመለስ አሉ፡፡ በመጨረሻም አምላክ ድምፁን ማሰማት ጀመር፡፡ ‘አዳምን ወዴት ነህ?’ ይላቸው ጀመር፡፡ አስቀድሞ በእግር እንደሚመላለስ ሰው ኾኖ በድምፅ ብቻ መጥራቱ መንገድ ጠራጊው ዮሐንስን እንደሚልክላቸው፣ ቀጥሎ ድምፅ አሰምቶ ወዴት ነህ ብሎ መፈለጉም ወልደ እግዚአብሔር ራሱ በተዋሕዶ ፍጹም ሰው ኾኖ ሊያድናቸው እንደ ፈቀደ ያጠይቃል” ይላል /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Genesis/፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ኦሪት ዘልደትን በተረጐመበት በ፲፯ኛው ድርሳኑ ላይ፡- “በዚህ ንግግሩ የእግዚአብሔር ከአእምሮ የሚያልፈውን ፍቅሩን እንመለከታለን፡፡ አንድ አባት ልጁ የማይረባውን ነገር በማድረግ ከክብሩ ቢዋረድም አባቱ እጅግ እንዲወደውና ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ እንዲደክም፤ እግዚአብሔርም ከሰው ልጆች ጋር ይህን የመሰለ ፍቅር ሲያሳይ እናስተውላለን፡፡ አንድ ሐኪም ወደ ታማሚው አልጋ ጠጋ ብሎ በሽተኛውን እንዲጠይቀውና አስፈላጊውን ኹሉ እንደሚያደርግለት፣ ሰው ወዳጁ እግዚአብሔርም ወደ አዳም ጠጋ ብሎ ሲያነጋግረው እንመለከታለን” ይላል፡፡
ዳግመኛም በሌላ አንቀጽ “አዳም ሆይ ወዴት ነህ” ማለቱ፣ ለአቅርቦት መኾኑን ሲገልጥ፡- “አዳም ሆይ! ምን ኾንክብኝ? በመልካም ቦታ አስቀምጬህ ነበር፤ አሁን ግን ቦታህ ተለወጠብኝ፡፡ ብርሃን ተጐናጽፈህ ነበር፤ አሁን ግን ጨለማ ውስጥ አይሃለሁ፡፡ ልጄ! ወዴት ነህ? ይህ ኹሉ እንደምን ደረሰብህ? በአንተ ውስጥ ያኖርኩት መልኬ ማን አበላሸብኝ? በዚህ ያህል ፍጥነት የጸጋ ልብስህን ገፎ የጽልመት ልብስ ያከናነበህ ማን ነው? ውዴ! ባለጸጋ አድርጌ ፈጥሬህ አልነበረምን? ታድያ አሁን ድኽነት ውስጥ የከተተህ ማን ነው? ያን የግርማ ልብስህን ሰርቆ ዕራቆትህ ትኾን ዘንድ ያደረገህ ማን ነው? እኮ የጸጋ ልብስህን እንድታጣ ያደረገህ ማን ነው? ይህን የመሰለ ቅጽበታዊ መለወጥ ከወዴት መጣብህ? የከበረ ዕንቁህን እንድትጥል ያደረገህ ምን ቢገጥምህ ነው? አክብሮ በተወደደ ቦታ ካስቀመጠህና ኹል ጊዜ በስስት ዐይን ሲያነጋግርህ ከነበረው አምላክህ ተደብቀህ እንድትሸሸግ ያደረገህ ምንድነው? ማንም የወቀሰህ ሳይኖር፣ እንዲህ እንዲህ አድርገህ በድለሃል ብሎ የመሰከረብህ ሳይኖር ይህን ያህል በፍርሐት መናጥ ከወዴት አገኘህ?” ይላል /Daily Readings of St. John Chrysostom/፡፡
ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ሆይ! ፭ ሺሕ ከ፭፻ ዘመን በግብርናተ ዲያብሎስ የነበረ አዳምን ነፃ ካደረገው ልጅሽ ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡ “ቅድስት” ማለቱ ንጽሕት፣ ጽንዕት፣ ክብርት ልዩ ሲል ነው፡፡ ይኸውም፡-
· ሌሎች ሴቶች ከነቢብ ከገቢር ቢነጹ ከሐልዮ አይነጹም፡፡ እሷ ግን የዕንቆራው ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ቴዎዶጦስ “ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ ድንግል በሕሊናሃ ወድንግል በሥጋሃ- ከፈጠራት ጀምሮ በምንም በምን (በሕሊናዋም በሥጋዋም) ከድንግልናዋ አልተለወጠችም” /ሃይ.አበ.፶፫፡፳፪/ እንዲል ከነቢብ፣ ከገቢር፣ ከሐልዮ ኃጢአት ንጽሕት ናትና፡፡
· ጽንዕትም አለ፡፡ ሌሎች ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው፤ ኋላ ተፈትሖ አለባቸው፡፡ እሷ ግን ቅድመ ፀኒስ ጊዜ ፀኒስ፤ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ጽንዕት (ወትረ ድንግል) ናትና፡፡
· ክብርትም አለ፡፡ ሌሎችን ሴቶች ብናከብቸው ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንትን ወለዱ ብለን ነው፡፡ እሷን ግን ወላዲተ አምላክ ወልዳልናለች ብለን ነውና፡፡
· ልዩም አለ፡፡ እናትነትን ከድንግልና፣ አገልጋይነትን ከእናትነት፣ ወተትን ከድንግልና ጋር አስተባብራ የተገኘች፤ በድንግልናም እያለች ከጡቶቿ ወተት ተገኝተው በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግብ መጋቤ ፍጥረታት አምላክን የወለደች፤ እሳታውያን የሚኾኑ ኪሩቤል ሱራፌልም በፍርሐት በረዐድ ኹነው ዙፋኑን የሚሸከሙት እሳተ መለኮት ጌታን ፱ ወር ከ፭ ቀን በማሕፀኗ የተሸከመች፣ በክንዷ የታቀፈች፣ በዠርባዋ ያዘለች ከእመቤታችን በቀር ሌላ ሴት የለችምና፡፡
እንኳን ለእመቤታችን ጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ!
የእመቤታችንን የፍልሰታ ጾም ስናስብ በቤተ ክርስቲያናችን የሚሰማውን የውዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ እናስተውላለን፡፡
ይህን pdf በማውረድ የእመቤታችንን ውዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ ተጠቀሙበት፡፡
ለሌሎች ለማጋራት ሊንኩን ይላኩ 👉 /channel/Ethiopian_Orthodox/3485
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
በቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመማር ባሻገር ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ብናስቀድስ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ደሙን ብንቀበል በበረከት ላይ በረከትን፤ በጸጋ ላይ ጸጋን እናገኛለን፡፡
በኋላም ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንችላለን፡፡
ነገር ግን በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ በዚህ ወቅትም ኾነ በሌላ ጊዜ ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉ ወጣቶች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም አረጋውያንና ሕፃናት ብቻ ሳይኾኑ ወጣቶችም ጭምር የመቍረብና የመዳን ክርስቲያናዊ መብት እንዳለን በመረዳት ራሳችንን ገዝተን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ይገባናል፡፡ አምላካችን በማይታበል ቃሉ “ሥጋዬን የሚበላ፤ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው” በማለት ተናግሯልና /ዮሐ.፮፥፶፬/፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox