በዚህ Channel ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ ፤ ቀኖና እና ትውፊት የጠበቁ ትምህርቶች ይተላለፉበታል፡፡ ለአስተያየት: ጥቆማና ጥያቄ በዚህ ያግኙን ☞ @Ethiopian_Orthodox_bot Buy ads: https://telega.io/c/Ethiopian_Orthodox
የሰሙነ ሕማማት ዕለታት-ዓርብ
✅የስቅለት ዓርብ
✅መልካሙ ዓርብ
@Ethiopian_Orthodox
🩸 "ተወዳጅ ልጅሽን" 🩸
ተወዳጅ ልጅሽን ህማሙን ስታይ
ማሰብ ይሳነኛል የአንቺን ስቃይ
በእሾህ አክሊል ጉንጉን የቆሰለ ራሱን
በብዙ ግርፋት የታመመ አካሉን(፪)
በዕፅ መስቀሉ የወረደ ደሙ
የቀራንዮ ግፍ እጅግ ማስገረሙ
ደጉ ልጅሽ ታስሮ የፍጥኝ ሲሰቃይ
ተሰክቶ ቀረ ዓይንሽ ወደ ሰማይ(፪)
ስለመሰቀሉ አይሁድ ሲደሰቱ
ሲስቁ ሲያሾፉ ቁማር ሲጫወቱ
ሲዘባበቱበት አይንሽ በማየቱ
ህሊናሽ ተገርፏል በሀዘን በብርቱ(፪)
ብላቴናይቱ የዳዊት ልጅ ማርያም
ስለደረሰብሽ ቢነገር አያልቅም
ተጠማው ቢላቸው መፃፃ አስጎነጩት
መርገም አስወግዶ ቢሰጣቸው ሕይወት(፪)
ለመጠጡ እንዲሆን መፃፃ ከሐሞት
ሰፍነግን ጨምረው በዘንግ አስጎነጩት
ዳዊት በትንቢቱ እንደተነበየው
በምግቤ መራራን ጨመሩ እንዳለው(፪)
ይኄ ሁሉ ሲሆን ድንግል ተመልክታ
መፅናናት ተሳናት በሐዘን ተነክታ
ኤሎሄ ኤሎሄ ጌታ ባለ ጊዜ
እጅግ ኃያል ነበር የማርያም ትካዜ(፪)
በሊቀ መዘምራን ይልማ ኃይሉ
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
የሰሙነ ሕማማት ዕለታት-ሐሙስ
✅ሕጽበተ ሐሙስ
✅ጸሎተ ሐሙስ ይባላል
✅የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ
@Ethiopian_Orthodox
የሰሙነ ሕማማት ዕለታት
ሐሙስ
ከስቅለትና ከትንሣኤ በፊት ያለው ሐሙስ በቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ ስያሜዎች
አሉት፡፡
ሀ. ጸሎተ ሐሙስ ይባላል።
የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ይለምን ይማልድ የነበረን ሥጋን የተዋሐደ ፍጹም አምላክ፤ ፍጹም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ነው፤ (ማቴ 26፤36-46፣ ዮሐ.17)
ለ. ሕጽበተ ሐሙስ ይባላል ።
ሕጽበተ እግር፦ ይህ ስያሜ የተሰጠው ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት ነው፤ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳትና የደብር አስተዳዳሪዎች በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብሕን ኃጢአት እጠብ ሲሉ ከአገልጋዮቹ ጀምረው በቤተክርስቲያን የተገኙትን ምእመናን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ሲያጥቡ ያረፍዳሉ፡፡
ሐ. የምሥጢር ቀን ይባላል ።
ከሰባቱ ምሥጢራት አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷልና፤ ይኸውም ‹‹ይህ ስለእናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ ብሉ›› ጽዋውንም አንሥቶ አመሰገነ ‹‹ይህ ስለእናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ›› በማለት እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ የምንሆንበትን መንገድ ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ቅዳሴ ይቀደሳል፤ የሚቀደሰውም በለሆሳስ ሲሆን እንደ ቃጭል ሆኖ የሚያገለግለውም ጸናጽል ነው፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ ሲመጡ ድምጻቸውን ዝግ አድርገው፣ በለሆሳስ እየተነጋገሩ መምጣታቸውን ለማሰብ ነው፤ በቅዳሴውም ጸሎተ ተአምኖ፣ ኑዛዜ አይደረግም፤ ሥርዓተ ቁርባን ግን ይፈጸምበታል፤ ይህም ጌታችን የሰጠውን ዘለዓለማዊ ቃል-ኪዳን ለማሰብ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ተዘጋጅቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ይኖርበታል፡፡
መ. የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡
ጸሎተ ሐሙስ ( የፋሲካ እራት) ፦ ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጐ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹ይህ ጽዋዕ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱም ጠጡ››በማለቱ ይታወቃል፡፡ (ሉቃ.22፤20) ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊ ቃል-ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት መሆኑን በማሰብ የቃል-ኪዳኑ ፍጻሜዎች፣ ጠባቂዎች መሆን እንደሚገባን እንማራለን፡፡
ሠ. የነጻነት ሐሙስ ይባላል።
ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባርያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ራሱ ጌታችን ስለሰው ልጅ ነፃነት ሲናገር ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፡፡›› በማለቱ(ዮሐ.15፤15) ከባርነት የወጣንበት ቀን መሆኑን መጽሐፍ በግልጥ ያስረዳናል፡፡
ስለዚህ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከኃጢአት ባርነት ተላቅቆ፤ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርበታል፡፡
እርሱ ጠላቶቹ ስንሆን ወዳጆቹ አድርጐናልና፡፡
ረ. አረንጓዴ ሐሙስ አምላካችን የጸለየበትን የአትክልት ቦታ ወይም ጌቴሴማኒ ለማሰብ ይህ ስያሜ ተሰጥቶታል።
ጌታ እንዴት፣ ምን እና ለምን ጸለየ?
እንዴት ጸለየ?
አምላካችን የምሥጢር ሐዋርያቱን (ዮሐንስ ፣ ያዕቆብ እና ጴጥሮስ ) አምስት ትእዛዝን (ተቀመጡ ፣ ትጉ ፣ ጸልዩ ፣ ተኙ ፣ ዕረፉ ) በማዘዝ ግንባሩን ምድር አስነክቶ ሰግዶ ጸለየ።(ማቴ፳፮:፴፮-፵፭)
ምን ጸለየ?
ሦስት ጊዜ ደጋግሞ የጸለየው ጸሎት አንድ ዓይነት ነው ይኸውም:- "አባቴ ቢቻልስ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ ፣ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ።"(ማቴ፳፮:፴፮-፵፭)
ለምን ጸለየ?
፩. ምሣሌ ይሆነን ዘንድ ነው።
፪. ፈቃዱን ማስቀደም እንዳለብን እናውቅ ዘንድ ነው።
፫. ወደፈተና እንዳንገባ መጸለይ እንደሚገባ እናውቅ ዘንድ ነው።
የጸሎቱ ትርጓሜ ምንድን ነው?
፩. ዓለም እንድትድን እና ክብርን እንድታገኝ ለሞት ተላልፎ እንደሚሰጥ ገልጿል።
"ያለ እኔ ሞት የዓለሙ ደኅንነት ያለ እኔ ሐሳር የዓለሙ ክብር አይቻልም እንጂ የሚቻልስ ከሆነ ይህ ጽዋዓ ሞት ይለፍልኝ። ነገር ግን ያንተ ፈቃድ ይደረግ እላለሁ እንጂ የኔ ፈቃድ ይደረግ አልልም።" (ወንጌል አንድምታ ገጽ፪፻፸፱)
፪. ሞት እንዲቀርልን እንደ ሞተ ገልጿል። "በኔ ሞት የዓለም ደኅንነት በኔ ኃሣር የዓለም ክብር የሚቻልስ ከሆነ እኔ ከሞትሁላቸው ከኔ ሞት የተነሳሣ ይህ ጽዋዕ ሞት ይቅርላቸው።(ወንጌል አንድምታ ገጽ፪፻፸፱)
፫. አብነት ይሆነን ዘንድ ሞትን እንደሚቀምስ ገልጿል። " ከኔ ለምዕመናን ይለፍላቸው ። እኔን አብነት አድርገው ይሙቱ ። ነገር ግን የኔ ፈቃድ ካንተ ፈቃድ ልዩ ሁኖ የኔ ፈቃድ ይሁን አልልም። የኔ ፈቃድ ካንተ ፈቃድ ጋራ አንድ ነውና ያንተ ፈቃድ ይሁን እላለሁ እንጂ። " (ወንጌል አንድምታ ገጽ፪፻፸፱)
በዚህ ዕለት በወንጌላት የተመዘገቡ ድርጊቶችን ቀጥለን እንመልከት፡
ሀ. የፋሲካ ዝግጅት የተደረገበት ዕለት ነው ።
ዝግጅቱ በሦስቱ ወንጌላት ላይ ተመዝግቧል፡፡ (ማቴ.26፤17-19፣ ማር 14፤1-16፣ ሉቃ.22፤6-13) ፋሲካ ማለት ማለፍ ማለት ነው፤ ይኸውም እሥራኤላውያን በግብጽ ምድር ሳሉ መልአኩን ልኮ እያንዳንዱ እሥራኤላዊ የበግ ጠቦት እንዲያርድና ደሙን በበሩ ወይንም በመቃኑ እንዲቀባ ለሙሴ ነገረው፤ ሙሴም ለሕዝቡ ነገረ፤ ሁሉም እንደታዘዙት ፈጸሙ፤ መቅሰፍተ ከእግዚአብሔር ታዞ መልአኩ የደም ምልክት የሌለበትን የየግብጻውያን ቤት በሞተ በኵር
ሲመታ፤ የበጉ ደም ምልክት የእሥራኤላውያንን ቤት ምልክቱን እያየ ማለፉን ለማመልከት ነው፡፡ (ዘዳ.12፤1-13) በዚህ መነሻነት በየዓመቱ እሥራኤላውያን በመጀመሪያ ወራቸው በዐሥራ ዐራተኛው ቀን በግ እያረዱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡ ሀገራችንም አስቀድማ ብሉይ ኪዳንን የተቀበለች ሀገር እንደመሆኗ ይህ ድርጊት ይፈጸምባት ነበር፡፡ በአንጻሩም ዛሬ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ፋሲካ ተብሎ የተጠራበት ምክንያት በዚህ በፋሲካ በዓል ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጐ ደሙን ስላፈሰሰልን ነው፡፡ በደሙ መፍሰስ ሞተ በኵር የተባለ ሞተ ነፍስ ቀርቶልናልና፡፡ ‹‹ፋሲካችንም ክርስቶስ ነው፡፡›› (1ኛ
ቆሮ.5፤6፣ 1ኛ.ጴጥ.1፤10)
ለ. በዚህ ዕለት እንደ ማክሰኞ ለደቀመዛሙርቱ ረጅም ትምህርት አስተምሯል።
ምሥጢረ ሥላሴ የሦስትነት ትምህርት፤ ምሥጢረ ሥጋዌ (የአምላክ ሰው መሆን)፤ በዮሐ.14፤16የሚገኘው በጠቅላላ የዚህ ዕለት ትምህርት ነው፡፡ የትምህርቱም ዋና ዋና ክፍሎች ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንና የዳግም ምጽአቱ ነገር ነው፡፡
እነዚህም በስፋትና በጥልቀት መማር እንደሚገባ ሲያስረዳን፤በተአምራት ሊገልጥላቸው ሲችል በረጅም ትምህርት እንዲረዱት አድርጓል፡፡ ተማሪዎቹን እሱ እያስተማራቸው ሳለ ያልገባቸውን እየጠየቁ ተረድተዋል፡፡ከዚህም እያንዳንዳችን በቤተክርስቲያን ተገኝተን መማርና ያልገባንን ጠይቆ መረዳት እንደሚገባን እንማራለን፡፡
ሐ.ይህ ዕለት ከደቀመዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለ ጌታ ሆይ፣ መምህር ሆይ ብሎ በመሳም አሳልፎ የሰጠበት ዕለት ነዉ።
የሰሙነ ሕማማት ዕለታት-ረቡዕ
✅ምክረ አይሁድ
✅የመልካም መዓዛ ቀን
✅ከዳተኛው ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያንና ከካህናት አለቆች ዘንድ ሠላሳ ብር ለመቀበል ተስማምቷል።
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
🩸"ጌታ ሆይ" 🩸
ጌታ ሆይ አይሁድ አማፅያን ሰቀሉህ ወይ
የዓለም መድኃኒት የዓለም ሲሳይ ሰቀሉህ ወይ/2/
የአዳም በደል አደረሰህ አንተን ለመሰቀል
የሄዋን ስህተት አበቃህ ለሞት ቸሩ አባት/2/
ንጹህ ክርስቶስ ሆንክ በደለኛ ብለህ ስለኛ
መስቀል አሸክመው አሥረው ገረፉህ እያዳፉህ/2/
እጅና እግርህ በችንካር ተመታ የዓለም ጌታ
የእሾህ አክሊል ደፍተህ ጎንህን ተወጋህ አልፋ ኦሜጋ/2/
ግብዞች እንደራሳቸው መስሏቸው
ምራቅ እየተፉ በፊትህ ቀለዱ አንተን ሊጎዱ/2/
በመስቀል ላይ ተጠማሁ ስትል ታላቅ በደል
ሃሞትና ከርቤ ሰጡህ ቀላቅለው ጠጣ ብለው/2/
ይቅር ባይ ግልጽ በደላችን ሁሉን ሳታይ
አንተ ይቅር በለን በእኛ ሳትከፋ እንዳንጠፋ/2/
በሊቀ መዘምራን ኪነጥበብ ወ/ቂርቆስ
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
የሰሙነ ሕማማት ዕለታት
ማክሰኞ
በዚህ ዕለት አምላካችን ለጥያቄዎች በሙሉ መልስ የሰጠበት እና በስፋት ያስተማራቸው ትምህርቶች የሚታሰቡበት ዕለት ነው።
፩. የጥያቄ ቀን ትባላለች።
በዚህ ዕለት አምላካችን ስለ ሥልጣኑ በካህናት አለቆችና በሕዝብ አለቆች"በምን ሥልጣንህ እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንንስ ሥልጣን የሰጠህ
ማነው?"(ሉቃ፳:፩-፵፩) የሚል ጥያቄ ለፈተና የተጠየቀበት ዕለት በመሆኑ የጥያቄ ቀን ትባላለች፡፡
ጥያቄዎቹ በቁጥር አምስት ናቸው። እነዚህም:-
፩. ሥልጣኑን የተመለከተ ጥያቄ ቀርቦለታል። (ሉቃ፳:፪) ለክፋት የቀረበ ጥያቄ በመሆኑ ጥያቄውን በጥያቄ መልሶታል።
፪. በወይን አትክልት መስሎ ጥያቄ አቅርቦላቸዋል። (ሉቃ፳:፱)ይህ ምሳሌ በቀጥታ ከእነርሱ ጋር እንደሚገናኝ ተረድተውም ነበር።
፫. ግብርን የተመለከተ ጥያቄ ቀርቦለታል። (ሉቃ፳:፳፪) ይህንንም በድንቅ ጥበቡ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ብሎ መልሶላቸዋል።
፬. ትንሣኤ ሙታንን የተመለከተ ጥያቄ ቀርቦለታል። (ሉቃ፳:፴፫) ከጋብቻ ጋር በተገናኘ ምድራዊ አስተሳሰብ ሰማያዊውን ኑሮ አውርደው ለጠየቁት ለሰዱቃውያን ከሞት በኋላ እንደ መላእክት ያለን ኑሮ የመኖር ዕድል እንዳለው የሰው ልጅ መልሶላቸዋል።
፭. ክርስቶስን የዳዊት ልጅ ለምን ይሉታል የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸዋል።(ሉቃ፳:፵፩)
መልስ ላጡበት ጥያቄ ራሱ በመመለስ እርሱ የዳዊት ጌታ መሆኑን አስተምሯቸዋል።
፪. የትምህርት ቀን ትባላለች።
በዚህ ዕለት ደቀ መዛሙርቱን ሰፊ ትምህርትን ስለ መጨረሻው ዘመን ምልክቶች አስተምሯቸዋልና የትምህርት ቀን ተብላ ትጠራለች። (ሉቃ፳:፵፬-፵፯) ያስተማራቸው ትምህርቶች
፩. የአምልኮ መልክ ካላቸው ተጠንቀቁ
፪. ታይታን ከሚወዱ ተጠንቀቁ
፫. ለራሳቸው ክብርን ከሚሰጡ ተጠንቀቁ
፬. የባልቴቶችን ገንዘብ ከሚበሉ ተጠንቀቁ
፭. በምክንያት ጸሎት ከሚያረዝሙ ተጠንቀቁ
ሌላው በግብረ ሕማማት ካህናት በዚህች ዕለት ስለሚያከናውኗቸው ስራዎች እንዲህ ተብሎ ተገልጿል:-"ከዚህ በኋላ በከበረች ቤተክርስቲያን ማክሰኞ ከሌሊቱ መጀመሪያው ሰዓት ካህናት ይሰብሰቡ። ተዘከሮ እግዚኦ የሚለውን የዳዊት መዝሙር ወአሰሰልኩ ዕለተ እስከሚለው ድረስ ጸልዩ። ውዳሴ ማርያምም የቀዳሚትን ይድገሙ።" ግብረ ሕማማት (ገጽ፪፻፴፪)
የመዝሙረ ዳዊት ምንባባት
በ፩ ሰዓት (መዝ፴፬:፬-፭)
በ፫ ሰዓት (መዝ፻፲፰:፻፶፬)
በ፮ ሰዓት (መዝ፲፯:፲፯)
በ፱ ሰዓት (መዝ፳፬:፩)
በ፲፩ ሰዓት (መዝ፵፬:፮)
እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ፃማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ ለብርሃነ ትንሣኤሁ እግዚአብሔር በፍስሓ ወበሰላም አሜን!
ያለ ደዌና ያለ ሕማም ያለ ፃማና ያለ ድካም እግዚአብሔር ለትንሣኤው ብርሃን እንደ ዛሬ ቀን በደስታና በፍቅር በአንድነት ያድርሰን ያድርሳችሁ አሜን!
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
በሰሙነ ሕማማት ይህንን አድርጉ
ሰሙነ ሕማማት አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ሁሉ ቤዛ ሆኖ ተላልፎ መሰጠቱን የምናስታውስበት ሳምንት ነው።
ይህንን ምክንያት በማድረግ የሥርዓት ለውጥ ሲደረግ ሲመለከቱ ግራ የሚጋቡና ሥርዓተ አምልኮውን በሚገባ ከመከታተል ይልቅ ሥርዓት የጣሱ እየመሰላቸው የሚጨነቁ ስላሉ ልናደርገው የሚገባንን እጽፍላችኋለሁ።
1️⃣. በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብሎ ፊትንና መላ ሰውነትን በትዕምርተ መስቀል {በመስቀል ምልክት} ማማተብ አይከለከልም። ከካህን እጅ ቡራኬ አንቀበልም በካህኑ እጅ ያለውን መስቀል አንሳለምምና ማማተብም የለብንም በሚል ፍልስፍና ካልሆነ ማማተብ ክልክል ነው ተብሎ የተጻፈበት ቦታ የለምና።
2️⃣. የሚከለከል ጸሎት የሌለ መሆኑን አውቃችሁ ያስለመዳችሁትን ጸሎት በትጋት ጸልዩ። መሥዋዕት ካለመሠዋታችን ቅዳሴ ካለመቀደሳችን በቀር በዚህ ሳምንት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጀምሮ እስከ ሊቃውንት ድርሳናት ድረስ በቤተ ክርስቲያን የማይጸለይ ጸሎት የለምና።
3️⃣. ሰላምታ መስጠት ከጸሎተ ሐሙስ ዕለት በቀር አልተከለከለም፤ እሱም ቢሆን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በይሁዳ ሰላምታ ተላልፎ መሰጠቱን ለማስተዎስ እንጅ ሌላ የተለየ ምክንያት ስለሌለው በመርሳት ወይም በሌላ ከድፍረት በተለየ ምክንያት ሰላምታ ያቀረበላችሁን ሰው ልታስደነግጡና ትልቅ ኃጢአት እንደሠራ አድርጋችሁ ልታስጨንቁት አይገባም።
4️⃣. “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ” ብሎ መጻሕፍትን ማንበብ ወይም ሌላ ሥራን መጀመር ይቻላል። ስመ እግዚአብሔር መጥራት የምንከለከልበት ጊዜ መቸም የለምና።
5️⃣. የጌታችንን ሕማሙንና ሞቱን የሚያስታውሱ መጻሕፍትን በማንበብና በመስማት ጊዜአችንን መወሰን ይገባናል።
6️⃣. በዚህ ሳምንት ተድላ ደስታን ሲያደርጉ መገኘት ከአይሁድ ጋር እንደ መተባበር የሚያስቆጥር ስለሆነ አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት፣ ያማረውንና ጌጠኛውን ልብስ በመልበስ፣ ባልና ሚስት በምንጣፍ በመገናኘት እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያት ከምናደርጋቸው ተድላ ደስታዎች መራቅ ይገባናል። ቅዱሳን በዘመናቸው ሁሉ ባሰቡት ጊዜ የሚያስጨንቃቸውን የክርስቶስን መከራ እያሰብን ለጥቂት ጊዜም እንኳን ቢሆን የክርስቶስን መከራ በሰውነታችን ማሰብ ይገባናል።
የተቻለው እንደ ጴጥሮስ የራሱን ኃጢአት እያሰበ እንደ ማርያም መግደላዊት የክርስቶስን ሞት እያዘከረ ሊያለቅስ ይገባዋል።
በወዲያኛው ዓለም ከማልቀስ የሚያድነን ዛሬ የራሳችንን ኃጢአት አስበን የክርስቶስን ሞት አዘክረን የምናለቅሰው ለቅሶ ነው እንጅ ዛሬ ከተደሰትን ደስታችንን በዚህ ዓለም ማድረጋችን አይደለምን?
7️⃣. በተቻለን መጠን በቤተ ክርስቲያን መዋል ይገባናል፤ ሕማማተ መስቀልን የሚያስታውሱ መጻሕፍት የሚነበቡበት ሳምንት ስለሆነ ነው። ነገር ግን በልዩ ልዩ ምክንያት በቤተ ክርስቲያን መዋል እንኳን ባይቻላችሁ ባላችሁበት ቦታ ሁናችሁ እየዋሻችሁ በሐሰት የከሰሱትን፣ እየቀማችሁ ልብሱን የገፈፉትን፣ ሰው እየደበደባችሁ በጅራፍ የገረፉትን፣ በወንድሞቻችሁና በእኅቶቻችሁ ላይ እየፈረዳችሁ በክርስቶስ ላይ የፈረዱበትን፣ በሰዎች ላይ እየተዘባበታችሁ የተዘባበቱበትን፣ በሳቅና በሽንገላ ሰውን እየሸነገላችሁ ሽንገላ በተሞላበት ሰላምታ ጌታውንና መምህሩን አሳልፎ የሰጠ ይሁዳን ልትመስሉ አይገባም።
ይልቁንም በአይሁድ እጅ ተላልፎ ቢሰጥም ንጹሓ ባሕርይ መሆኑን በማመን እስከ ቀራንዮ የተከተሉትን ደቀመዛሙርት ልትመስሉ ይገባል። እግራችሁ በመቅደሱ ውስጥ ባይቆምም ልባችሁን ከመቅደስ ልታወጡት አይገባም። እያዘናችሁ ባላችሁበት ቦታ ዋሉ።
8️⃣. በቤታችሁም ሆነ በቤተ ክርስቲያን አብዝታችሁ ስገዱ። ስለሁላችንም ቤዛ የሚሆን ክርስቶስ በፊታችን መስቀል ተሸክሞ ሲወድቅ እያያችሁት ትቆማላችሁን? አይሁድ ገፍተውት አንድ ጊዜ ወደ ምድር በወደቀ ጊዜ ለወደቀው መውደቅ ዘመናችንን ሙሉ ብንወድቅ ብንነሣ ውለታ መክፈል እንችል ይመስላችኋል?
ቅዱሳን ሳያቋርጡ ሲሰግዱ የሚኖሩት ክርስቶስ በፊታቸው በአይሁድ እጅ እየተገፋ መስቀሉን እንደተሸከመ ሲወድቅ በዓይነ ሕሊናቸው ስለሚያዩት ነው።
በስንክሳር ተጽፎ የምናገኘው ዜና ሞታቸው እየሰገዱ ሳሉ ሞት ነፍሳቸውን ከሥጋቸው ለይቶ እንደሚወስዳትና ለስገደት ታጥቀው እንደተንበረከኩ እንደሚገኙ ይነግረናል። የተሰቀለውን ክርስቶስን የሚያስብ ሰው ለሰውነቱ ዕረፍትን አይሻም።
9️⃣. ከሁሉም ሰው ጋር ፍቅርን አድርጉ። ሰውን ለመውደድ ምክንያት አታብጁ። ክርስቶስ አሳልፎ የሰጠውን ይሁዳን “ወዳጄ” ብሎ ሲጠራው አትሰሙትም?
እግዚአብሔርን አንተን ያለ ምክንያት እንደ ወደደህ አንተም ያለ ምክንያት ሰውን መውደድ ልመድ። ክርስቶስ አንተን ጠላቱ ሆነህ ሳለ ፍቅርን ካላጎደለብህ ለጠላትህ ፍቅርን አታጉድልበት።
ክርስቶስ ይሁዳን ‘’ወዳጀ’’ ብሎ ከጠራው አንተም ይሁዳዎችህን ወዳጀ ብለህ ጥራቸው። አውቃለሁ ጠላትን መውደድ መራራ ሐሞትን ከመጠጣት በላይ መራራ ነው። ነገር ግን እኔም ለይሁዳዎቻችን ፍቅርን እንስጥ ማለቴ መራራ ሐሞት የጠጣ ክርስቶስን እንድንመስለው ነው።
1️⃣0️⃣. ለሁሉም መስጠት በምትችሉት መጠን ስጡ እንጅ አትቀበሉ። ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነውና በመስጠታችሁ ብፁዓን ተብለው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገቡት ትቆጠራላችሁ።
ምናልባትም የምትሰጡት ገንዘብ ባይኖራችሁ ዕዳ ይሆንባችሁም ቢሆንም ገንዘብ ለሰጧችሁ ባለጠጎች የምትሰጡት ጸሎት ሊኖራችሁ ይገባል። ከምንጊዜውም የበለጠውን ስጦታ የተቀበልንበት ሳምንት መሆኑን እያሰባችሁ አንዳች የምትሰጡት ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ስጦታ የሌላችሁ ባዶዎች እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ።
ከሁሉ በላይ የሆነውን ስጦታ የጌታን ሥጋና ደም እነሆ ተቀብለናል።
ክርስቶስ መድኃኒነ
መጽአ ወሐመ በእንቲአነ
ወበሕማማቲሁ ቤዘወነ‼
© ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአከ
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
የሰሙነ ሕማማት ዕለታት-ሰኞ
✅መርገመ በለስ
✅አንጽሖተ ቤተ መቅደስ
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
ሥርዓተ ጸሎት ዘሰሙነ ሕማማት ፪
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
፬. በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዐርብ የስቅለቱ መታሰቢያ ነው፦ ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሰሩትን ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱን በወይራ ቅጠል ትከሻቸውን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሳፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጠባው የሚደረግለት ሰው በህማማቱ ወቅት የፈጸመው በደል ወይም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እያለ እንዲል ያደርጋል፡፡
፭. አክፍሎት፡- በሰሙነ ሕማማት ዕለተ ዐርብ ከስግደት በኋላ ምእመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሁድ /የትንሳኤ በዓል/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡ ከዓርብ እስከ ቅዳሜ ሌሊት ለእሁድ አጥቢያ ማክፈል የብዙዎች ነው፡፡ አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታቸን ያዕቆብ እና ዩሐንስ የጌታን ትንሳኤ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሳኤ መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡
ከሰኞ እስከ ሐሙስ ዕለት የሚካሄደው የሰሙነ ሕማማት የጸሎት ሥርዓት እንደሚከተለው በምስል ቀርቧል:
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
“ሆሣዕና”
በዘማሪ አቤል ተስፋዬ
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
ሆሣዕና
የዐብይ ጾም ስምንተኛ እሑድ(ሳምንት)
ሆሣዕና ከጌታችን አምላካችን ከዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከኢየሩሳሌም ወደ ቤተ መቅደስ ለመግባት በፈለገ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ፊታችው ባለው ሀገር "ሂዱና አህያ ከውርጭላዋ ጋራ ታስራ ታገኛላችው ፈታችው እምጡልኝ። 'ምን ታደርጋላችሁ?' የሚላችሁ ሰው ካለ 'ጌታቸው ይፈልጋቸዋል' በሉ" ብሎ ላካቸው ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንዳዘዛቸው ሄደው ፈተው አመጡለት በዚያም የተሰበሰቡት ሁሉ በአህዮች ላይ ልብሳቸውን ጎዘጎዙለት ጌታችንም በሁለቱ አህዮች ላይ ተቀመጠ ከሌሎቹ እንስሳት አህዮችን መርጦ በአህዮች ተቀምጧል፡ አህዮች በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ታሪክ አላቸውና።
✅የበልአም አህያ የመልአኩን ክብር ለመግለጥ አፍ አውጥታ ተናግራለች። (ዘሁል 22+28)
✅ጌታችን በተወለደ ጊዜ አህዮች ከከብቶች ጋር በበረት እስትፋሳቸውን ገብረዋል። (ቅዳሴ ማርያም)
የሆሣዕና እህዮች ከሁሉ ተመርጠው አምላካችን ተቀምጦባቸዋል: 'ለምን የተዋረዱት አህዮችን መረጠ?' ቢባል:-
፩. ደመናን አዝዞ : ነፋስን ጠቅሶ : በእሳት መንኮራኩር ላይ የሚረማመድ አምላክ ሲሆን ነገር ግን የመጣው ትሕትናን ለማስተማር : የትሕትና ጌታ መሆኑን ለመግለጽ ነውና በአህያ ተቀመጠ።
፪. ትንቢቱን ለመፈጸም <<አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዪ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሁትም ሁኖ በአህያም በውርንጭላቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል ሰረገላውንም ከኤፍሬም ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም ያጠፋል>> ብሎ ዘካርያስ ትንቢት ተናግሮ ነበርና ለመፈጸም ነው። ዘካ ፱÷፩
፫. ምሳሌውን ለመግለጽ
ምሳሌ- ቀድሞ ነቢያት ዘመነ ጸብእ ከሆነ በፈረስ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ይታያሉ ዘመነ ሰላም ከሆነ በአህያ ተቀምጠው መነሳንስ ይዘው ይታዩ ነበርና ጌታችንም ዘመነ ሰላም ነው ሲል በአህያ ተቀምጦ መጥቷል።
፬. ምሥጢሩን ለመግለጽ
ምሥጢር- በአህያ የተቀመጠ ሸሽቶ አያመልጥም አሳዶም አይዝም እሱም ካልፈለጋችሁኝ አልገኝም ከፈለጋችሁኝ አልታጣም ሲል በአህያ ተቀምጦ መጥቷል።
ህድግት የእስራኤል ምሳሌ ህድግት ቀንበር መሸከም የለመደች ናት= እስራኤልም ህግ መጠበቅ ለምደዋልና
እዋል የአህዛብ ምሳሌ
እዋል ቀንበር መሸከም አልለመደችም=አህዛብም ህግ መጠበቅ አልለመዱምና (አንድም) ህድግት የኦሪት ምሳሌ ህድግት ቀንበር መሸከም እንደለመደች=ኦሪትም የተለመደች ህግናትና
እዋል የወንጌል ምሳሌ
እዋል ቀንበር መሸከም አልለመደችም=ወንጌልም ያልተለመደች አዲስ ህግ ናትና
በሁለቱም ላይ መቀመጡ ኦሪትንም ወንጌልንም የሰራሁ እኔ ነኝ ሲል ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ ፲፮ ምእራፍ ነው ፲፬ቱን ምእራፍ በእግሩ ሂዶ ሁለቱን ምእራፍ በአህያይቱ ሂዷል በውርጭላይቱ ሁኖ ፫ ጊዜ ቤተ መቅደሱን ዙሯል ፲፬ ምእራፍ የአስርቱ ትእዛዛትና የአራቱ ኪዳናት ምሳሌ፤ አስሩ ምእራፍ የአስርቱ ትአዛዛት፣ አራቱ ምእራፍ የአራቱ ኪዳናት ምሳሌ ነው፣ አራቱ ኪዳናት የሚባሉት እነዚህ ናቸው፦ ኪዳነ ኖህ : ክህነተ መልከ ጼዴቅ :ግዝረተ አብርሀም እና ጥምቀተ ዮንሐስ ናቸው፡፡
በአህያይቱ ላይ ልብሳቸውን አንጥፈውለታል::
ልብስ በአካል ያለውን ነውር ይሸፍናል አንተም ከባቴ አበሳ ነህ ሲሉ።
በአህያዋ ላይ ኳርቻ ሳያደርጉ ልብስ አንጥፈውለታል :-
ኳርቻ ይቆረቁራል ልብስ አይቆረቁርም የማትቆረቁር ህግ ሰራህልን ሲሉ ነው።
ስለምን ልብሳቸውን አነጠፉለት ቢባል ? በእዩ ልማድ ነው ፡
እዩ የተባለው ሰው በእስራኤል ላይ ሲነግሥ እስራኤል ልብሳቸውን አንጥፈውለት ነበረና በዚያ ልማድ አንጥፈውለታል እኩሌቶቱ ደግሞ ዘንባባ አንጥፈውለታል ። 🌴
በዕለተ ሆሳዕና እስራኤላውያን ለምን የዘንባባ ዝንጣፊ፤ የቴምር ዛፍ ዝንጣፊ እና የወይራ ዛፍ ዝንጣፊ ይዘው ዘመሩ? (ማቴ. ፳፩÷፩-፲፯፣ ማር. ፲፩÷፩-፲፣ ሉቃ. ፲፱÷፳፱-፴፰፣ ዮሐ. ፲፪÷፲፪-፲፭)
የዘንባባ ዝንጣፊ
✅ ዘንባባ የድል ምልክት የደስታ መግለጫ የምስጋና መስጫ ነው፡፡
✔️ይስሃቅ በተወለደ ጊዜ አብርሃም ደስ ብሎት ዘንባባ ይዞ እግዚአብሄርን አመስግኖበታል።
✔️ይስሐቅም ያእቆብን በወለደ ጊዜ አምላኩን በዘንባባ አመስግኗል።
✔️እስራኤል ከግብጽ በወጡ ጊዜ በዘንባባ ንሴብሆ እያሉ እህተ ሙሴ ማርያም ከበሮ እየመታች አምላካቸውን አመስግነዋል፡፡
✔️ዮዲት እስራኤልን እየገደለ ያስቸገረው ሆለፎርኒስን አንገቱን ቆርጣ በገደለችው ጊዜ እስራኤል ዮዲት መዋኢት ዮዲት ኀያሊት ብለው በዘንባባ አመስግነዋታልና።
✅ዘንባባ ደርቆ እንደገና ህይወት ይዘራል የደረቀ ሕይወታችንን የምታለመልም አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
✅ዘንባባ የሰላም ምልክት ነው የሰላም አምልክ ነህ ሲሉ ነው።
✅ዘንባባ እሾሃማ ነው አንተ ህያው አሸናፊ አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
✅ዘንባባ እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል እንጅ ጌታም አንተ ባህርይህ የማይመረመር ነው ሲሉ ነው።
✅ዘንባባ የነፃነት ምልክት ነው ከባርነት ነፃ የምታወጣን አንተነህ ሲሉ ነው አኛም ይህን በማሰብ ዘንባባ ይዘን ሆሳእና በአርያም እያልን እለቱን እናስባለን፡፡
የቴምር ዛፍ ዝንጣፊ
✅የቴምር ዛፍ ፍሬ ጣፋጭ ነው፦ በሃጥያት የመረረውን ህይወታችንን የምታጣፍጥልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
✅ የቴምር ፍሬ የሚገኘው ከዛፉ ከፍታ ላይ ነው:- አንተ አምላካችን ልዑለ ባህሪ ነህ ከፍ ከፍ ያልክ አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
✅ የቴምር ዛፍ ፍሬ በውስጡ ያለው ፍሬ አንድ ነው አንድ አካል አንድ ባህሪ ነህ ሲሉ ነው።
✅ የቴምር ፍሬ በእሾህ የተከበበ ነው ይህም የአንት ባህሪ የማይመረመር በእሳት የተከበበ ነው ሲሉ ነው።
የወይራ ዛፍ ዝንጣፊ
✅ የወይራ ቅጠል የሰላም ማብሰሪያ ነው ሰላማችንን የምታበስርልን የምታስገኝልን አንተ ነህ ሲሉ ነው፡፡
✅ የወይራ ቅጠል ከእንጨት ሁሉ ጽኑ ነው አንተም ጽኑ ሃያል አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
✅ወይራ ለመብራት ያገለግላል ፍሬው ዘይት ያወጣል ከወይራ የሚገኝ ዘይት ጨለማን አሸንፎ ብርሃን እንደሚሰጥ ሁሉ አንተም ጨለማ ህይወታችንን የምታስወግድልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው።
✅ በኦሪት ግዜ የወይራ ዘይት ለመስዋአትነት ይቀርብ ነበር አንተም እንደ ዘይቱ ለመተላለፋችን መስዋዕት ሆነህ የምትቀርብ አምላክ ነህ ሲሉ ነው። በመስቀል ላይ መስዋዕት ሆኗልና።
ከፊት ከኋላ ያሉት "ሆሣዕና በዓርያም ለዳዊት ልጅ መድኀኒት መባል ይገባዋል" እያሉ አመስግነውታል የምስጋና ጌታም በአህዮች ተቀምጦ ወደ መቅደስ ገብቷል።
በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ጥቅሶች፦
-ዕብ ፱፥፲፩ እስከ ፍጻሜ
-፩ጴጥ ፬፥፩-፲፪
-ሐዋ ፳፰፥፲፩ እስከ ፍጻሜ
ምስባኩም፦ መዝ፰፥፪
"እመ አፈ ደቂቅ ወሕጻናት አስተዳሎከ ስብሐተ በእንተ ጸላኢ ከመትንሥቶ ለጸላዒ ወለገፋዒ"
"ከሕጻናት አንደበት ምስጋናን አዘጋጀህልኝ፡፡ ስለ ጠላትና ቂመኛን ለማጥፋት"
ወንጌሉም፦ ዮሐ፭፥፲፩-፲፫
ቅዳሴ ፦ ዘጎርጎርዮስ (ነአኵቶ)[በዕዝል ዜማ]
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
የሰሙነ ሕማማት ዕለታት
ዓርብ
ዕለተ ዓርብ በቤተክርስቲያን ልዩ ቀን ነው፡፡ የማይታመመው ታሞ የዋለበት፣ የወደቁ ከተረሱበት ከትቢያ የሚያነሳ እሱ ሲወድቅ ሲነሳ የዋለበት፣ ሕመምተኞችን የሚፈውስ እሱ ሲያቃስት የዋለበት፣ ከሲኦል የዲያብሎስ ግብር ነፃ የሚያወጣ ሲገረፍ የዋለበት፣ ወልደ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ድኅነት በመስዋዕትነት ሙሽራ የሆነበት የደስታ ቀን፤ አሳዳጅ አሳሪያችን ዲያብሎስ ከነወጥመዱ ድል የተነሳበት ቀን ነው። ከዚህም የተነሳ በቤተክርስቲያን የተለያየ ምስጢራዊ ስያሜዎች ተሰጥቶታል፡፡
የስቅለት ዓርብ ይባላል
የዓለም ሁሉ መድኀኒት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ለዓለም ድኅነት መስዋዕት ሆኖ የዋለበት ዕለት በመሆኑ የስቅለት ዓርብ ተብሏል። (ማቴ 27፡35)
መልካሙ ዓርብ ይባላል
ይህም የሚያስገነዝበን ከስቅለተ ክርስቶስ በፊት ማንም ሰው ሲያጠፋ በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት ይደረግ ነበር፡፡ በተለይ በሮማውያንና በፈሪሳውያን ሕግ መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ነበረ። በዚህ ዕለት ግን ታሪክን የሚቀይር ነገርን የሚገለብጠው አምላክ የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል በደሙ ቀድሶ የምህረት ምልክት፣ የሕይወት አርአያ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ ፣ የቤተክርስቲያን ጌጥ፣ የገዳማት ዘውድ ስላደረገውና በዕለተ ዓርብ በሞቱ ሕይወትን ስላገኘን መልካሙ ዓርብ ተብሏል፡፡
† 13ቱ ሕማማተ መስቀል
1ኛ. ተአስሮ ድኅሪት (ወደኋላ መታሰር)
2ኛ. ተስሕቦ በሐብል (በገመድ መሳብ)
3ኛ. ወዲቅ ውስተ ምድር (በምድር ላይመውደቅ)
4ኛ. ተከይዶ በእግረ አይሁድ (በእግረ አይሁድመረገጥ)
5ኛ. ተገፍዖ ማዕከለ ዓምድ (ከምሶሶ ጋርመላተም)
6ኛ. ተጽፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)
7ኛ. ተቀሰፎ ዘባን (ጀርባን በጅራፍ መገረፍ)
8ኛ. ተኰርዖተ ርእስ (ራስን በዱላ መመታት)
9ኛ. አክሊለ ሦክ (የሾህ አክሊል መድፋት)
10ኛ. ፀዊረ መስቀል (መስቀል መሸከም)
11ኛ. ተቀንዎ በቅንዎት (በችንካር መቸንከር)
12ኛ. ተሰቅሎ በዕፅ (በመስቀል ላይመሰቀል)
13ኛ. ሰሪበ ሐሞት (መራራ ሐሞትንመጠጣት)
† ጌታችን ከ6-9 ሰዓት በመስቀል ላይ ሳለ የተናገራቸው 7ቱ የፍቅር ቃላት
1ኛ.ኤሎሄ ኤሎሄ ኤልማስ ላማ ሰበቅታኒ ማቴ.27፤46
2ኛ. እውነት እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ፡፡ ሉቃ.23፤43
3ኛ.አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራእሰጣለሁ፡፡ ሉቃ.23፤46
4ኛ.አባት ሆይየሚያደርጉትን አየውቁምና ይቅር በላቸው፤ሉቃ.2334
5ኛ. እናትህ እነኋት፤ እነሆ ልጅሽ፤ዮሐ.19፤26-27
6ኛ. ተጠማሁ፤ ዮሐ.19፤30
7ኛ. ተፈጸመ፤ ዮሐ.19፤30
† ጌታችን በመስቀሉ ከ6-10 ሰዓት በመስቀልላይ ሳለ የተፈጸሙ 7ቱ ተአምራት፤
1ኛ. ፀሐይ ጨለመች
2ኛ. ጨረቃ ደም ሆነች
3ኛ. ከዋክብት ብርሃናቸውን ነሱ
4ኛ. የቤተመቅደስ መጋረጃ ለሁለት ተከፈለ
5ኛ. ዐለቶች ተሰነጣጠቁ
6ኛ. መቃብራት ተከፈቱ
7ኛ. የሞቱት ተነሡ፤ ማቴ.27፤45-46
5ቱ ቅንዋተ መስቀል ችንካሮች ሳዶር ፣ አላዶር ፣ ዳናት ፣ አዴራ እና ሮዳስ ይባላሉ።
1. ሳዶር ፦ ማለት ቀኝ እጁ የተቸነከረበት
2. አላዶር፦ ማለት ግራ እጁ የተቸነከረበት
3. ዳናት ፦ ማለት እግሮቹ የተቸነከረበት
4. አዴራ ፦ ማለት ደረቱን የተቸነከረበት
5. ሮዳስ ፦ ማለት ከወገቡ(እብርቱ) አጣብቆ እንዲይዝ የተቸነከረበት
=============================
☞ሞትን ይሽረው ዘንድ የማይሞተው ሞተ መከራን ታገሰ
☞ሁሉን የያዘውን እርሱን ያዙት
☞ሁሉን የሚገዛውን እርሱን የአምላካችንን እጅ አሰሩት
☞ኃጥአትን የሚያስተሰርይ እርሱን ኃጢአተኛ አሉት
☞የማይገረፍ አምላክ እርሱን የሰውን ሥጋ በመልበሱ ገረፉት
☞እንደ መብረቅ የሚያንፀባርቀውን ነጭ ልብስ የሚያለብስ አምላክ እርሱን ቀይ ግምጃ አለበሱት።
☞በእሳት በተጋረዱ ዙፋን ላይ የሚቀመጥ እርሱን በመዘባበቻ ወንበር ላይ አስቀመጡት።
☞እንደ ድንኳን ሰማይን የዘረጋ እርሱን በመስቀል ላይ ሰቀሉት
☞የመላእክትን አለቆች በፊቱ በመፍራት የሚቆሙለት እርሱን በጲላጦስ ፊት አቆሙት
☞በሕያዋንና በሙታን ላይ የሚፈርድ እርሱን እንደበደለኛ ተፈረደበት
☞ዓለምን ሁሉ በቅፅበት የፈጠረ እርሱ በሥጋው ሞተ በመለኮት ሕያው ሆነ
እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ፃማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ ለብርሃነ ትንሣኤሁ እግዚአብሔር በፍስሓ ወበሰላም አሜን!
ያለ ደዌና ያለ ሕማም ያለ ፃማና ያለ ድካም እግዚአብሔር ለትንሣኤው ብርሃን እንደ ዛሬ ቀን በደስታና በፍቅር በአንድነት ያድርሰን ያድርሳችሁ አሜን!
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
ጉልባን እና ምሣሌው
ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ በጸሎተ ሐሙስ በቤት ውስጥ ከሚፈጸሙ ተግባራት አንዱ ጉልባን ማዘጋጀት ነው፡፡ ጉልባን እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ በችኮላ መጓዛቸውን የምናስታውስበት ከእስራኤላውያን የመጣ ትውፊታዊ ሥርዓት ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ አብዛኞቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ይህ ሥርዓት ዛሬም በኢትዮጵያውያን ምእመናን ዘንድ ይከበራል፡፡
❖ ጉልባን እስራኤላውያን ከባርነት በወጡ ጊዜ አቡክተው፣ ጋግረው መብላት አለመቻላቸውን ያስታውሰናል፡፡ በወቅቱ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መመገብ፤ ንፍሮ ቀቅለው ስንቅ መያዝ የመንገድ ተግባራቸው ነበርና፡፡ ይህን ታሪክ ለማሰብም በሰሙነ ሕማማት በተለይም በጸሎተ ሐሙስ ቂጣና ጉልባን ይዘጋጃል፡፡ በጸሎተ ሐሙስ የሚዘጋጀው ጉልባንና ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ይኸውም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ዅሉ፣ ጌታችንም በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ ነው፡፡ ባቄላው ይከካል ቅርፊቱ ይላጣል ምሳሌውም የጌታችንን መከራ እና አይሁዳውያን ልብሱን አውልቀውት ነበር የዚያ መታሰቢያ ነው።
❖ በሊቃውንቱ ትምህርት ጉልባን ከስንዴ እና ከባቄላ ይዘጋጃል፤ ባቄላው ይታመሳል፣ ይፈተጋል፣ይከካል ስንዴው ግን አይከካም ፣ አይፈተግም፣ አይታመስምም ይኸውም ምሳሌነቱ ስለእኛ በተዋህዶ ለከበረው አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ መታሰቢያ ነው። ማለትም ባቄላው የስጋ ስንዴው ደግሞ የመለኮት ምሳሌ ነው። ምንም እንኳን መለኮት ከሥጋው ያልተለየው አምላክ ቢሆንም ሕማሙ ግን መለኮትን አላገኘውም። የተዋህዶ መዶሻ የተባለ ቅዱስ ቄርሎስ እንዳስተማረው ነገረ ተዋህዶን በጋለ ብረት እንዳስተማረው ብረን ከእሳቱ ውስጥ ቢጨምሩት ብረቱ እሳቱን ይመስላል እሳቱም የብረቱን ቅርፅ ይይዛል ብረቱን ቢመቱት ይለዝባል የማይጨበጠው እሳትም ከብረት ስለተዋሀደ አንጥረኛው ይመተዋል እሳቱን ግን አያገኘውም።
መለኮት የተዋሀደው ሥጋ መከራን ተቀበለ በሥጋም ሞተ ፤ ለመለኮት ግን ሕማም ድካም ሞት አይስማማውም፤ ይኸውም መለኮት ከሥጋው አንደተዋሀደ በነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ምርኮን ማረከ ነፍሳትን ነፃ አወጣ ገነትም አስገባቸው ፤መለኮት የተዋሀደው ሥጋ ወደ መቃብር ቢወርድም በሦሥተኛውም ቀን በታላቅ ኃይል በስልጣን ክርስቶስ ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ።
መልካም በዓል!
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
የሰሙነ ሕማማት ዕለታት-ሐሙስ
✅የምሥጢር ቀን
✅የነጻነት ሐሙስ
✅አረንጓዴ ሐሙስ አምላካችን የጸለየበትን የአትክልት ቦታ ወይም ጌቴሴማኒ ለማሰብ ይህ ስያሜ ተሰጥቶታል
@Ethiopian_Orthodox
ጭፍሮቹም በዚሁ ዕለት ሌሊት የክብር ባለቤት የሆነውን ጌታችንን ይዘው ወደፊት፣ ወደኋላ እየጐተቱ፣ እያዳፉ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወስደውታል።
መዝሙረ ዳዊት ምንባባት
በአንድ ሰዓት፡- "አፉ ከቅቤ ይልቅ ለዘበ ፤ በልቡ ግን ሰልፍ ነበረ ፤ ቃሎቹም ከዘይት ይልቅ ለሰለሱ ፤ እነርሱ ግን እንደ ተመዘዘ ሰይፍ ናቸው" (መዝ፶፬(፶፭)፡፳፩)
በሦስት ሰዓት፡- "የጻድቅን ነፍስ ያደቡባታል፤ በንጹህ ደምም ይፈርዳሉ፡፡"(መዝ፺፫(፺፬):፳፩)
በስድስት ሠዓት፡- "የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁና በዙሪያው ፍርሃት ነበረ በላዬ በአንድነት በተሰባሰቡ ጊዜ ፤ ነፍሴን ለመንጠቅ ተሰባሰቡ፡፡"(መዝ፴ (፴፩):፲፫
በዘጠኝ ሰዓት፡- "እግዚአብሔር እረኛዬ ነው ፤ የሚያሳጣኝም የለም ፤ በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፡፡" መዝ፳፪(፳፫):፩-፪
ኅጽበተ እግር ሲጀመር ደግሞ "በሂሶጵ እርጨኝ እነጻማለው እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለው፡፡" (መዝ፶:(፶፩):፯)
በመጽሐፈ ግብረ ሕማማት፡- "ከዚህ በኋላ የእግር እጥበት ሥርዓት ነው ፤
ዲያቆን ሁለት ኩስኩስቶች ያቅርብ በውስጣቸውም ውኃ ይምላባቸው አንዱ
ለእጅ መታጠቢያ እንዲሆን ካህኑም እስከ መጨረሻው ጸሎተ አኮቴት ይበል ፤
ጸሎተ ዕጣኑንም ደግሞ ዕጣንን ያሳርግ ፤ ስለ ሰላም ስለ ሊቀ ጳጳሳት ስለ ማኅበር ይጸልይ፡፡ ሕዝቡም ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን ይበሉ፡፡ አቡነ ዘበሰማያትም ይበሉ ፤ ኀምሳኛውንም የዳዊትን መዝሙር ይበሉ፡፡" (ግብረ ሕማማትገጽ፭፻፵፪)
"ከዚህ በኋላ ሕዝቡ ይነሱ አርባ አንድ ጊዜ ኪራላይሶን ይበሉ ካህኑም መስቀል ይዞ ውኃውን ሦስት ጊዜ አሐዱ አብ ቅዱስ (ልዩ ክቡር ንጹሕ ጽኑዕ ነው) ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ (ልዩ ክቡር ንጹሕ ጽኑዕ ነው) ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ (ልዩ ክቡር ንጹሕ ጽኑዕ ነው) እያለ ሦስት ጊዜ ውኃውን ይባርክ፡፡" (ግብረ ሕማማት ገጽ ፭፻፶፱)
"ከዚህ በኋላ ካህኑ እንደ ሥርዓቱ ኅጽበተ እግርን ያድርግ (ይፈጽም) ከዚህ በኋላም ጥቁር ልብስ ለብሰው ሥርዐተ ቅዳሴውን ይጀምሩ የቃጭል ድምጽንም አያሰሙ፡፡" (ግብረ ሕማማት ገጽ፭፻፷፩)
በአሥራ አንድ ሰዓት፡- "በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ ጽዋዬም የተረፈ ነው" (መዝ፳፪(፳፫):፭-፮)
የአይሁድ ካህናት ያለበደል እና ያለጥፋት ንጹሑን ክርስቶስን ለመስቀል ሞት እንዲደርስ በጭካኔ በዕለተ ሐሙስ ከሌሊቱ 3፡00 ጀምሮ ብዙ መከራ አደረሱበት ፤ እጅጉን ተሰቃየ ፤ እያዳፉ አንዳች ሳይናገር አሰቃዩት ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በትንቢት መነጽር የተመለከተውን የጌታችንን ስቃይ እንዲህ ሲል ያመጣዋል፡-
"ተጨነቀ ተሠቃየም አፉንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ከክፉዎቹም ጋር መቃብሩን አደረጉ..."(ኢሳ፶፫:፩-፰)
እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ፃማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ ለብርሃነ ትንሣኤሁ እግዚአብሔር በፍስሓ ወበሰላም አሜን!
ያለ ደዌና ያለ ሕማም ያለ ፃማና ያለ ድካም እግዚአብሔር ለትንሣኤው ብርሃን እንደ ዛሬ ቀን በደስታና በፍቅር በአንድነት ያድርሰን ያድርሳችሁ አሜን!
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
🩸"በዕፀ መስቀል ላይ"🩸
በዕጸ መስቀል ላይ በዚያ አደባባይ/2/
አምላክ ሆይ ጌታ ሆይ ተንገላታህ ወይ
አምላክ ሆይ ጌታ ሆይ መከራ አየህ ወይ
አዝ
መስቀል አስይዘው ኪርያላይሶን
ወደ ጎልጎታ " "
ሲገርፉህ ሲያዳፉህ " "
ስትንገላታ " "
አዝ
ያንን አቀበት ኪርያላይሶን
ያንን ዳገት " "
ጀርባህ ተገርፎ " "
ስትቃትት " "
አዝ
አንተን እያዩ ኪርያላይሶን
ሴቶች ሲያለቅሱ " "
እናቶች ቀርበው " "
ላብህን ዳበሱ " "
አዝ
መስቀል አስይዘው ኪርያላይሶን
እንዲያ ሲያዳፉህ " "
የቀሬናው ሰው " "
ስምኦን አገዘህ " "
በዘማሪት ማርታ ኃይሉ
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
የሰሙነ ሕማማት ዕለታት
ረቡዕ
በዚህች ዕለት ያስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ እንደሰጠውና ሌሎችም ይታሰባሉ። በቅዱስ ማቴዎስና በቅዱስ ማርቆስ አመዘጋገብ መሠረት በዕለተ ረቡዕ የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ተፈጽመዋል፦
፩. ምክረ አይሁድ ይባላል
የካህናት አለቆች፣ የሕዝብ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታችን ላይ ተማክረዋል፤
፪. የመልካም መዓዛ ቀን ይባላል
ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ አንዲት የተጸጸተች ሴት ሽቱ ቀብታዋለች፡፡
፫. ከዳተኛው ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያንና ከካህናት አለቆች ዘንድ ሠላሳ ብር ለመቀበል ተስማምቷል፡፡
የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሹማምት በጌታችን ላይ ይሙት በቃ ለመወሰን የሰበሰቡት ሸንጐ ‹ሲኒሃ ድርየም› ይባላል፡፡ በዚህ ሸንጐ ላይ በአብዛኛው የተሰየሙት ሰዱቃውያን ሲኾኑ ሌሎቹ ደግሞ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ነበሩ፡፡
ሸንጐው በአጠቃላይ ሰባ ሁለት አባላት የነበሩት ሲኾን የሚመራውም በሊቀ ካህናቱ በቀያፋ ነበር፡፡ በዕለቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ይዘው እንደሚገድሉት አይሁድ በዚህ ሸንጎ መክረዋል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳም ጸሐፍት ፈሪሳውያንና የካህናት አለቆች በጌታን ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ያውቅ ስለነበር ‹‹ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ? እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤›› በማለት ጌታችን አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተስማቷል፡፡
ጌታችን ያስተምር በነበረበት ወቅት የአስቆሮቱ ይሁዳ ከምእመናን ለሚገባው ገንዘብ ሰብሳቢ (ዐቃቤ ንዋይ) ነበር፡፡ ከሚሰበሰበው ሙዳየ ምጽዋት ለግል ጥቅሙ እየቀረጠ የማስቀረት የእጅ አመል ነበረበት፡፡ ይሁዳ ፍቅረ ንዋይ እንደሚያጠቃው ድብቅ አመሉ ጎልቶ የወጣው ጌታችን በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የኾነ ሽቱ በቀባችው ጊዜ ነው፡፡ በዚያች ዕለት ይሁዳ የተቃውሞ ድምፅ ካሰሙት አንዱ ነበር፡፡
‹‹ይህ ሽቱ ተሽጦ ለድሆች ቢሰጥ መልካም ነበር፤›› በማለት ያቀረበው አሳብ ‹‹አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓች›› እንደሚባለው ነበር፡፡ ሽቱ ሲሸጥ የሚያገኘው ጥቅም አለ፤ ሽቶው በጌታችን እግር ሥር ከፈሰሰ ለእርሱ የሚተርፈው የለም፡፡
ይሁዳ ተቆርቋሪ መስሎ ያቀረበው አሳብ ተቀባይነት በማጣቱም ማኩረፊያ ያገኘ
መስሎት በቀጥታ ከካህናት አለቆች ዘንድ ሔዶ ጌታንን በሠላሳ ብር ለመሸጥ ተዋዋለ፡፡ ይህ ታሪክም በሦስቱ ወንጌላት ውስጥ በሚከተሉት ምዕራፎች ተመዝግቦ እናገኛዋለን፤ ማቴ. ፳፮፥፫-፲፮፤ ማር. ፲፬፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፪፥፩፮፡፡
የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ተምሯል፡፡ በረከተ ኅብስቱን ተመግቧል፡፡ ልዩ ልዩ ተአምራት በጌታችን እጅ ሲደረጉ ዅሉ ተመልክቷል፡፡
ጌታችንም ከሌሎች ሐዋርያት ሳይለየው እግሩን አጥቦታል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳ ግን ለሐዋርያነት የጠራውን፣ ተንበርክኮ እግሩን ያጠበውን ጌታ ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ‹‹የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሔዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት!›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፳፮፥፳፬)፡፡ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ዘንድ ፍቅሩን ገንዘብ ሲያደርጉ ይሁዳ ግን እርግማንን ነው ያተረፈው፡፡ ‹‹ገንዘብ የኃጢአት ሥር ነው፤›› ተብሎ አንደ ተነገረ የኃጢአት ሥር የተባለው ገንዘብ የክርስቲያኖችን ሕይወት ያዳክማልና ምእመናን እንደ ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር እንዳንወድቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሰው ‹‹ይህን ዓለም ቢያተርፍ ነፍሱን ከጐዳ ምን ይጠቅመዋል?›› ተብሎ የተነገረውን ቃል ልብ ማለት ጠቃሚ ነው፡፡
ክርስቲያን ነን በማለት የክርስትናውን ስም በመያዝ እምነታቸውን፣ የቆሙበትን ዓላማ በመገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ዛሬም እንደ ይሁዳ ጌታችንን እየሸጡት እንደ ኾነ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ለድሆች መመጽወት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡
ዳሩ ግን በድሆች ስም የሰውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ድሆችን ለረኃብ ለችግር ባልንጀራቸውን ለመከራ እና ለሞት አሳልፈው ሲሰጡ ምንም አይጸጽታቸውም፡፡
እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ሕይወታችንን ለገንዘብ ፍቅር ሳይኾን ለእምነታችንና ለባልንጀራችን አሳልፈን መስጠት ይኖርብናል፡፡ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሰዎችን አሳልፎ በመስጠት ለአይሁዳዊ ሸንጐ ምቹ ኾነን መገኘት እንደሌለብን መገንዘብ አለብን፡፡
እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ፃማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ ለብርሃነ ትንሣኤሁ እግዚአብሔር በፍስሓ ወበሰላም አሜን!
ያለ ደዌና ያለ ሕማም ያለ ፃማና ያለ ድካም እግዚአብሔር ለትንሣኤው ብርሃን እንደ ዛሬ ቀን በደስታና በፍቅር በአንድነት ያድርሰን ያድርሳችሁ አሜን!
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
የሰሙነ ሕማማት ዕለታት-ማክሠኞ
✅የጥያቄ ቀን
✅የትምህርት ቀን
@Ethiopian_Orthodox
🩸"ዓለምን ለማዳን"🩸
ዓለምን ለማዳን የተሰቀለው
ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው /፪/
ጌታችን ተሰቅሎ ሲያዩት መላእክት
በዝማሬ ፈንታ አለቀሱለት
ሚካኤል ዝም አለ ገብርኤል ገረመው
አምላኩን እርቃኑን ተሰቅሎ ስላየው
አዝ=====
ነፍሱን ለወዳጁ የሚሰጥ ቢገኝም
ለጠላቱ የሚሞት በጭራሽ አይኖርም
ጠላቶቹ ስንሆን ለእኛ የሞተው
በመስቀል የዋለው በፈቃዱ ነው
አዝ=====
እውሩን ቢያበራ የሞተ ቢያስነሳ
በመመስገን ፈንታ ሆነበት ወቀሳ
ከመከራ ሊያድን ቢገለጥ በስጋ
የእሾህ አክሊል ደፋ ቀኝ ጎኑ ተወጋ
አዝ=====
የጸሎተ ሐሙስ ዕለት እራት የሆነው
አርብ በመስቀል ላይ የተሰቀለው
ፍቅር አስገድዶት ለእኛ የሞተው
መልካሙ እረኛችን መድኃኔዓለም ነው /፪/
በዘማሪት ፋንቱ ወልዴ
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
የሰሙነ ሕማማት ዕለታት
ሰኞ
፩. መርገመ በለስ (በለስ የተረገመችበት) ዕለት ነው።
አንድምታ፡
ወንጌሉ እና ግብረ ሕማማቱ ላይ እንደተገለጸው
☞በለስ የቤተ እስራኤል እና ፍሬ የሃይማኖትና የምግባር ምሳሌ ናቸው ፡፡ ጌታችን ከእስራኤል ፍቅርን፣ ሃይማኖትን፣ ምግባርን ፈለገ፤ አላገኘም፡፡ ስለዚህም እስራኤል ሕዝበ እግዚአብሔር መባልን እንጂ፣ ነቢይነት፣ ካህንነት፣ መሥዋዕት አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፡፡ በመርገሙ ምክንያት ትንቢት ክህነት መሥዋዕት ከቤተ እስራኤል ጠፉ፡፡
☞በለስ ኦሪት ናት፤ ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት "ኦሪትና ነቢያትን ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣሁም፡፡" በማለት ፈጸማት ፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና ፍሬ ባንቺ አይሁን አላት ፤ ድኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡ በአዲስ ኪዳን የድኅነት ዘመንም ተተካች፡፡
☞በለስ ኃጢአት ናት ፤ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነ ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሰሩት ደስ ያሰኛል ኋላ ግን ያሳዝናል፡፡ "በአንቺ ፍሬ አይገኝ" ማለቱም
"በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር" ማለት ነው፡፡ በለሷም ስትረገም ፈጥና መድረቋ፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በአምላካችን እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡
፪. አንጽሖተ ቤተመቅደስ የተከናወነበት ዕለት ነው።
ጌታችን በለስን ከረገማት በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ ቤተ መቅደስ፣ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምስያጥ (የንግድ ቤት) ሆኖ ቢያገኘው "ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች… እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት" ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው፣ ገርፎም አስወጣቸው...'' እንዲል። (ማቴ ፳፩፡፲፫)
ምስጢሩ :-
☞ቤተመቅደስ የሆንን እኛ የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ አንጽሖተ ቤተመቅደስ የተፈጸመበት ሰኞም በማለት ሊቃውንት ይገልጹታል።
እንበለ ደዌ ወሕማም እንበለ ፃማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሐነ ያብጽሕክሙ ለብርሃነ ትንሣኤሁ እግዚአብሔር በፍስሓ ወበሰላም አሜን!
ያለ ደዌና ያለ ሕማም ያለ ፃማና ያለ ድካም እግዚአብሔር ለትንሣኤው ብርሃን እንደ ዛሬ ቀን በደስታና በፍቅር በአንድነት ያድርሰን ያድርሳችሁ አሜን!
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
እብኖዲ፣ ትስቡጣ ፣ ማስያስ ፣ ታኦስ ፣ ናይናን እና ኪርያላይሶን ትርጉማቸው ምንድን ነው???
@Ethiopian_Orthodox
በግብረ ሕማማት ውስጥ የሚገኙ ባዕድ ቃላት
በግብረ ሕማማት ውስጥ ወደ ግእዝም ሆነ በኋላ ወደ አማርኛ ሳይተረጎሙ የተቀመጡ የዕብራይስጥ፣ የቅብጥ እና የግሪክ ቃላት ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ቃላት ትርጉም የሚከተለው ነው፡፡
ኪርያላይሶን ቃሉ የግሪክ ሲሆን አጠራሩ «ኪርዬ ኤሌይሶን» ነው፡፡ «ኪርያ» ማለት «እግዚእነ» ማለት ሲሆን «ኪርዬ» ማለት ደግሞ «እግዚኦ» ማለት ነው፡፡ ሲጠራም «ኪርዬ ኤሌይሶን» መባል አለበት፡፡ ትርጉሙም «አቤቱ ማረን» ማለት ነው፡ ፡ «ኪርያላይሶን» የምንለው በተለምዶ ነው፡፡ ይኼውም ኪርዬ ከሚለው «ዬ» ኤላይሶን ከሚለው ደግሞ «ኤ» በመሳሳባቸው በአማርኛ «ያ»ን ፈጥረው ነው፡፡
ናይናን-የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «መሐረነ፣ ማረን» ማለት ነው፡፡
እብኖዲ-የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «አምላክ» ማለት ነው፡፡ «እብኖዲ ናይናን» ሲልም «አምላክ ሆይ ማረን» ማለቱ ነው።
ታኦስ-የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙ «ጌታ፣ አምላክ» ማለት ነው፡፡ «ታኦስ ናይናን» ማለትም «ጌታ ሆይ ማረን» ማለት ነው፡፡
ማስያስ-የዕብራይስጥ ቃል ሲሆነ ትርጉሙ «መሲሕ» ማለት ነው፡፡ «ማስያስ ናይናን» ሲልም «መሲሕ ሆይ ማረን» ማለት ነው።
ትስቡጣ-«ዴስፓታ» ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ደግ ገዥ ማለት ነው።
አምንስቲቲ ሙኪርያቱ አንቲ ፋሲልያሱ የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ- አቤቱ በመንግሥትህ አስበን» ማለት ነው፡፡
አምንስቲቲ መዓግያ አንቲ ፋሲልያሱ የቅብጥ ቃል ሲሆን «ተዘከረነ ኦ ቅዱስ በውስተ መንግሥትከ – ቅዱስ ሆይ በመንግሥትህ አስበን» ማለት ነው።
አምንስቲቲ ሙዳሱጣ አንቲ ፋሲልያሱ የቅብጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም «ተዘከረነ እግዚአ ኩሉ በውስተ መንግሥትከ-የሁሉ የበላይ የሆንክ ወይ በመንግሥትህ አስበን» ማለት ነው፡፡
@Ethiopian_Orthodox
የ፵፩/41 ስግደት ምን እየተባለ ይሰገዳል?
አንድ ክርስቲያን በጾም ጊዜ ከጸሎት በኋላ የጌታን መከራና ለእኛ ያሳየውን ፍቅር እያሰበ ከሐጢያቱ ብዛት ከአምላኩ ይቅርታ ያገኝ ዘንድ ፵፩/41 ጊዜ እንዲህ እያለ ይስገድ:-
፲፪/12 ጊዜ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ
፲፪/12 ጊዜ በእንተ እግዝዕትነ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ
፲፪/12 ጊዜ ኪርያላይሶን
፭/5 ጊዜ ሳዶር፣አላዶር፣ዳናት፣አዴራ፣ሮዳስ(አምስቱ የጌታ ችንካሮች)
እነዚህም ቢደመሩ ፵፩/41 ይሆናሉ፡፡
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
ሥርዓተ ጸሎት ዘሰሙነ ሕማማት ፩
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox
🩸 ሰሙነ ሕማማት 🩸
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከዕለተ ትንሣኤ በፊት ያለውን ሳምንት "ሰሙነ ሕማማት" በማለት ታከብረዋለች። "ሕማማት" የሚለው ቃል "ሐመ" ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን የዚህ ስያሜ መነሻም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መከራው፣ሕማሙና ሞቱ የሚዘከርበት ከአዳም እስከ ክርስቶስ የነበረው የዓመተ ፍዳ የዓመተ ኩነኔ ወቅትም የሚታሰብበት ስለሆነ "ሰሙነ ሕማማት" ተብሏል።
በዚህ ልዩ በሆነ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠልስት፣ በቀትር፣ በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ያዘክራሉ፤ ቅዱስ ያሬድ በመጨረሻው ሳምንት በየዕለቱ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን ነገረ መስቀል በተመለከተ ያዘጋጀውን መዝሙር ይዘምራሉ፤ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሆኖ ሳለ ሕማማትን መቀበሉ ስለምን ነው ቢሉ፡-
☞ፍቅሩን ለመግለጽ፡- ለፍጥረቱ ይልቁንም ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅሩን ይገልጽ ዘንድ(ዮሐ ፫÷፲፮) ምንም በደል ሳይኖርበት ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ(ዮሐ ፲፭÷፲፫)
☞የኃጢአትን ፍዳ ከባድነት ለማሳየት፡- እርሱ ጻድቅና ንጹህ ሆኖ ሳለ ሰውን ወዶ ይህን ያህል መከራ ከተቀበለ ሰው ኃጢአት በመሥራት ቢመላለስ የኃጢአትን ውጤት ከባድነት ያስተምረናል፡፡ ራሱ ጌታችንም ከጲላጦስ ግቢ እስከ ቀራንዮ አደባባይ መስቀል ተሸክሞ ሲንገላታ ላለቀሱለት የኢየሩሳሌም እናቶች <<በእርጥብ እንጨት የሚያደርጉ ከሆነ በደረቀውስ እንዴት ይሆን>> በማለት ገልጾለታል፡፡ (ሉቃ ፳፫÷፳፪)
☞ቤዛ ለመሆን፡- በኦሪት ዘመን ሰዎች ለሠሩት ኃጢአት ኃጢአታቸውን ለማስተሰርይ ነውር የሌለበትን በግ ቤዛ እንዲሆናቸው መስዋዕት ያቀርቡ ነበር ይህ ግን ከአዳም የተሰወረውን ኃጢአት ማስቀረት ስላልቻሉ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሁኖ መጣ <<እነሆ የእግዚአብሔር በግ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ>>(ዮሐ ፪÷፳፮)
☞እርግማናችንን ለማስቀረት፡- <<በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፏልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን>>(ገላ ፫÷፲፫) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው እርግማናችንን ተሸክሞ ሕማማትን መቀበሉ የቀድሞው ኃጢአት ምንም ያህል ከባድ ቢሆን በታላቅ መስዋዕትነት እንዳስቀረልን ሊያስተምረን ነው፡፡ (ዘዳ ፳፩÷፳፫)
☞የድኅነታችንን ክቡርነት /ውድነት/ ሊያስረዳን ፡- ድኅነታችንን የእግዚአብሔር ልጅ ደሙን እስኪያፈስለት ድረስ እጅግ ውድ መሆኑን ሊያስተምረን፡፡ (ራዕ ፭÷፱)
@Ethiopian_Orthodox
ሰሙነ ሕማማትን ከሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ልዩ የሚያደርገው ሥርዓት አለ፡፡
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ደንብ መሠረት በሰሙነ ሕማማት :
ሊሰሩ ያልተፈቀዱ በርካታ ናቸው:: በመስቀል መባረክ፣ መሳቅ፣ መሳሳም፣ ከሴት ጋር መገናኘት(ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 593)፣ ኑዛዜ መፈጸም ፈጽሞ የተከለከለ ሲሆን የ5500ው የጨለማ ዘመን መታሰቢያ በመሆኑ መንበሩ በጥቁር ልብስ ይሸፈናል ካሕናትም ጥቁር ይለብሳሉ:: በዚህ ሳምንት ለሞተ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይለትም፣ ክርስትናም እንዲሁ አይፈጸምም:: "እግዚአብሔር ይፍታህ" አይባልም(ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 600)፤ ሳምንቱ የሚታሰበው ሕማሙን ሞቱን በማሰብና በስግደት ነው:: የግዝት በዓላት(12፣21 እና 29) እንኳ ይሰገድባቸዋል:: የዚህ ሳምንት ጾም የቻለ ሁለት ሁለት ቀን ያልቻለ እስከ ጀንበር ግባት ድረስ ነው:: ምግቡም ቆሎ ዳቦ የላመ የጣመ ያልሆነ ደረቁን በበርበሬ ነው፤ መጠጡም ንጹህ ውኃ ነው:: ጠጅ ያንቆረቆረ ጮማ የቆረጠ እድል ፈንታው ጽዋእ ተርታው በጌታ ሞት ከተደሰቱት ከአይሁድ ጋር ነው።(ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 578)
ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም። ጸሎቱ ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃን፣ መልክአ ሕማማትና መዝሙረ ዳዊት ናቸው።
ስናጠቃልለው የተከለከሉ ነገሮች ምን ምን ናቸው ካሉ፡
1. መሳሳም
2. ሩካቤ ሥጋ ማድረግ
3. መስቀል ማሳለም እና መሳለም
4. ክርስትና ማስነሣት
5. ለሙታን ፍትሐት ማድረግ
6. ክህነት መስጠት
7. የላመ የጣመ ምግብ መመገብ
8. መሳቅ መጫወት መጨፈር
9. አብዝቶ ጠግቦ መመገብ
10. መስከር ወዘተ ናቸው፡፡
ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሣዕና ይከናወናሉ፡፡
@Ethiopian_Orthodox
የሰሙነ ሕማማት ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ክንዋኔዎች:
፩. አለመሳሳም ፡- ከላይ እንዳየነው በሰሙነ ሕማማት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፣ መሳሳምን የትክሻ ሰላምታ መለዋወጥን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማግሰኞ መከሩ አልሰመረላቸውም፡፡ ምክራቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡ ስለዚህ አይሁድ እያንሾካሾኩ እንስቀለው ፤እንግደለው ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ በዘመነ ፍዳ ወቅት ሠላምና ፍቅር አለመኖሩን የሚገልፅልን በመሆኑ ያንን ለማስታወስ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡
፪. ሕፅበተ እግር፡- ጌታ በፍጹም ትህትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ህይወት ማሕተም የሆነውን ምስጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው። ጸሎተ ሐሙስ ሕፅበተ እግር ጌታችን በዚህ ዕለተ እናንተ ለወንድማችሁ እንዲሁ አድርጎ ለማለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡
፫. ጉልባን እና ቄጠማ ፡- ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጀና የጸሎት ሐመስ እለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብጽ ተሰደው በሚነጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካው ሊጥ እያጋገሩ ቂጣ መብላት ንፎሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓል ይታሰባል፡፡ [በጸሎተ ሐሙስ ዕለት በስፋት የምናየው ይሆናል።]
ቄጠማ (ቀጤማ)፡- በቀዳም ስዑር ቀሳውስቱን ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ አዋዲ/ እየመቱ "ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃደ" የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠ እና ትንሳኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመኑም ለቤተ ክርስቲን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ ቀጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሰሩበትን ድርጊት የሚያስተውስ ነው፡፡ በዚህ እለት ልብስ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲቆናትን ቄጠማ ተሸክመው ቃጭል ሲቃጭሉ መታየታቸው እለተ ትንሳኤውን ለምዕመናን ትልቅ ብስራት ነው።
ሰ) ድንግልናን ጠብቆ መኖር ጋብቻ ሳይዘገይ በጊዜው እንዲፈጸም ይገፋፋል፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ጤናማ ሰው የተቃራኒ ፆታ አቻውን የመሻት ዝንባሌ አለው። ታዲያ ይህ በውስጡ የሚገኝ ሩካቤ መሻትና ከጋብቻ በፊት የሚደረግ ሕገ ወጥ ሩካቤን ላለመፈጸም (ድንግልናውን ጠብቆ ለመኖር) የሚያደርገው ጥረት የሚታረቁለት ሲያገባ ብቻ በመሆኑ ድንግልናውን ጠብቆ እስከ ጋብቻ ለመቆየት ዓላማ ያለው ሰው በውስጡ ያለውን የፍትወት ግፊት ለማብረድ ሲል ቶሎ ብሎ ማግባት እንዳለበት ይሰማዋል፡፡
ድንግልናን ስለመጠበቅ ግድ የሌላቸውና ቅድመ ጋብቻ የሚደረግ ዝሙትን የተለማመዱ ሰዎች ግን ጋብቻን እንደ መታሰር ስለሚቆጥሩትና በውስጣቸው ያለውን የፍትወት ግፊት እንደ ፈቃዱ እያስተናገዱት በመሆኑ ወደ ጋብቻ የሚገፋቸው ውስጣዊ ኃይል ስለሚቀንስ ከማግባት ይቦዝናሉ። ስለዚህ በዘማዊያን ዘንድ ዘግይቶ ማግባት የተለመደ ነው፡፡ ድንግልናቸውን ጠብቀው የኖሩ ሰዎች ግን ወደ ጋብቻ ለማምራት ቆራጦች በመሆናቸው ውሳኔያቸው እጅግ ፈጣን ነው።
ጋብቻ ለመፈጸም የሩቅ ቀጠሮ ያላቸው ሰዎች እንኳን ከጋብቻ በፊት ምንም ዓይነት ሩካቤ ማድረግ እንደማይፈቀድላቸው ሲያውቁ የጋብቻ ቀጠሮአቸውን በማሳጠር የአግቡኝ ሮሮ የሚያሰሙት በዚህ ምክንያት ይመስላል።
ሸ) ከጋብቻ በፊት የሚደረግ ሩካቤ ሥጋ የጋብቻን ቀነ ቀጠሮ እንዲራዘም ከማድረጉም በላይ ለመለያየትም በር ከፋች ነው። የተጋቡ ሰዎች ሩካቤ ለመፈጸም የማይችሉበት ሁኔታ ሲፈጠር ለመለያየት እንደሚገፋፉ ሁሉ ያልተጋቡም ሰዎች ሩካቤ መፈጸማቸው እንዲለያዩ ዓይነተኛ ምክንያት ይሆናል።እንደ አምኖን የሚሹትን ሲያገኙ «ለዚህ ሴትነትሽ ነውን?» የሚሉ ወንዶች ቁጥር እጅግ በርካታ ነው። 1ኛ ሳሙ 13÷14-16
ቀ) አስቀድሞ የምንኩስና ዝንባሌ ያለው ስው ከጋብቻ በፊት ሩካቤ መፈጸሙ የበለጠ ወደ ምንኵስና እንዲገፋፋ ይሆናል፡፡ ይህ አካሄድ ግን ለፈተና የሚመጣ እንጂ ለመልካም አይደለም፡፡ በእግዘአብሔር ፈቃድ የሚሆን ምንኩስና አይሆንምና፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰው በመጀመሪያ የሥጋ ፈተና ጨርሶ የራቀለት ይመስልዋል።በመቀጠልም ቢመነኩስ ሥርየት እንደሚያገኝ ይሰማዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ ግን የሌላውን ሕይወት አበላሽቶ መመንኮስ እንደማይገባው ቢሰማው የተሻለ ነበር፡፡ ለራሱም ቢሆን ጣዕመ ዓለምን ባይቀምስ መልካም ነበር፡፡ ለምንኩስናውም ይረዳው ነበር:: ነገር ግን ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ሰይጣን በስሜት እየነዳ እንዲመነኩስ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ ከጋብቻ በፊት የሚፈጸም ሩካቤ በምንም መልኩ ጠቀሚ አይደለም:: ለምንኩስና መገፋፋቱም አሉታዊ እንጂ አዎንታዊ ገፅታው አይደለም።
በአጠቃላይ ከጋብቻ በፊት የሚደረግ ግንኙነትና ድንግልናን ማጣት በባልና በሚስት መካከል ደስታን፣ መተማመንን፣ ፍቅርን ይቀንሳል፡፡ መጸጸትንና ሰላም ማጣትን በመካከላቸው ይፈጥራል፡፡ ለልዩ ልዩ በሽታዎችና ላልታሰበበት እርግዝና ከዚያም አልፎ ለውርጃ ያጋልጣል:: ያለ ጋብቻ መዘግየትን ያመጣል:: አለመጽናት” አለመታገሥን፣ አለመታመንንና የመሳሰሉትን ያመለክታል:: ብዙ መንፈሳዊ ጸጋዎችንም ያሳጣል፡፡ ያለ አግባብ ለመመንኮስ ወይም ደግሞ ለባሰ የዝሙት ተግባር ሊገፋፋም ይችላል፡፡
በቀጣይ ምዕራፍ ስምንት ክፍል አምስት:
👉 ድንግልናን የሚያሳጡ አደገኛ ወቅቶች፣ቦታዎችና አጋጣሚዎች በሚል ይቀጥላል....
ለጥያቄና አስተያየት @Ethiopian_Orthodox_bot ተጠቀሙ።
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox