ethiopian_orthodox | Unsorted

Telegram-канал ethiopian_orthodox - የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

30344

በዚህ Channel ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ ፤ ቀኖና እና ትውፊት የጠበቁ ትምህርቶች ይተላለፉበታል፡፡ ለአስተያየት: ጥቆማና ጥያቄ በዚህ ያግኙን ☞ @Ethiopian_Orthodox_bot Buy ads: https://telega.io/c/Ethiopian_Orthodox

Subscribe to a channel

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ጥልን በመስቀሉ ገደለ

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

መስቀል
🌋✝

ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና ቸር አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ከሰማያዊ ክብሩ ወደ ምድር ወርዶ: በማሕጸነ ማርያም እግዝእት በኪነ ጥበቡ ተጸንሶ: በኅቱም ድንግልና ተወልዶ: በፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀብሎ:
¤ከግራ ቁመት:
¤ከገሃነመ እሳት:
¤ከሰይጣን ባርነት:
¤ከኃጢአት ቁራኝነትም አድኖናል::

=>+"+ እምእቶነ እሳት ዘይነድድ አንገፈነ +"+ እንዳለ ሊቁ::

+ምንም መስቀል በብሉይ የወንጀለኞች መቅጫ ሆኖ ቢቆይም እግዚአብሔር ለዓለም መዳኛነት የመረጠው ነውና ሕብረ ትንቢቶች ሲነገሩለት: በብዙ ሕብረ አምሳልም ሲመሰል ኑሯል:: ከተፈጥሯችን ጀምሮ ዓለም ራሷ አርአያ ትዕምርተ መስቀል ናት::

+እግዚአብሔር ለቃየን እንዳይገድሉት ከሰጠው ምልክት (ዘፍ. 4:15) ጀምሮ
¤ይስሐቅ ሊሰዋ የተሸከመው እንጨት (ዘፍ. 22:6):
¤ቅዱስ ያዕቆብ ያያት የወርቅ መሰላል (ዘፍ. 28:12):
¤ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች የባረከበት መንገድ (ዘፍ. 48:14):
¤ባሕረ ኤርትራን የከፈለችው የሙሴ በትር (ዘጸ. 14:15):
¤የናሱ ዕባብ የተሰቀለበት እንጨት (ዘኁ. 21:8) ጨምሮ በርካታ ምሳሌዎች ለቅዱስ መስቀሉ መኖራቸውን መተርጉማን ተናግረዋል::

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

መስከረም ፲
ጼዴንያ ማርያም


ጼዴንያ በምትባል ሀገር ማርታ የምትባል ደግ ሴት ነበረች፡፡ ይህች ደግ ሴት በቤቷ ትልቅ አዳራሽ ሠርታ እንግዶችን እንደ አባታችን አብርሃም ተቀብላ አብለታ አጠጥታ ማደሪያ ቦታም ሰጥታ ታስተናግድ ነበር፡፡ አባ ቴዎድሮስ የሚባል ኢትዮጵያዊ መነኩሴ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ መሽቶበት ከማርታ ቤት በእንግድነት አደረና ጠዋት ሊሄድ ሲነሣ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ሲነግራት ‹‹የእመቤታችንን ሥዕል ገዝተህ አምጣልኝ ዋጋውን ልስጥህ›› አለችው፡፡ እርሱም ‹‹ገንዘቡን ሥዕሉን ሳመጣልሽ ትሰጪኛለሽ›› ብሏት ሄደ፡፡ ኢየሩሳሌምም ደርሶ ቅዱሳት መካናትን ተሳልሞ ሥዕሉን ረስቶ ሳይገዛ ሲመለስ «አደራ ጥብቅ አይደለምን? ያቺ ሴት አደራ ያለችህን ለምን ረሳህ» የሚል ድምፅ ሰማ፡፡ በጣም ደንግጦ ተመልሶ ሄዶ ገዝቶ በረሃ በረሃውን መጓዝ ጀመረ፡፡ በመንገድም እየተጓዘ አንበሳ ሊበላው እየሮጠ ወደ እርሱ ሲመጣበት አየ፡፡ መነኩሴው አንበሳውን ከመፍራት የተነሣ ደነገጠ፣ ተንቀጠቀጠ ደንግጦ ቁሞ ሳለ ያች ሥዕል ከአንበሳው ጩኸት ሰባት እጅ በሚበልጥ አስፈሪ ድምፅ ጩሃ ተናገረች፡፡ ያን ጊዜ አንበሳው ደንግጦ ፈጥኖ ሸሸ፡፡ መነኩሴውም መንገዱን ቀጠለ፡፡ በመንገዱም ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ወጥተው ወንበዴዎች ሊቀሙትና ሊገድሉት ከበቡት፡፡ ከሥዕለ ማርያሟም እንደ መብረቅ ያለ ታላቅ ቃል ወጣ፡፡
ወንበዴዎችም እጅግ ፈርተው ሸሽተው ከጫካው ውስጥ ገቡ፡፡ ያም መነኩሴ እነኚህን የሚያስደንቁ ተአምራት በተመለከተ ጊዜ በልቡ «ለእኔ ረዳት ትሆነኝ ዘንድ ወደ ሀገሬ ይዣት እሄዳለሁ እንጂ ለላከችኝ ሴት አልሰጥም» ብሎ ወደ ሀገሩ ሊሄድ በመርከብ ተሳፈረ፡፡ በባሕር ላይም ሳለ ጽኑ ነፋስ ተነስቶ መርከቡን እየገፋ ማርታ ወዳለችበት ሀገር ወደ ጽዴንያ ዳርቻ አደረሰው፡፡ ማደሪያም ስለሌለው ወደ ደጓ ሴት ወደ ማርታ ቤት ከእንግዶች ጋር አብሮ ገብቶ አደረ፡፡ ሲነጋ ወጥቶ ሊሄድ ከደጃፍ ሲደርስ ደጃፉ ጠፍቶት ከአጥሩ ሲታገል ዋለ፡፡ ማርታም «አባቴ ያመመህ የደከመህ ትመስላለህ ዛሬ ደግሞ እዚህ እደርና ነገ ትሄዳለህ» አለችውና አደረ፡፡ በሁለኛውም ዕለት እንደ መጀመሪያው ቀን በሩን አልፎ መሄድ አቃተውና እዚያው ማርታ ቤት አደረ፡፡ በሦስተኛው ቀን መውጣት ፈልጐ አሁንም ከአጥሩ ጋር ሲታገል አይታ «አባቴ የሆንከው ምንድነው? እነሆ ዛሬ ሦስተኛ ቀንህ ነው» አለችው፡፡
መነኩሴውም «ይህችን ተአምረኛ ሥዕል አልሰጥም ብዬ ነው፡፡ እኔኮ ሥዕል ከኢየሩሳሌም ግዛልኝ ያልሽኝ መነኩሴ ነኝ» ብሎ ሥዕለ ማርያምን አውጥቶ ሰጣት፡፡ እርሷም እጅግ በጣም ተደስታ እግዚአብሔርን አመሰገነች፡፡ በሥዕሏም ፊት ሰግዳ ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም ምስጋናን አቀረበች፡፡ ተቀብላም ሥዕል ቤት አሠርታ በክብር አስቀመጠቻት፡፡ ይህችም ሥዕል ቅዱስ ሉቃስ የሳላት ናት፡፡ ሥጋ የለበሰች ትመስላለች፡፡ ከፊቷም ወዝ ይንጠባጠባል፡፡ በዚህችም ሥዕል ብዙ ተአምራት ተደረገ ሕሙማን ተፈወሱ፣ ዐይነ ስውራን ማየት ቻሉ፡፡ በዚያ ዘመን የነበረው ሊቀ ጳጳስ ተአምሯን ሰምቶ ሥዕሏ ወደ ማርታ ቤት የገባችበት ዕለት መስከረም ፲ ቀን እንዲከበር ሥርዓት ሠራ፡፡ ይህም በዓል በቤተ ክርስቲያናችን ሁልጊዜ ይከበራል፡፡
የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክ ፍቅሯን ጣዕሟን ታሳድርብን፣ ልጇ አምላካችን በጸሎቷ ይማረን!

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

እነርሱም በታላቅ ጉስቁልና ውስጥ እየኖሩ እያለ በአንዲት ዕለት የአገረ ገዥው ልጅ ለመታጠብ ወደ ውሽባው ቤት ገባ፡፡ በውሽባ ቤቱም የሰይጣን ኃይል ስለነበረበት የመኰንኑን ልጅ አንቆ ገደለው፡፡ የአገሪቱም ሰዎች ሁሉ ለሞተው የመኰንን ልጅ ሊያለቅሱ ሲሰበሰቡ ቅዱስ ዮሐንስም አብሮ ቆሞ ሲመለከት ሮምና መጥታ "በጌታዬ ልጅ ሞት ልትደሰት መጣህን" እያለች ረገመችው፡፡ እርሱም "አይዞሽ አትዘኚ" አላትና ወደ ሞተው ልጅ ቀርቦ በመስቀል ምልክት ካማተበበት በኋላ በፊቱ እፍ አለበት፡፡ የሞተውም ልጅ ድኖ ተነሣ፡፡ የሀገሪቱም ሰዎች እጅግ ደነገጡ፡፡ ሮምናም ደንግጣ "እግዚአብሔር የሚሉት አምላክ አንተ ነህን" ብላ ጠየቀችው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም "በፍጹም እኔ አምላክ አይደለሁም፣ እኔ የእርሱ አገልጋዩና ሐዋርያው ነኝ እንጂ" አላት፡፡ ሮምናም ስለበደለቻቸው በደል ሁሉ መሪር ዕንባን እያለቀሰች ይቅር እንዲሏት ለመነቻቸው፡፡ እነርሱም አረጋጉዋት፡፡ ከሕዝቡም ውስጥ ብዙዎቹ በጌታችን አመኑ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ሌሎች ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ ወንጌልን እየሰበከ ከጣዖት አገልጋዮች በቀር ሁሉንም አሳምኖ አጠመቃቸው፡፡ አገልጋዮችን ኤጲስቆጶሳትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ከሾመላቸው በኋላ ወደ ሌሎች አቅራቢያ አገሮች ሄደ፡፡

በመጨረሻም በከሃዲውና በጨካኙ በድምጥያኖስ ዘመን በጣዖት አምላኪዎች ተከሶ ለፍርድ ቀረበ፡፡ በፈላ ውኃ ካሠቃዩት በኋለ በፍጥሞ ደሴት አጋዙት፡፡ በዚያም ሳለ ራእዩን ተመልክቶ ጻፈው፡፡ ድምጥያኖስም ከተገደለ በኋላ ከግዞቱ ተመልሶ ሦስቱን መልእክታቱንና ቅዱስ ወንጌሉን ጽፏል፡፡ ጌታችንም አስቀድሞ ሞትን እንደማይቀምስ ለዮሐንስ ቃል ገብቶለት ነበርና (ዮሐ 21፡22) ጥር 4 ቀን እንደ ኤልያስና ሄኖክ ሞትን እንዳያይ ወደ ብሔረ ሕያዋን ወስዶታል።

ጌታችን ለዮሐንስ ያልነገረው እርሱም ያላስተማረው ምሥጢር የለም፡፡ ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር "በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ…" ብሎ የጌታችን ነገር ተመራምሮ ለመድረስ ሲል በመሀል መልአኩን በዮርዳኖስ ባሕር ላይ ሲሄድ አገኘው፡፡ መልአኩም የዮርዳኖስን ባሕር በእንቁላል ቅርፊት እየጨለፈ ወደ ውጭ ሲያፈስ ተመለከተው፡፡ ዮሐንስም ተገርሞ "ምን ማድረግህ ነው" አለው፡፡ መልአኩም "የዮርዳኖስን ባሕር ቀድቼ እየደፋሁ ልጨርሰው ነው" ሲለው ዮሐንስም መልሶ "ታዲያ በእንቁላል ስባሪ ነውን?" አለው፡፡ መልአኩም "አዎን" አለው፡፡ ዮሐንስም "በከንቱ ደከምክ" አለው፡፡ ይህን ጊዜ መልአኩም መልሶ "አንተስ እንጂ ደግሞ የአምላክን መገኘት፣ አኗኗሩንም ተመራምረህ በጥበብ ለማግኘት ብለህ 'በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ..' ብለህ ጀምረህ የለምን? አንተ ጌታን ተመራምረህ ካገኘህና ከደረስክበት እኔም የዮርዳኖስን ወንዝ በዚህ እንቁላል ቅርፊት ቀድቼ እጨርሰዋለሁ" አለው፡፡ ዮሐንስም ይህን ጊዜ ደንግጦ ዝቅ ብሎ "ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ…" ብሎ ሀሳቡን ለወጠና ሌላ ታሪክ ቀጠለ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ ወክሎ እመቤታችንን በአደራ የተቀበለ እርሱም ለመቤታችን በአደራ የተሰጠ ሲሆን እመቤታችንን ከወሰዳት በኋላ ለ16 ዓመት እየተንከባከበ ጠብቋታል፡፡ እናቱም በሕፃንነቱ ስለሞተች እመቤታችን ናት እየተንከባከበች ያሳደገችው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በመልኩም ከጌታችን ጋር ይመሳል ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሥዕል የመሳል ተሰጥኦም ነበረው፡፡ ጌታችን በተሰቀለበት ዘመን የነበረው ጢባርዮስ ቄሳር ልጁ በሽተኛ ነበር፡፡ የጌታችንን የማዳን ሥራ እየሰማ እነ ጲላጦስም ስለጌታችን የሚጽፉለትን ይሰማ ስለነበር ልጁን ከጌታችን መቃብር ላይ እንዲያኖሩለት ላከው፡፡ ልጁም ፈጥኖ ተፈወሰለት፡፡ ጢባርዮስ ቄሳርም በልጁ መዳን ምክንያት የጌታችንን ውለታ ማስቀመጥ ፈልጎ የጌታችንን ሥዕሉን የሚሥልለትን ሲያጠያይቅ ዮሐንስን አገናኙት፡፡ ዮሐንስም ጌታችንን ልክ በዕለተ ዓርብ እንደተሰቀለ አድርጎ በመሣል ለጢባርዮስ ቄሳር ሰጠው፡፡ ሲሥለውም በመጀመሪያ ጌታችንን ልክ እንደተሰቀለ አድርጎ ራቁቱን ነበር የሳለው፡፡ ዮሐንስ የሳለው የጌታችን ሥዕልም አፍ አውጥቶ "በመጀመሪያ አይሁድ በኢየሩሳሌም ራቁቴን ሰቀሉኝ፣ አሁን ደግሞ አንተ ድጋሚ በሮም ራቁቴን ትሰቅለኝን?" ብሎ ተናገረው፡፡ ዮሐንስም እጅግ ደንግጦ "እንዴት አድርጌ ልሳልህ?" ብሎ የሳለውን ሥዕል ቢጠይቀው ሥዕሉም "ከለሜዳ አልብሰህ ሳለኝ" አለው፡፡ ዮሐንስም እንዳለው ከለሜዳ አልብሶ ከሳለው በኋላ ሥዕሉን ትኩር ብሎ ተመልክቶ ቢስመው ከንፈሩ አንድ ቀን ተኩል ያህል ተጣብቆ ቆይቷል፡፡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምባቸውን የጌታችንን ስነ ስቅለት የሚያሳዩ ሥዕሎች መገኛቸው ይህ ወንጌላዊው ዮሐንስ የሳለው ሥዕል ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በተለያዩ ስሞች ይጠራል፦
👉በሕይወቱና በኑሮው ሁሉ ጌታችንን ለመምሰል ይጥር ነበርና ጌታችንም እጅግ ይወደው ስለነበር "ፍቁረ እግዚእ" ተባለ፣
👉 የታላቁ ያዕቆብ ታናሽ ወንድም ስለሆነና አባቱም ዘብድዮስ ስለሚባል "ዮሐንስ ወልደ ዘብድዮስ" ተባለ፣
👉ለጌታችን ባለው ቅናትና ከወንድሙ ጋር ሆነው ባሳዩት የኃይል ሥራ እንዲሁም የጌታችንን አምላክነት በመግለጡ "ቦአኔርጌስ ወይም ወልደ ነጎድጓድ" ተብሏል:
👉ነገረ መለኮትን ከሌሎቹ በበለጠ ሁኔታ አስፍቶና አምልቶ በማስተማሩ "ነባቤ መነኮት ወይም ታዖሎጎስ" ተብሏል።
👉ኃላፊውንና መጻዒውን ጊዜ በራእዩ ስለገለጠ "አቡቀለምሲስ" ተባለ፣ ይህም በግሪክኛ ባለራእይ ማለት ነው፡፡
👉የጌታችንን መከራ መስቀሉን እያስታወሰ ፸ ዘመን ሙሉ እያለቀሰ ስለኖረና ፊቱም በሀዘን ስለተቋጠረ "ቁጹረ ገጽ" ተብሏል፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ በረከቱ አይለየን!

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

"በምድረበዳው... መጥምቁ ዮሐንስ እርሱ ነው"

ዘማሪ ዲያቆን ዮሐንስ በላቸው

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

መስከረም ፪
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ

መስከረም ሁለት በዚህች ቀን የካህኑ የዘካርያስ ልጅ የከበረ አጥማቂው ዮሐንስ ሕግን አፍራሽ በሆነ በንጉሥ ሄሮድስ እጅ ሰማዕት ሆነ።

ይህም እንዲህ ነው በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ነቢዩ ዮሐንስ በገሠጸው ጊዜ ፊልጶስ ወንድሙ ስለሆነ ቅዱስ ዮሐንስም የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም ይለው ነበርና።

ቅዱስ ዮሐንስም ሄሮድስን የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ስለማግባቱና ሌላም ያደርገው ስለነበረ ክፉ ሥራ ሁሉ ይገሥጸው ነበር። ደግሞም በተግሣጽ ላይ ተግሣጽን ጨመረ። ስለዚህም ዮሐንስን ተቀየመውና በግዞት ቤት አኖረው።

ሄሮድስም ዮሐንስን ይፈራው ነበር ጻድቅ ቅዱስ ሰው እንደሆነ ያውቅ ነበርና ብዙ ይጠባበቀውም ነበር። ሄሮድስ የተወለደባትን ቀን በዓል የሚያከብርባት ዕለት ነበረች መኳንንቱን አለቆቹን መሣፍንቱን ሹሞቹን በገሊላ አገር ያሉትን ታላላቅ ሰዎች ግብር አገባ።

የሄሮድያዳ ልጅም ወደ አዳራሹ ገብታ ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው ከእርሱ ጋር በማዕድ የነበሩትንም ንጉሡም ያቺን ብላቴና የምትሺውን ለምኚኝ እሰጥሻለሁ አላት። እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስም ቢሆን የለመነችውን ሊሰጣት ማለላት።

ወጥታም እናቷን ምን ልለምነው አለቻት እናቷም የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አለቻት። ያን ጊዜም እየሮጠች ወደ ንጉሡ ገብታ የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን እንድትሰጠኝ እሻለሁ ብላ ለመነችው። ንጉሡም ስለ መሐላው አብረውት ስለ ነበሩትም ሰዎች አዘነ እምቢ ሊላት ግን አልወደደም።

ያን ጊዜም ባለወጎችን ላከ በእሥር ቤትም ሳለ የዮሐንስን ራስ ቆረጡ ራሱንም በወጭት አምጥተው ለዚያች ብላቴና ሰጡአት እርሷም ወስዳ ለእናቷ ሰጠች። በዚያችም ቀን የቅዱስ ዮሐንስ ራስ ከሄሮድያዳ ከእጆቿ ላይ ወደ አየር ስለ በረረች ታላቅ ድንጋፄ ሆነ።

ደግሞም ሄሮድስ ሆይ የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም እያለች በመጮኽ ዘልፋዋለችና። ደቀ መዛሙርቱም በሰሙ ጊዜ መጥተው በድኑን ወስደው ቀበሩት።

©ስንክሳር

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼
"ወትባርክ፡አክሊለ፡ዓመተ፡ምሕረትከ፡ወይጸግቡ፡ጠላተ፡ገዳም"
             መዝ ፷፬÷፲፩    
 "በቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ  ምድረ በዳዎችም ጠልን ይጠግባሉ።"
            መዝ 64÷11         

ዐውደ ዓመት ለባርኮ ባርኮ ዐውደ ዓመት:
ንዒ ማርያም ለምሕረት ወሣህል።
           ~~~
እሰይ ደስ ደስ ይበላችሁ ደስ ደስ ይበላችሁ:
ቅዱስ ዮሐንስ መጣላችሁ ደስ ደስ ይበላችሁ።

እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ አሸጋገራችሁ አሸጋገረን::                                  
 
          
    መልካም አዲስ ዓመት!
       🌼እንቁጣጣሽ🌼                                        
         
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox                              
🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼🌼

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

“ይሄን የምናገረው የሰልጤ ሕዝብ እንዲሰሙት ነው። ከዚህ በኃላ በስልጤ ዞን በእሳት ቤተ ክርስቲያንን እያነደዱብን፣ እኛ መልሰን ስንሰራ የምንኖርበት መንገድ አይኖርም። ሕዝባችንና ታቦታችንን ይዘን ከተማቸውን ለቀንላቸው እንወጣለን መልሹ ግን ከባድ ነው።

የስልጤ ሕዝብ ከ100/60 % ባልተወለደበት ቀዬ በሌላ ቦታ በሰው ሀገር እየነገደ እየሸጠ እያተረፈ፣ መንገድ እየዘጋ እየሰገደ ሃይማኖቱ ተከብሮለት የሚኖረ ሕዝብ ነው። የስልጤ ሕዝብ በዛ በኔ ተወለደኩበት በሚለው ቀዬ ግን? ቤተ ክርስቲያን አናስነድድም የሚሉ የክርስቲያኖችን መኖሪያ ቤትና ሱቅ መርጦ ያቃጣላል። ከእንግዲህ ግን ክርስቲያኖችን ማሳደድ ዋጋ ያስከፍላል።

እደግመዋለሁ ይሄን የምናገረው የሰልጤ ሕዝብ እንዲሰሙት ብዬ ነው። ከዚህ በኃላ ቤተ ክርስቲያን አዋጅ ታውጃለች ከስልጤ ሱቅ የሚገዛውን ቤተ ክርስቲያን ካወገዘች እንዲሁም በተከታታይ ሌላ እርምጃም ከወሰደች የማይወጡት አደጋ ውስጥ ነው የሚገቡት።

ቤተ ክርስቲያን ያቃጥላሉ በሳምንቱ ሽማግሌ ይልኩና እንታረቅ ብለው እግር ላይ የወድቃሉ፣ መልሰው ግፋቸውን በደላቸውን ቤተ ክርስቲያን ላይ ግን ደጋግመው ይፈጽማሉ። ከዚህ በኃላ እንደ በፊቱ የምንታገስበት አይደለም። እርምጃው ከባድ ነው። አፀፋው ከባድ ነው።

መንግስትም ቢሆን ግብር የሚከፍል ሕዝብ ነው፣ ለምንድነው ደኅንነቱን የማያስጠብቅለት? ቤቱ በእሳት ሲነድ የሕፃናት ጡጦን እና ልብስ እንኳን መያዝ ያልተፈቀደለት መከረኛ ሕዝብ እያለ መንግስት ለሞሮኮ የሐዘን መግለጫ ይልካል።

ከዛሬ 18 ወራት በፊት በአንድ ጀንበር አምስት ዓብያተ ክርስቲያናት ከነ ሙሉ ነዋየ ቅዱሳቱ ነበር ያነደዱብን። አሁን ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን አናስነካም ያሉ ምእመናንን ምክንያት በመፍጠር ሱቃቸውንና ቤታቸውን ከነ ሙሉ እቃቸው አንድደውባቸው የለበሱትን ልብስ ብቻ ይዘው ነው የወጡት። በስልጤ ዞን የሚኖሩ ክርስቲያኖች ወንጀላቸው ክርስቲያን መሆናቸው ማኅተም ማድረጋቸው ብቻ ነው። በስልጤ ዞን ቤተ ክርስቲያን ስደት ላይ ነች እንደ ታቦተ ጺዮን የስልጤ ማርያምን ይዘው ቡታጅራ ማርያም በጥገኝነት ተቀምጠው እየፀለዩ ነው ያሉት።”
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ
የከምባታ ሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ይህች ቤተ ክርስቲያንም ከመሰረቷ አናወጻት፡፡ ያን ጊዜ ትልቁም ትንሹም ወንዱም፣ ሴቶችም፣ የተሾሙ ዲያቆናት፣ ካህናት፣ ሕዝቡም ሁሉ ደነገጡ ታወኩ፡፡ አሣ አንበሪው ግን መንቀሳቀሱን አልተወም፡፡ በመንቀሳቀሱም የቤተ ክርስያኗ ሕንፃ እኩሌታ ይሰነጠቅ ዘንድ ጀመረ፣ ምድርን ተናወፀች፣ ንጉስና፣ ሊቀ ጳጳሳቱም፣ ካህናቱም፣ ዲያቆናቱም፣ ህዝቡም፣ ሁሉም ካሉበት በባህሩ ወደብ ከተሰራች ከዚህች ቤተ ክርስቲያን መናወጥ የተነሳ ፍርሃት መንቀጥቀጥ በላያቸው ወረደ፡፡ ያ አንበሪ ግን በባህሩ ውስጥ ወደፊት መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗም በጀርባው ላይ ነበረች፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የሉትም ሁሉ ያ አሳ አንበሪ ወደ ባሕሩ ውስጥ ሊያሰጥመን ነው ሲሉ አሠቡ፡፡ ያን ጊዜም በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ስዕል ፊት በጽኑ አለቀሱ፡፡ በአንድ ቃልም "ገናናው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ሆይ ርዳታህ ፈጥኖ ይደርስልን ዘንድ በቅድስት ቤተክርስቲያን ወደተሰበሰብን ወዳጆችህ ተመልከት" እያሉ ይጸልዩ ጀመር፡፡ ያንጊዜም የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ከሰማይ ወርዶ ያችን ቤተክርስቲያን በብሩሃት ክንፎቹ እንደደመና ጋረዳት፡፡ በእጁ በተያዘ የብርሃን በትረ መስቀሉ ያን ኣሣ አንበሪ ወገቶ "በኢየሱስ ክርስቶስ ሃይል ከቦታህ ሳትንቀሳቀስ እስከትውልድ ፍፃሜ ዘመን ለዘለአለም ትኖር ዘንድ አዝዝሃለሁ" አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ሊቀመላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያኗን ከነመዓዘኗ ከግርግዳዎቿ ከመሠዊያዋ በውስጧ ተተክለው ካሉት ሁሉ ጋር ከጀርባው ላይ እያለች ያንን አሳ አንበሪ ወግቶ በያዘበት ብርሃናዊ በትረ መስቀሉ ወደቀድሞው የባሕሩ ወደብ ጎተተው፡፡ ያንጊዜም ግንቡ ቦታውን ሳይለቅ እርስ በእርሱ ተጣበቀ፡፡

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ዓሣ አንበሪውን በቀድሞ ሥፍራው ያቺን ቤተክርስቲያን በቀደመ መሠረቷ ላይ አጽንቷቸዋልና፡፡ ሊቀመላእክት ቅዱስ ሩፋኤልም አዳኝ የሆነ የጌታው የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ጠርቶ ከሞት እንዳዳናቸው ሁሉም አስተዋሉ፡፡ በድንቅ ተዓምራቱ የዳኑ ንጉሡና ሕዝቡም ሁሉ በሊቀመላእክቱ ቅዱስ ሩፋኤል ላይ አድሮ ድንቅ ተዓምራቱን ስለገለጸላቸው የቅዱስ ሩፋኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ የዚህች ቤተክርስቲያን ታሪክም በዓለም ሁሉ በየአውራጃዎቹም ተሰማ፡፡ የቅርብም የሩቅም ሰዎች ሁሉ ተሰብስበው ታላቁ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል የለመኑትን ሁሉ ያደርግላቸው ዘንድ የነገሩትን ያማልዳቸው ዘንድ በውስጧ ይጸልያሉ፡፡ በዚችም ቤተክርስትያን ብዙ ውስጥ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራት ተደረጉ፡፡ ታኅሣሥ 13 ቀንም ተአምራቶቹ ከተፈጸመባቸው ዕለታት አንዷ ናት፡፡ ቅዳሴ ቤቱም በዚሁ ዕለት ተከናውኗል፡፡

በዚኽች ዕለት ታስበው የሚውሉት ቅዱሳን የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል፣ የካህኑ መልከጼዴቅ፣ የአቡነ ሰራጵዮን ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

"አባ አቡነ.. አባ ተክለሃይማኖት"
በሊቀ መዘምራን ኪነጥበብ ወ/ቂርቆስ

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ

በዚህች ቀን ደግሞ ኢትዮጵያዊት የሆነች ተጋዳይ የከበረች ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው፡፡ በሸዋ ከፍለ አገር በቡልጋ አውራጃ ልዩ ስሟ ቅዱስ ጌዬ የተባለች አገር ነበረች ይህችም የእናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የትውልድ አገሯ ናት። በዚህም አገር በወርቅና በብር በሐር እና በልዩ ልዩ ልብስ በወንድና በሴት አገልጋዮች በፈረስና በበቅሎ የከበረ አንድ ስሙ የታወቀ ሰው ነበር። የዚህ ሰው ስሙ ቅዱስ ደረሳኒ ሲሆን የሚስቱም ስም ቅድስት ዕሌኒ ይባላል ሁለቱም ባልና ሚስቱ እግዚአብሔር የሚፈሩ ደጋግ ሰዎች ስለነበሩ በጎ ሥራቸው በዓለም ሁሉ የታወቀ ነበር። እሊህም ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ የተመረጠችና የከበረችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን ወልደው በደም ግባቷና በጠባይዋ እየተደሰቱ አሳደጓት ከዚያም የእግዚአብሔርን ሕግጋትና ሥርዓቶችንም ሁሉ አስተማሯት። ባደገችና ለአቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ የንጉሥ ባለሟል የሆነ ትውልዱ፤ ነገዱ ከአባ ፃሠርጓ ወገን የሆነ ለኢየሱስ ሞዓ ልጅ ለሠምረ ጊዮርጊስ በሕግ አጋቧት። እሱም በዚህ ዓለም ገንዘብ በጣም የከበረ ከመሆኑም በላይ በይበልጥ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ነበረ። ከደም ግባቷ የተነሣ ሙሽራይቱ ማለት እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን እጅግ አድርጎ ወደዳት። አሟቷ ኢየሱስ ሞዐም ይህች ብላቴና "በታላቅ ቁም ነገር የተመረጠች ነች" በማለት ትንቢት ይናገርላታል ስለዚህ እንደ እመቤቱ አድርጐ ያከብራት ነበር። ከዚህም በኋላም ለሕጋዊ ባሏ ለሠምረ ጊዮርጊስ ዓሥራ አንድ ልጆች ወለደችለት ከነዚህም መካከል ዘጠኙ ወንዶች ሁለቱ ሴቶች ነበሩ። ልጆችዋንም ሕገ እግዚአብሔርን እያስተማረች በክብር በሥርዓት አሳደገቻቸው።

በዚያን ዘመን የእግዚአብሔር ባለሟል የሚሆን ዓፄ ገብረ መስቀል የሚባል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበር። እርሱም ዝናዋን ሰምቶ ሥነ ምግባሯን ተመልክቶ ይልቁንም በሷ ላይ ያደረውን ኃይለ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ስለገለጸለት እጅግ አድርጐ ይወዳትና ያከብራት ነበር። ከዕለታት ባንድ ቀን በጸሎትሽ አስቢኝ በማለት በራሱ በንጉሡ ቤተ መንግሥት ከሚያገለግሉ አገልጋዮች ወይም ሠራተኞች መካከል እንዲያገለግሏት 174 አገልጋዮች ላካላት። ዳግመኛም ፈረስና በቅሎ ከነሥራታቸው እንደዚሁም ለነሥታት ሚስቶች የሚገባ ከሐርና ከወርቅ የተሠራ ልብስና የወርቅ ጫማ ላከላት። ነገር ግን እሷ ይህን ሁሉ ክብር አልፈለገችም ይልቁንም ለዓላማየ ዕንቅፋት ወይም ከንቱ ውዳሴ ይሆንብኛል በዚያውስ ወርቁ ጌጡ ልብሱ ተሸጦ ለነዳያን ይመጸወታል ለቤተ ክርስቲያን መባዕ ይሰጣል እኒህን አገልጋዮች ግን ምን አደርጋቸዋለሁ በማለት ወደ እግዚአብሔር እያመለከተች ቆየች።

ከአገልጋዮችዋ መካከል ምግባሯ የከፋ የምታናድዳትና የምታበሳጫት አገልጋይ ነበረች። ከዕለታት በአንድኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ በጣም ተበሳጨችና በዚያች አገልጋይ አፍ ውስጥ የእሳት ትንታግ ጨመረችባት።  ያም እሳት ትንታግ በአገልጋይዋ ጉረሮ ድረስ ዘለቀና ገደላት። በዚህን ጊዜ ቤተሰቦችዋ መጥተው የአገልጋይቱን አስከሬን ወደሌላ ክፍል ወሰዱት። ብፅዕት ክርስቶስ ሠምራም ደንግጣ ካለችበት ቤት ውስጥ ወደ ሌላው ክፍል ገባችና ወደ ሰማይ አቅንታ "ወይኔ ወዮልኝ ወዮታ አለብኝ የካህን ሚስት ስሆን ነፍስ ገዳይ ሆኛለሁና። ሰውስ ምን ይለኛል ለነፍሴስ ምን እመልስላታለሁ ከእግዲህ ከክርስቲያን ወገን ልቆጠር አይገባኝም በደሌንስ እንደምን አድርጌ ልሸሸሽጋት እችላለሁ" እያለች አለቀሰች።

ከዚህ በኋላ እንዲህ ስትል ለእግዚአብሔር ብፅዓት አደረገች "አቤቱ ይህችን በእኔ እጅ የሞተችውን አገልጋይ ነፍስዋን ከሥጋዋ አዋህደህ ብታሥነሣልኝ ልጆቼን ቤቴን ንብረቴን ትቼ ባለ ዘመኔ ሁሉ አንተን እከተላለሁ። አንተን ከመከተል ከቶ ወደኋላ አልልም። ለሰውነቴ ጌጥ ወይም ግርማ ሞገስ የሚሆናት ወይም የሚሞቃት ልብስ ከቶ አልለብስም ሥጋዬን የሚያረካ ምግብም አልመገብም። አቤቱ ጌታዬ ሆይ ጸሎቴን ስማኝ ልመናዬም በፊትህ ፈጥኖ ይድረስ አቤቱ ፊትህን ከኔ ከባሪያህ አትመልስ"። እንዲህ እንዲህ እያለች በልቅሶና በኀዘን ለብዙ ሰዓት ከጸለየች በኋላ ድካም ተሰማትና ዕረፍት አደረገች። ከዚህ በኋላ ቤተሰቦችዋ እስዋ ወዳለችበት ክፍል መጥተው "እመቤታችን ሆይ ሙታ የነበረችው አገልጋይሽ በእግዚአብሔር ኃይልና በአንቺ ጸሎት ተነሥታለችና ደስ ይበልሽ" አሏት። በዚህ ጊዜ ፈጥና ተነሥታ ደስ እያላት ሙታ የነበረችው አገልጋይ ካለችበት ቦታ ደረሰችና ሕይወት አገኘቻት ከዚያም ቃሏን ከፍ አድርጋ "ልመናዬን ቸል ያላለ ቸርነቱንም ከኔ ከባሪያው ያላራቀ ፈጣሪ ይክበር ይመስገን" ብላ በታላቅ ምስጋና እግዚአብሔር አመሰገነች።

ከዚህ በኋላ አስቀድሞ ከአፏ የወጣውን ከአንደበቷ የተነገረውን ቃል አስባ ልብሰ ምንኵስናዋን ማለት ቆቧን ቀሚሷን አጽፏን መታጠቂያዋን አዘጋጀች። ቤተሰቦቿና አገልጋዮቿም "እመቤታችን ሆይ ይህ የምታዘጋጂው የምናኔ ልብስ ለምንሽ ነው ወይስ ለማን ነው የምታዘጋጂው" አሏት። እርሷም " ሃይማኖት ያስተማሩኝ አባቴ ልብስ አልቆባቸዋል ሲሉ ሰምቼ ለሳቸው ነው የማዘጋጀው" አለቻቸው።

ከዚህም በኋላ ከዕለታት ባንደኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ አገልጋዮቿን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄድ ዘንድ ተዘጋጁ አለቻቸውና እነሱም አሺ በጎ ብለው አጅበዋት ወደቤተ ክርስቲያን ሄዱ። ከዚያም እንደደረሱ "በሉ እንዲህ እኔ ከዚህ ጥቂት እቆያለሁና እናንተ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ ለኔ ይህች አንድዲት አገልጋይና ይህ ሕፃን ልጅ ብቻ ይበቁኛል አለቻቸው። በዚያኑ ጊዜ አገልጋዮቿ እጅ እየሱ ወይም እየተሰናበቱ ወደቤታቸው ተመለሱ። ከዚያም ከዳዊት መዝሙር "ልቤ ጽኑ ነው አቤቱ ልቤ ጽኑ ነው እግዚአብሔርን ፈጽሜ አመሰግነዋለሁ እግዚአብሔር የደህንነቴ መብራት ስለሆነ ምን ያስደነግጠኛል እግዚአብሔር የሕይወቴ መተማመኛ ነው ምንስ ያስፈራኛል የሚለውን እየጸለየች የሚያልፈን ዓለም በማያልፈው ዓለም ለመተካት ወይም ለመለወጥ አውጭኝ እግሬ ብላ ገሠገሠች። ያ በልስላሴና በእንክብካቤ የኖረ እግር ከመንገዱ ብዛት እንደዚሁም ከቅርቅፍቱና ከእንቅፋቱ የተነሣ ፈለግ ሲያወጣ ሥጋውን እየቆረጠች ስትጥለው ደሙ እንደጒርፍ ውሃ ይወርድ ነበር። ያች የተከተለቻት አገልጋይ ግን ከእመቤቷ እግር እየተቆረጠ የሚወድቀውን የአካል ቊራጭ እያነሳች በልብሷ ትቋጥረው ነበር። በዚህ ዓይነት ችግርና ፀሐይ ሐሩር የብዙ ጐዳና ጉዞ ተጉዛ ከአሰበችበት አገር ደረሰች። በደብረ ሊባኖስ አቅራቢያ ወይም አካባቢ ስትደርስ የራስ ፀጒራን ይዛው በነበረ ምላጭ ላጨች ልብሷንም አውልቃ ለነዳያን አከፋፈለች የያዘችውንም ገንዘብ በመንገድ ላይ ላገኘችው ሁሉ መፅውታ ጨረሰች። ከዚያም አስቀድማ ያዘጋጀችውን ልብስ ምንኵስና ማለት ቀሚስዋን አጥልቃ አጽፋን ተጐናጽፋ ቆቧን ደፍታ ደብረ ሊባኖስ ከሴቶች ገዳም ደረሰች። የገዳሙ መነኰሳትም በታላቅ ክብር ተቀብለው ወደበዓታቸው አስገቧት ...

እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ለሳጥናኤል ምሕረት እንደለመነች፦ ከዕለታት በአንድኛው ቀን እናታችን ክርስቶስ ሠምራ ጓንጉት በምትባል ደሴት ውስጥ ዓርብ ዕለት ከቀኑ በስድስት ሰዓት ላይ ስለሰው ልጆች ስትጸልይ ሣለ። ዓለሙ ሁሉ ከንቱ እንደሆነና የሰውም ልጅ ሕይወት እንደጥላ ኃላፊ ጠፊ መሆኑን ፈጽማ ተመለከተች። ነቢዩ ዳዊት "ሰው ከንቱ ነገርን ይመስላል ዘመኑ ወይም ሕይወቱ እንደጥላ ያልፋል" ሲል ተናግሯልና። ዳግመኛም "ሰው ክብር እንኳ ቢሆን ሊኖር አይችልም እንደሚጠፋ ወይም ማስተዋል እንደሌለው እንስሶች መሰለ...

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ነሐሴ ፳፬

ነሐሴ ሃያ አራት በዚህች ቀን ታላቅ የከበረ ሐዲስ ሐዋርያ አባታችን ተክለሃይማኖት አረፈ፣ የከበረች ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት

ነሐሴ ሃያ አራት በዚህችም ቀን ታላቅ የከበረ ሐዲስ ሐዋርያ የትሩፋትም መምህር የሆነ አባታችን ተክለሃይማኖት አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ጸጋ ዘአብ የእናቱ ስም እግዚእ ኀረያ ነው እሊህም ቅዱሳን ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ብርሃንን ላበሩ ካህናት ከወገኖቻቸው የሆኑ ናቸው። እግዚእ ኀረያም መካን ስለሆነች ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እያዘኑ ሲጸልዩ ኖሩ።

በዚህም ነገር እያሉ የዳሞት ገዥ ሞተለሚን ሰይጣን አነሣሣው የሸዋን አውራጃዎች እስከ ጅማ እስከ ገዛ ድረስ። የሀገር መኳንንቶችም በየተራቸው ሚስቶቻቸውን ይሰጡታል። ከማረከውም ደምግባት ያላቸውን ሴቶች ያገኘ እንደሆነ ቁባቶች ያደርጋቸዋል።

በዚያም ወራት ወደ ጽላልሽ ደርሶ ብዙ ክርስቲያኖችን ገደለ ከእርሳቸውም የሚበዙትን ማረከ ጸጋ ዘአብም ከግድያ ፍርሃት የተነሳ ሸሸ አንድ ወታደርም ተከተለው እርሱም ወደ ባሕር ተወርውሮ ገባ በእግዚአብሔርም ፈቃድ በባሕሩ ውስጥ ተሸሸገ።

ሚስቱን እግዚእ ኀረያንም ወታደሮቹ ማረኳት ወደ ሞተለሚም አደረሷት ባያትም ጊዜ ውበቷንና ላህይዋን አደነቀ በልቡም እጅግ ደስ ብሎት ብዙ ሽልማትን ጌጥን ሰጥቷት በሽልማትና በጌጥ ሁሉ ሸለማት አስጌጣትም የጋብቻ ሥርዓትንም ማዘጋጀት ጀመረ ለሠርጉም እንዲሰበሰቡ ወደመኳንንቶቹ ሁሉ ላከ።

እግዚእ ኀረያም ይህን በሰማች ጊዜ ከአረማዊ ጋር አንድ ከመሆን ያድናት ዘንድ በብዙ ልቅሶ ወደ እግዚአብሔር ጸሎትን አደረገች። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በብርሃናዊ ክንፉ ተሸክሞ ከዳሞት አገር ወደ ምድረ ዞራሬ አድርሶ ወዲያውኑ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ በሴቶች መቆሚያ አቆማት። ባሏ ጸጋ ዘአብም ከማዕጠንት ጋራ በወጣ ጊዜ እንደተሸለመች ቁማ አያት አድንቆ በልቡ ይቺ ሴት ምንድን ናት ወደዚህስ ማን አመጣት አለ።

የማዕጠንቱንም ሥራ ጨርሶ ወጣ በጠየቃትና በመረመራት ጊዜ እርሷ ሚስቱ እግዙእ ኀረያ እንደሆነች አገኛት እርሷም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እግዚአብሔር ያደረገላትን ነገረችው።

ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ በአንዲት ሌሊት ተገለጠላቸው የዜናው መሰማት በዓለሙ ሁሉ የሚደርስ የተባረከ ልጅ ይወልዱ ዘንድ እንዳላቸው ነገራቸው አበሠራቸው።

ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ይህ ቅዱሱ ተፀንሶ በታኀሣሦ ወር በሃያ አራት ተወለደ በጸጋ ዘአብና በእግዚእ ኀረያ ቤታቸው ታላቅ ደስታ ሆነ ከዘመዶቻቸውና ከጐረቤቶቻቸው ጋራ ደስ አላቸው።

ለክርስትና ጥምቀትም በአስገቡት ጊዜ ፍሥሓ ጽዮን ብለው ሰየሙት። ሕፃኑም አደገ ድንቅ ተአምራትንም እያደረገ ዕውቀትንና ኃይልንም ተመልቶ በመነፈስ ቅዱስ ጸና።

ከዚህም በሗላ ዲቁና ይሾመው ዘንድ አባ ጌርሎስ ወደ ተባለ ጳጳስ ወሰዱት በዚያንም ዘመን በዛጔ መንግሥት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚን ነበር። ወደ ጳጳሱም በአደረሱት ጊዜ ይህ ልጅ የተመረጠ ዕቃ ይሆናል ብሎ ትንቢት ተናገረለት። የዲቁና ሹመትንም ተቀብሎ ወደ ሀገሩ ተመለሰ።

ጐልማሳ በሆነ ጊዜ አራዊትን ሊያድን ወደ ዱር ሔደ። ቀትር ሲሆንም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልኩ የሚያምር ጐልማሳ አምሳል በቅዱስ ሚካኤል ክነፍ ላይ ተገለጠለትና እንዲህ አለው ወዳጄ አትፍራ እንግዲህ የኃጢአተኞችን ነፍስ ወደ ሕይወት የምታጠምድ ትሆናለህ እንጂ አራዊትን የምታድን አትሆንም ስምህም ተክለ ሃይማኖት ይሁን እንደ ኤርምያስና እንደ አጥማቂው ዮሐንስ እኔ ከእናትህ ማኀፀን መርጬ አከብሬሃለሁና እነሆ በሽተኞችን ትፈውስ ዘንድ ሙታንንም ታሥነሣ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠሁህ ርኩሳን አጋንንትንም ከሁሉ ቦታ ታሳድዳቸዋለህ።

ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ገንዘብን ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በተነ ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጠፋ ለሰው ምን ይጠቅመዋል እያለ ቤቱን እንደ ተከፈተ ትቶ ምርኩዙን ይዞ በሌሊት ወጣ።

ከዚህም በኋላ ወደ ጳጳስ ሔዶ የቅስና ሹመት ተቀብሎ ለሸዋ አገር ሁሉ ወንጌልን መስበክ ጀመረ። ዐሥራ ሁለት ሽህ ሦስት መቶ ነፍስ ያህል አጠመቀ ለጣፆት የሚሠውበትን ሁሉ ሻረ በውስጡ የሚኖሩ አጋንንት እስከሸሹ ድረስ ዐፀዶቻቸውን ሁሉ ቆረጠ።

ሁለተኛም ወደ ዳሞት ምድር ሔዶ ብዙ ሟርተኞችንና አስማተኞችን ጠንቋዮችን አሳመነ ከሀዲ ሞተለሚም ብዙ ወራት ተቃወመው በጉማሬ ማጥመጃ ውስጥ በመጨመር ብዙ ጊዜ ወደ ገደል ወረወረው እርሱ ግን በደኀና ይመለሳል ደግሞ ሊወጋው ጦር ወረወረ ጦሩም ተመልሶ እጁን ወግቶ ተጠመጠመበት በተሠቃየም ጊዜ አባታችንን ለመነው እርሱም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሳምኖ አዳነው የተጠመጠመበትንም ጦር ፈታለት ቀናውን መንገድ የሚያጣምሙ ሟርተኞችንም አጠፋቸው።

ከዚህም በኋላ በክብር ባለቤት ጌታችን ስም ያደረገውን ድንቅ ተአምራቱን አይተው የአገር ሰዎች ሁሉም ከንጉሣቸው ጋራ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶላቸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት አስተማራቸው በቀናች ሃይማኖትም አጸናቸው ከዚህም ሁሉ ጋራ በጾም በጸሎት በስግደት ሁልጊዜ ያለ ማቋረጥ ተጠምዶ ይጋደል ነበር።

ዜናውንም ሰምተው ወደርሱ የሚመጡትን የነፍሳቸውን ድኀነት ያስተምራቸዋል የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችን ኢየሱስን በማመን ያጸናቸዋል።

ከዚህ በኋላ በኤልያስ ሠረገላ ተቀምጦ ወደ አምሐራ ሀገር ሔደ በገድል ተጸምዶ ወደሚኖር መነኰስ ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል በአንዲት ቀን ደርሶ በዚያ እንደባሪያ ሲያገለግል ኖረ በአንድነት የሚኖሩ መነኰሳትንም ያገለግላቸው ነበር የሞተውንም እስከማንሳት ድረስ ከደዌያቸው ይፈውሳቸው ነበር።

በዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ከሆነው በሗላ ሐይቅ በሚባል ቦታ ወደሚኖር ወደ ኢየሱስ ሞዓ የእግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው ሔዶ ከእርሱም የምንኲስና ልብስ ቀሚስና ቅናትን ተቀበለ። ከዚያም ወደ ደብረ ዳሞ ሔዶ ለአቡነ አረጋዊ አራተኛ ከሆነ ከአባ ዮሐኒ ዘንድ ቆብንና አስኬማን ተቀበለ። ሁለተኛም ወደ ኢየሩሳሌም ሒዶ ከከበሩ ቦታዎችና ከሊቀ ጳጳሳቱ ቡራኬን ተቀበለ።

በዚያም ወደ ሸዋ ምድር ተመልሶ የአባቱ ወንድም ልጅ የሆነ አባ ዜና ማርቆስን አገኘው በወግዳ በረሀም በአንድነት ኖሩ ከዚያም ግራርያ ወደ ሚባል አገር ሒዶ በኮረብታ መካከል ዋሻ አዘጋጅቶ ተቀመጠ በቀንም በሌሊትም ከዚያ አይወጣም ነበረ ከጥቂት ቅጠልም በቀር እህልን አይቀምስም መጠጡም ጥቂት ውኃ ነው።

ብዙ ወንዶችና ሴቶች ወደርሱ መጥተው መነኲሳቶች ሆኑ በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ መኝታ ላይ ተኝተው ያድራሉ እርስበርሳቸውም አይተዋወቁም እነርሱም እንደ ሕፃናት ናቸው በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜም በአንድነት ይቆማሉ በዘመኑ ሰይጣን ሰለ ታሠረ ወንዱ ሴቷን ሴት እነደሆነች አያውቅም እንዲሁም ሴቷ ወንዱን ወንድ እንደሆነ አታውቅም።

በዚህም በኋላ መጠጊያ ሠርቶ በፊቱ በሗላው በቀኙ በግራው የተሳሉ ፍላጻዎችን ተከለ ይህንም ማድረጉ በመደገፍና በመተኛት እንዳያርፍ ነው በዚያም እግሩ ከቅልጥሙ እስቲሰበር ሰባት ዓመት ቆመ። በዚያም ወራት ምንም የዕንጨት ፍሬ ወይም ቅጠል ሳይቀምስ ውኃም ሳይጠጣ ኖረ።

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ሥርዓተ ማኅሌት ዘነሐሴ ተክለሃይማኖት "ነሐሴ ፳፬"

ስምዓኒ እግዚኦ ጸሎትየ፡ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፡
ወይብጻሕ ቅድሜከ ገአርየ፡ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፡
ወኢትሚጥ ገጸከ እምኔየ፡ በዕለተ ምንዳቤየ አጽምእ እዝነከ ኀቤየ፡
ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፡ አመ ዕለተ እጼውአከ ፍጡነ ስምዓኒ፡
ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፡ ለዓለም ወለዓለመ ዓለም፡
ሃሌ ሉያ ዘውእቱ ብሂል፡
ንወድሶ ለዘሃሎ እግዚአብሔር ልዑል፡
ስቡሕ ወውዱስ ዘሣረረ ኲሎ ዓለመ፡ በአሐቲ ቃል።

መልክዐ ሥላሴ

ሰላም ዕብል ለንዋየ ውስጥ ምሕረትክሙ:
ትሩፋተ ገድል ኲኑኒ ሥላሴ አምጣነ ትሩፋት አንትሙ:
ሶበ ሖርኩሰ ከመ እሳተፍ ገድሎሙ:
ጊዮርጊስ ኢወሀበኒ መጠነ ነጥበ ጠል እምደሙ:
ወተክለሃይማኖት ከልአኒ ስባረ እምዐጽሙ፡፡

ዚቅ

ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ዘኢይነውም ትጉህ:
በውስተ ቅዱሳን ስቡሕ:
ከመ ቀስተ ደመና የዓውዶ ሱራሄ:
ሎቱ ለባሕቲቱ ይደሉ ስባሔ፡፡

ነግሥ

ሰላም ለዝክረ ስምኪ ዘመንክር ጣዕሙ:
ለወልድኪ አምሳለ ደሙ:
መሠረተ ሕይወት ማርያም ወጥንተ መድኃኒት ዘእምቀዲሙ:
ኪያኪ ሠናይተ ዘፈጠረ ለቤዛ ዓለሙ:
እግዚአብሔር ይትባረክ ወይትአኮት ስሙ፡፡

ዚቅ

አመ ኖኅ ይእቲ መድኃኒት
እንተ ኮነት አንቀጸ ሕይወት:
ማርያም ቅድስት፡፡

ወረብ

ማርያም ቅድስት አንቀጸ ሕይወት
አመ ኖኅ አንቀጸ ሕይወት
ማርያም ቅድስት/፪/ ይእቲ መድኃኒት
"እንተ ኮነት"/፪/አንቀጸ ሕይወት/፪/

መልክዐ ተክለሃይማኖት

ሰላም ለዝክረ ስምከ ዘጥንተ ፊደሉ መስቀል:
ስም ክቡር ወስም ልዑል:
ተክለሃይማኖት ማቴዎስ በዓለ ቀዳማይ ወንጌል:
ከመ እወድሰከ መጠነ አውሥኦተ እክል:
ማዕሠረ ልሳንየ ትፍታሕ ማርያም ድንግል።

ዚቅ

ወንጌለ መለኮት ሰበከ:
ስምዓ ጽድቅ ኮንከ:
ወበእንተዝ ተክለ ሃይማኖት ተሰመይከ፡፡

ወረብ

ወበእንተዝ "ተሰመይከ"/፪/ተክለሃይማኖት/፪/
"ስምዓ ጽድቅ ኮንከ"/፪/ተክለሃይማኖት/፪/

መልክዐ ተክለሃይማኖት

ሰላም ለአዕይንቲከ ዘአርያኣሆን ሐዋዝ:
እለ ጽዱላት እማንቱ ከመ ሠርቀ ቤዝ:
ተክለ ሃይማኖት ኅብአኒ እሞተ ኃጢአት አዚዝ:
ለከሰ አኮ ከመዝ:
ኢይረክበከ ሞት ዳግም እምዝ፡፡

አመላለስ

ዳግም እምዝ/፬/ ኢይረከቦ ሞት ለተክለ ሃይማኖት/፪/

ዓዲ ወረብ

"ዳግም እምዝ"/፪/ኢይረከቦ ከመዝ ሞት ለተክለ ሃይማኖት/፪/ ኢይረከቦ እምዝ ሞት ለተክለሃይማኖት/፪/

መልክዐ ተክለሃይማኖት

ሰላም ለኲልያቲከ ዘፈተኖን በትዕግስት:
ኢየሱስ ክርስቶስ አበ ብርሃናት:
ተክለ ሃይማኖት ሰጋዲ ከመ መላእክት:
ጸሎትከ ዘገበርካሃ እስከነ ኈልቊ ምዕት ዓመት:
መድኃኒተ ትኩነኒ እምግሩም ቅሥት፡፡

ዚቅ

ተክለ ሃይማኖት ሰማዕት ሰባኬ መድኃኒት:
ጸሎትከ ትኩነነ ፀወነ እመንሱት:
ተክለ ሃይማኖት ሰማዕት ሰባኬ መድኃኒት፡፡

ወረብ

ሰማዕት ሰባኬ መድኃኒት ተክለ ሃይማኖት/፪/
ጸሎትከ ትኩነነ "ፀወነ እመንሱት"/፪//፪/

መልክዐ ተክለ ሃይማኖት

ሰላም ለፀዐተ ነፍስከ በስብሐተ አዕላፍ እንግልጋ:
ለዓለም ዛቲ እምግብርናቲሃ ወጹጋ:
ተክለ ሃይማኖት ቶማስ ለመርአስ ዐቃቤ ሕጋ:
ለእለ ገብሩ ተዝካረከ እንዘ ሀለዉ በሥጋ:
ሀቦሙ እግዚእየ ሞገሰ ወጸጋ፡፡

ዚቅ

ወወጽአት መንፈሱ ሶቤሃ:
ወተቀበልዎ መላእክት በስብሐት ወበማኅሌት:
እንዘ ይብሉ ሃሌ ሉያ:
ወአብዕዎ ኢየሩሳሌም ሰማያዊተ፡፡

መልክዐ ተክለ ሃይማኖት

ሰላም ለበድነ ሥጋከ ኤልሳዕ መምህር ዘገነዛ:
በሠናይ ፄና መዓዛ:
ተክለ ሃይማኖት ሰባኪ ፊልጶስ ዘብሔረ ጋዛ:
ለሥጋየ መሬታዊት እመ የኀልቅ እዘዛ:
ስብረተ ዐፅምከ ይኩነኒ ቤዛ፡፡

ዚቅ

ሖረ ኀቤሁ ለተክለ ሃይማኖት ቀዲሙ ሌሊተ:
ኤልሳዕ ስሙ መልአኮሙ ለአርድዕት:
ውእቱኒ አምጽአ ከርቤ አፈዋት:
ገነዝዎ በሰንዱናት ለተክለሃይማኖት።

መልክዐ ተክለሃይማኖት

ሰላም ለግንዘተ ሥጋከ በዘቦቱ ይትመኀፀኑ:
ነገሥተ እስራኤል ኄራን ዘአስተሣነይዎ በበዘመኑ:
ተክለ ሃይማኖት ሠዋዒ ለእግዚአብሔር ካህኑ:
አድኀነኒ እምጸብአ ከይሲ ዘዐሥር ቀርኑ:
ወእምብእሲ ዘክልኤ ልሳኑ፡፡

ዚቅ

መላእክት አእመሩ ሃይማኖተከ:
ነገሥት ሐነፁ መካነከ:
አባ ተክለሃይማኖት ክርስቶስ ዘአፍቀርከ፡፡

መልክዐ ተክለሃይማኖት

ሰላም ለመቃብሪከ እምቅድመ ትኑም ውስቴታ:
ታቦተ ማርያም ድንግል ዘአንበርከ በውሳጢታ:
ተክለሃይማኖት አቡየ ለወልድከ ዕጓለ ማውታ:
ለበረከትከ ይከልለኒ ረድኤታ:
ወይዑደኒ ዘጽድቅከ ወልታ።

ዚቅ

ጸለየ ተክለ ሃይማኖት እንዘ ይብል ኀበ ተቀብረ ሥጋየ
ወተክዕወ ደምየ ህየ ይኩን በረከት፡፡

ወረብ

ጸለየ ተክለ ሃይማኖት እንዘ ይብል ኀበ ተክዕወ ደምየ/፪/
"ህየ ይኩን"/፪/በረከት/፪/

አንገርጋሪ

ሞቶሙሰ ለጻድቃን ሕይወቶሙ ውእቱ
እስመ ለጻድቅ ይትሌዓል ቀርኑ በክብር
ጻድቃን እለ አስመርዎ ለእግዚኦሙ
ምድረ ብርህተ ወጽዱተ ይወርሱ፡፡

አመላለስ፦

ገነተ ትፍሥሕት ኪያሃ አውረሶሙ
ወአቀቦሙ ከመ ብንተ ዐይን ለጻድቃን/2/
እለ ሎቱ ተቀንዩ በሕይወቶሙ/4/

ወረብ፦

አሜሃ ይቤሎ"እለ በየማኑ"/2/ /2/
ንዑ ለአቡየ ቡሩካኑ ለአቡየ ንዑ/2/

እስመ ለዓለም

ደሪዖሙ ተአጊሦሙ: መጠዉ ነፍሶሙ ለሞት:
እለ ሎቱ ተቀንዩ በሕወቶሙ:
እምፀሐይ ይበርህ ገጾሙ:
እለ አጥረይዋ ለትዕግስት:
እለ...: እፎ አምሰጥዎ ለመድብብ ከመ ይባዕዎ ለመርኀብ:
እለ...: ዕፎ አመሠጥዎ ለሞት: ዓደዉ እሞት ውስተ ሕይወት:
እለ...: እለ ጸውዖሙ ወይቤሎሙ: ንዑ ለአቡየ ቡሩካኑ:
እለ...: አመ ያቀውም አባግዐ በየማኑ: ወአጣሌ በጸጋሙ:
እለ...: አሜሃ ይቤሎሙ ለእለ በየማኑ: ንዑ ለአቡየ ቡሩካኑ: እለ...:ወያወርሶሙ ምድረ ሐዳሰ: እንተ ታውኀዝ ሀሊበ ወመዓረ: እለ...:ገነት ትፍሥሕት ኪያሃ አውረሶሙ ወዓቀቦሙ ከመ ብንተ ዓይን ለጻድቃን:
እለ ሎቱ ተቀንዩ በሕይወቶሙ፡፡

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

+ቅዱስ ዳዊትን የመሰሉ ነቢያት ደግሞ "ለሚፈሩሕ ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ምልክትን ሰጠሃቸው" እያሉ መስቀሉን ከርቀት ተመልክተዋል:: (መዝ. 59:4)

+በሐዲስ ኪዳን ግን ምሳሌው ገሃድ ሆኖ: ጌታ በዕፀ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ሥጋውን ቆረሰበት: ደሙን አፈሰሰበት: ዓለምንም አዳነበት:: ስለዚህም " መስቀል ብርሃን ለኩሉ ዓለም:  መሠረተ ቤተ ክርስቲያን" ተብሎ የሚመሰገን ሆኗል::

+ ቅዱስ ያሬድ ሊቁ አክሎ "መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር: ያድኅነነ እምጸር" ብሎ ጠላትን ማሳፈሪያ መሆኑን ይነግረናል::  ብርሃነ ዓለም  ቅዱስ ዻውሎስም ስለ መስቀሉ አምልቶ አጉልቶ አስተምሯል:: መመኪያችን ነውና:: (1ቆሮ. 1:18, ገላ. 6:14)

+አንዳንዶቹ እኛን 'የተሰቀለውን ትታቹሃል' ይሉናል:: የተሰቀለውማ የጌቶች ጌታ: የነገሥታት ንጉሥ: የአማልክት አምላክ: ሁሉ በእጁ የተያዘ: ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ከኦርቶዶክስ በላይ የሚያመልክ በወዴት አለና::

+ነገር ግን መስቀሉን ንቆ የተሰቀለውን ማክበር አይቻልምና እኛ ለመስቀሉ የጸጋ ስግደትን እንሰግዳለን: እናመሰግነዋለን: እናከብረዋለን: ቤዛ: ጽንዕ: መድኃኒት: ኃይል እያልንም እንጠራዋለን:: አባቶቻችን በመስቀሉ ምርኩዝነት ማዕበለ ኃጢአትን: ባሕረ እሳትን ተሻግረዋል::

+በመስቀሉ ቢመኩ አጋንንትን ድል ነስተዋል:: ጠላትንም አሳፍረዋል:: እኛም በመስቀሉ አምነን ከብረን: ገነን እንኖራለን:: ተጠቅመንበታልና ከራሳችን ሕይወት በላይ ምስክርን አንፈልግም::

+"+ በዓለ_መስቀል +"+

    በሃገራችን ኢትዮጵያ መስቀልን በሚመለከት ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ የደመራ መስቀል በዓል /መስከረም 16ና 17/ እንዲሁም መጋቢት 10 የመስቀለ ኢየሱስ በዓል ተያያዥነት ያላቸውና ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከጌታችን ሞትና ትንሣኤ በኋላ በቀራንዮ አደባባይ ጥቂት ጊዜ ከቆየ በኋላ ጌታችንን የገነዙት #ዮሴፍና #ኒቆዲሞስ ከቀራንዮ ወደ ጎልጎታ (ጌታችን ተቀብሮባት ወደነበረው መካነ መቃብር) ወስደው አኑረውታል፡፡

   አበው ሐዋርያት ወደየሀገረ ስብከታቸው ሲሄዱ የኢየሩሳሌሙ ጳጳስ ሐዋርያው #ያዕቆብ በኃላፊነት እንዲጠብቀው አድርገዋል፤ ከየአህጉረ ስብከታቸው ሲመለሱም በእግረ መስቀሉ ሥር እየተሰበሰቡ ይጸልዩ ነበር፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል #ማርያምም ጠዋትና ማታ በመስቀሉ ሥር ትጸልይ ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች ታሪኩንና ቦታውን በክርስቶስ ደም የተቀደሰውን ክቡር መስቀሉን ለማየት ያመኑትም በረከት ለማግኘት ከየአቅጣጫው ይመጡ ነበር፡፡ በመስቀሉ ተዓምራት ብዙዎች ከተለያዩ ደዌ /በሽታ/ ተፈውሰዋል፡፡ ይህም በጣም ብዙ ሰዎች ክርስቶስን ወደ ማመን ስቧቸዋል፡፡ ይህን ድንቅ ሥራ የተመለከቱ የክርስቶስ ሰቃዮች /ሰቃልያነ ክርስቶስ/ በሁኔታው ባለመደሰታቸው ሕይወት የሆነውን የጌታ መስቀሉን ከጎልጎታ አንስተው ቀብረውት #ለ300 ዓመታት ያህል የከተማው ጉድፍና ጥራጊ እየጣሉበት የተቀበረበት ቦታ ኮረብታ እስኪሆን ድረስ ቆይቷል ‹‹በቀራንዮ መካን ዘደፈኑ አይሁድ፤ መስቀልከ ዕፀ ሕይወት፥ ዕፀ መድኀኒት›› እንዲል፡፡ ሆኖም #በ4ኛው መ/ክ/ዘመን ለክርስቲያኖች ነፃነት የሚያስብና የሚያስከብር ንጉሥ በሮም ተነሣ፡፡ የንጉሡም ስም ቈስጠንጢኖስ ይባል ነበር፡፡ ይህ ንጉሥ ክርስቲያኖችን ይበልጥ እንዲወድ ያደረገው በጠላቱ በማክሴንዲዩስ (መክስምያኖስ) ላይ በዘመተበት ጊዜ ገና በጉዞ ላይ እያለ ‹‹በዝንቱ ትእምርተ መስቀል ትመውዕ ፀርከ (በዚህ የመስቀል ምልክት ጠላትህን ድል ታደርጋለህ)›› የሚል በመስቀለኛ ቅርፅ የተጻፈ ጽሑፍ በጠፈር ሰማይ አይቶ በመስቀል ምልክት #ድል በማድረጉ ነው፡፡

     የንጉሥ #ቈስጠንጢኖስ እናት ንግሥት #እሌኒ የመስቀሉ ፍቅር ያደረባት፥ ታሪኩ በውስጧ የሰረጸባት ቅድስት እናት ነበረች ቈስጠንጢኖስም በዘመነ መንግሥቱ በትዕምርተ መስቀል ብዙ የድል ሥራ ስለሠራ ለመስቀሉ ታላቅ አክብሮትና አድናቆት ነበረው፡፡ ንግሥት እሌኒም መስቀሉን ለማግኘት ሰው ብትጠይቅ የሚያውቅ አላገኘችም፡፡ በመጨረሻ ግን የመስቀሉ መውጣት የእግዚአብሔር ፈቃድ በመሆኑ ኪራኮስ የሚባል አረጋዊና መቃርስ የሚባል ኤጲስ ቆጶስ አገኘች፡፡ ከእነዚህም አረጋዊው ኪራኮስ ዕድሜው የሸመገለና በእስራኤል ባህልና ደንብ ያደገ ነበር፡፡ እሌኒም እሱን ጠይቃ መስቀሉን ለማግኘት እንዲተባበራት ጠየቀችው ሆኖም ሊተባበራት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ረሃብና ጽም ስታበዛበት ግን የረሃብና የጽሙን መጽናት ተመልክቶ ከእነዚህ ከሦስት ተራሮች አንዱ እንደሆነ ነገራት፤ ከሦስቱ ተራራ የትኛው እንደሆነ ለማወቅ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሱባኤ እንድትይዝ ነገራት፤ ሱባኤም ያዘች፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር #መልአኩን ልኮ እንዲህ አላት ‹‹አንቺም ሰውም በከንቱ አትድከሙ እንጨት አሰብስበሽ፥ ደመራ አስደምረሽ፥ በእሣት አያይዘሽ፥ በፍሕሙ ላይ ዕጣን አፍስሽ፤ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ አቅጣጫውን ተመልክተሽ ጢሱ ያረፈበትን ቦታ አስቆፍሪው›› አላት፡፡ እርሷም መልአኩ እንዳላት እንጨት አሰብስባ #ደመራ አስደመረች ዕጣንም አፈሰሰችበት #ጭሱም ሰማይ ደርሶ ቅድመ ሥላሴ ሰገዶ  ወደ ምድር ሲመለስ ቦታውን አመለከታት ይህም የሆነው #መስከረም_16 ቀን ነው፡፡ እኛ ደመራ ብለን የምናከብረው ይህን አብነት በማድረግ ነው፡፡

+"+ ቅዱስ_አውዶኪስ_ቀሲስ +"+

=>ይህ ቅዱስ ሰው ለቅዱስ መስቀሉ ከነበረው ፍቅር የተነሳ በብዙ ድካም ወደ #ኢየሩሳሌም በእግሩ ተጉዞ ነበር:: ከብዙ መንገደኞች ጋር በጐዳና ላይ ሳሉ ታዲያ አንድ አይሁዳዊ (ሰማርያዊ) ተቀላቀላቸው:: በወሬ በወሬ የት እንደሚሔዱ ሲጠይቃቸው "መካነ መስቀሉን ለመሳለም ወደ #ጐልጐታ ነን" አሉት::

+እሱ ግን ከት ብሎ ስቆ "እንዴት እንጨት ትሳለማላችሁ" በሚል አፌዘባቸው:: የፀሐዩ ሐሩር እጅግ ጠንቶ ነበርና ቅዱስ አውዶኪስ ኃይለ መስቀሉን ሊያሳይ ወደደ:: በመንገድም መርዝነት ያለው ውሃ ነበርና ቅዱሱ ቀርቦ ጸልዮ በመስቀሉ ባረከውና ፈጥኖ ወደ ጣፋጭነት ተቀየረ::

+ምዕመናኑ ደስ ብሏቸው ሲጠጡ ያ አይሁዳዊ 'እጠጣለሁ' ብሎ ቢቀርብ ወደ ነበረው ተመለሰበት:: 'በኮዳ የያዝኩትን እማልጠጣ' ብሎ ቢከፍተው ደግሞ ተልቶ አገኘው:: እጅግ ደንግጦ አለቀሰ:: በጣም ጠማው: ግን ምኑን ይጠጣ!

+አማራጭ ሲያጣ ወደ ቅዱስ አውዶኪስ ሒዶ እግሩ ላይ ወድቆ አለቀሰ:: በመስቀሉ ቢማጸን መራራው ጣፈጠለት:: በዚህ ምክንያትም ወደ ክርስትና ተመልሷል:: ቅዱሱ በመልካም ሽምግልና ሲያርፍ ውሃው የተቀየረበት ቦታ ላይ ቤተ መቅደስ ታንጾ በዚህ ቀን ተቀድሷል::

+"+ ቅድስት ታኦግንስጣ +"+

=>በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረችው ሮማዊቷ እናት መንገድ ላይ ቁማ ወንጌል ስታነብ በንጉሥ ወታደሮች ተማርካ ወደ ሕንድ ተወስዳለች:: በዚያም በመስቀል አማትባ ሙት በማስነሳቷ የሃገሩ ሰው ወደ ክርስትና ከነ ንጉሡ ተመልሰዋል:: እርሷም ገዳም አንጻ: ደናግሉን ሰብስባ በንጽሕና ኑራለች:: በዚህ ቀን ዐርፋ ሲቀብሯት የብርሃን መስቀል መቃብሯ ላይ ተተክሏል::

=>አምላከ ቅዱሳን በኃይለ መስቀሉ: በሞገሰ መስቀሉ ይጠብቀን:: ከበረከቱ አሳትፎ በዓሉን የሰላም ያድርግልን::

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

መስከረም ፬
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ

መስከረም አራት በዚህች ዕለት ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ከእናቱ ማርያም ባውፍልያ ከአባቱ ዘብዴዎስ የተወለደበት ዕለት እንደሆነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌልን ለመስበክ ዕጣ የደረሰው እስያ ስለነበር ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን አስከትሎ ሄደ፡፡ ይኽችውም ኤፌሶን በጥንቱ በታናሽ እስያ በዛሬው የቱርክ ግዛት ውስጥ ከተማ ናት፡፡ ዛሬ ኢያዞሎክ ተብላ የጥንት ታሪኳ ጠፍቷል፡፡ አስቀድሞ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ሰብኮባታል፡፡ ደቀ መዝሙሩን ቅዱስ ጢሞቴዎስንም በከተማዋ ላይ ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ እርሱም በግፍ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ቅዱስ ዮሐንስን እየረዳው በከተማዋ ብዙ አገልግሏል፡፡ በኋላ ግን በግፍ ገድለውታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ኤፌሶን ለመሄድ በመርከብ ሲሳፈር መርከቡ በማዕበል ተሰበረ፡፡ ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስን መዕበሉ ወደ አንዲት ደሴት አደረሰው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን በመርከቡ ስባሪ ተንጠልጥሎ በባሕሩ ማዕበል መካከል 40 ቀንና 40 ሌሊት ከኖረ በኋላ ማዕበሉ ተፍቶ አብሮኮሮስ ካለበት ደሴት አደረሰውና ተያይዘው ኤፌሶን ከተማ ገቡ፡፡ የከተማይቱም ሰዎች እጅግ ክፉዎች ስለነበሩ መጀመሪያ ላይ ቅዱስ ወንጌልን መስበክ አልቻሉም ነበር፡፡ እነርሱም እጅግ ክፉዎች መሆናቸውን ስላወቀ ቅዱስ ዮሐንስ ገና ዕጣው ሲደርሰው በሀዘን አልቅሶ ነበር፡፡ አሁንም ከተማው በገቡ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስ ምክንያት በመፍጠር ሮምና ለምትባል ሴት የውሽባ ቤቷ እሳት አንዳጅ ሆኖ አብሮኮሮስም ዕቃ አጣቢ ሆነው ተቀጠሩ፡፡ የቀጠረቻቸው ሴትም እጅግ ታሠቃያቸው ጀመር፡፡ ባሮቿ እንደሆኑ ተስማምተው ስለጻፉላት ትደበድባቸውም ነበር፡፡

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ዘከመ:መተሮ:ለዮሐንስ።

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ዐውደ ዓመት ለባርኮ

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ጳጉሜ ፫
ቅዱስ ሩፋኤል


ሰማያውያን ከሆኑ ከመላአክት አለቆች ከቅዱስ ሚካኤልና ከቅዱስ ገብርኤል ቀጥሎ 3ተኛ ነው፡፡ "ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” እንዲል፡፡ ጦቢት 12፡15፡፡ ሩፋኤል የሚለው የስሙ ትርጓሜ ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል መልአከ የሰላምና የጤና መልአክ ይባላል፡፡ በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ሆነ ቁስል ይፈወስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ “በሰው ቁስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው” መጽሐፈ ሄኖክ 6፡3፡፡

ቅዱስ ሩፋኤል የሰው ልጆች ከተያዙበት የኀጢአት ቁስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የማይለይ መልአክ ነው፡፡ “በበሽታ ሁሉ ላይ በሰው ልጆችም ቁስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡” በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል፡፡ ሄኖክ 10፡13፡፡ ለሴቶች ረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ በማኅፀን ላለ ችግርና ሴት በፀነሰችበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም፡፡ ሕፃኑ ዐርባ ቀን ሞልቶት በማሕፀን እያለ ማለትም በሥላሴ አርአያ መልኩ መሳል ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል አይለየውም፡፡ በመውለጃቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማኅፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀላል፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነት ያለን ረቂቅ ርኩስ መንፈስ ያውቃል፡፡ አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን በወለተ ራጉኤል ጭን ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሠቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል ጦቢት 3፡8-17፡፡
ይኽም ጻድቅ ጦቢት በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ዕውነትና ቅን በሆነ ሕግ ጸንቶ የሚኖር ነው፡፡ ከወገኖቹ ጋራ ከመማረኩ በፊት ለችግረኞች ብዙ ምጽዋትን ይሰጥ ነበር፣ ብዙ ጊዜም የበጎቹን ጠጉርና ከእህሉም ዓሥራት በኩራቱን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ይወጣ ነበር፡፡ ከገንዘቡም ከሦስት አንዱን ለድኆች ይሰጣል፡፡ በዚያን ጊዜም ሕዝቡ ሁሉም ክደው በዓልና ደማሊ ለሚባሉ ጣዖታት ይሰው ነበር፡፡
የቅዱስ ጦቢት ወገኖቹ ነነዌ በተማረኩ ጊዜ ሁሉም የአሕዛብን እህል በሉ እርሱ ግን ሰውነቱን ይጠብቅ ነበር፡፡ የአሕዛብንም መብል እንዳይበላ እግዚአብሔርን ያስበው ነበርና፡፡ በአንዲት ዕለትም በአደባባይ የወደቀ በድን አግኝተው ነገሩት፡፡ እርሱም እህል ሳይቀምስ ተነሥቶ ሔደ፡፡ ፀሐይም እስከሚገባ ወደ አንድ ቤት ውስጥ አስገብቶ አኖረውና ፀሐይ ሲገባ ቆፍሮ ቀበረው፡፡ በዚያችም ሌሊት እንደኃጢአተኛ ሆኖ በእድሞ ሥር ተኝቶ አደረ፡፡ በእድሞውም ላይ ወፎች መኖራቸውን ስላላወቀ ፊቱን ገልጦ ሳለ ወፎች እርኩሳቸውን ዐይኖቹ ላይ ጣሉበትና ዐይኖቹ ተቃጠሉ፡፡ ከዐይኖቹም ጢስ ወጣ፡፡ ታወሩም፡፡ ባለ መድኃኒትም ሊያድነው አልቻለም፡፡ መልአኩን ልኮ ነፍሱን እንዲወስዳት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ በዚያችም ዕለት የራጉኤል ልጅ የሣራ እና የጦቢት ጸሎታቸው ተሰማላቸው፡ ይህችም ሣራ አስማንድድዮስ የሚባል የሚባል ጋኔን በጭኗ አድሮ ሰባት ባሎቿን በየተራ የገደለባት ናት፡፡

ጦቢትም በገባኤል ዘንድ በአደራ ያስቀመጠውን ገንዘብ ያስመጣለት ዘንድ ልጁን ጦቢያን አሽከር እንዲፈልግ ነገረው፡፡ ጦቢያም ለአባቱ ታዥ ሆኖ አሽከር ሲፈልግም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ስሙን አዛርያ ነኝ ብሎ በሰው አምሳል ተገለጠለትና ጦቢት አንድ ላይ ላካቸው፡፡ ጤግሮስ ወንዝ በደረሱ ጊዜ ጦብያ ሊታጠብ ባለ ጊዜ ታላቅ ዓሣ ሊውጠው ሲል መልአኩ ‹‹አትራው ያዘውና ጉበቱንና ልቡን አውጣ›› አለው፡፡ እንዳዘዘውም አደረገ፡፡ ጦቢያም ‹‹አንተ ወንድሜ አዛርያ ሆይ! ይህ የዓሣ ሐሞት፣ ጉበትና ልቡ ምን ይሠራል?›› አለው፡፡ አዛርያ ጠባለው ቅዱሱ ምአክም ‹‹ጉበቱና ልቡ ከደቀቀ ዕጣን ጋራ ቢያጤሱት ጋኔን ያደረበትን ጢሱ ያድነዋል፤ ሐሞቱም ዐይኖቹ የታወሩበትን ሰው ቢኩሉት የታወረ ዐይኖቹ ይበራሉ›› አለው፡፡
ዳግመኛም አዛርያ የራጉኤልን ልጅ ሣራን እንዲያገባት ነገረው፡፡ እንዳይፈራም አጽናናው፡፡ ወደ ራጉኤል ቤት በደረሱም ጊዜ ሣራ ተቀብላ ደስ አሰኘቻቸው፡፡ ጦቢያም ሣራን ወደዳትና እርሷን ይሰጠው ዘንድ አባቷን ጠየቀው፡፡ አበቷም ካሁን በፊት ለሰባት ባሎች ሰጥቷት ሰባቱም እንደሞቱ ቢነግረው ጦቢያም ‹‹የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን›› አለው፡፡ አባቷም ሣራን ሰጠውና ወደ ጫጉላ ቤት ባገቧቸው ጊዜ ጦቢያ አዛርያ የነገረውን አስታወሰ፡፡ የዓሣውን ጉበትና ልብ ከደቀቀ ዕጣን ጋራ ቢያጤሰው ጋኔኑ አስማንድድዮስ ሸሸ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልም ይዞ ለዘለዓለም አሠረው፡፡ ከዚህም በኋላ ጦቢያ ሚስቱን ሣራን ወስዶ ወደ አባቱ ቤት ተመለሰ፡፡ የአባቱንም ዐይኖች በኳለ ጊዜ እንደ ጭጋግ ሆኖ ከዐይኖቹ ተገፈፈ፡፡እርሱም ዳነና ማየት ቻለ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልም ራሱን ገለጠላቸውና ብዙ ምሥጢርን ከነገራቸው በኋላ ዐረገ፡፡

ከዚህም በኋላ ጦቢት ከወገኖቹ ጋራ ታላቅ የደስታ በዓል አደረገ፡፡ ስለ ጌታችንም መከራ ትንቢት ሲናገር ‹‹እርሱ በኋጢአታችን ይገርፈናል፣ ደግሞ እርሱ ይቅር ይለናል፣ ይፈውናልም፡፡ ሁለተኛም መከራህን የሚያስቡ የተመሰገኑ ናቸው፣ እነርሱ ክብርህን ባዩ ጊዜ በአንተ ደስ ይላቸዋልና›› አለ፡፡ ከዚህም በኋላ ጦቢት ብዙ ትንቢቶችን ተናገረ፡፡ ስለ ኢየሩሳሌም መታነጽና የእስራኤል ምርኮኞች ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመለሱ ትንቢትን ተናገረ፡፡ ልጁን ጦቢያንም ‹‹ልጄ ሆይ! ምጽዋት እንደምታድንና እንደምታጸድቅ ተመልከት›› አለው፡፡ ይህንንም ተናገሮ በአልጋው ላይ ሳለ በ158 ዘመኑ በሰላም ዐረፈ፡፡
ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው” ሄኖክ 3፡5-7፡፡ በዚህ መሠረት ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሄኖክ 2፡18፡፡ ሰማያዉያን መዛግብት በእጁ የሚጠብቃቸው እግዚአብሔር እንዳዘዘዉ የሚከፍታቸዉ የሚዘረጋቸዉ ይህ ታላቅ መልአክ ነዉ፡፡
የምህረትና የረድኤት መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ከሥራዎቹ አንፃር በተለያየ ስም ይጠራል፡፡ "ፈታሄ ማህጸን" ይባላል-እናቶች ሲወልዱ ምጥ እንዳይበዛባቸዉ የሚራዳ መልአክ ስለሆነ አያሌ ክርስቲያኖች ማርገዛቸዉን ካወቁ ጀምሮ ድርሳኑን በማንበብ መልኩን በመድገም ጠበሉን በመጠጣት ሰዉነታቸዉን በመቀባት ይለምኑታል፡፡ እንደ እምነታቸዉ ጽናት ይደረገላቸዋል፡፡ ዳግመኛም "ዐቃቤ ኖኀቱ ለአምላክ" ይባላል-ሰማያዉያን መዛግብት በእጁ የሚጠበቅ ስለሆነ ነው፡፡ ዳግመኛም "መራሔ ፍኖት" ይባላል-ጦቢትን በቀና መንገድ መርቶታልና ነው፡፡ እንዲሁም "መላከ ክብካብ" ይባላል-ጦቢያና ሣራን ያጋባ ጋብቻቸዉን የባረከ በመሆኑ ነው፡፡

ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ያደረገው ተዓምር ይህ ነው፡፡ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል በዓል እስኪፈፀም ድረስ በከበረ ሊቀ ጳጳስ አባ ቴዎፍሎስ ዘመን በምድረ ግብጽ ውስጥ ከእስክንድርያ ውጭ በታናፀች አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በአንድነት ተሰበሰቡ፡፡ ይህች ቤተ ክርስቲያን ከአሳ አንበሪ ላይ የታነፀች ነበር፡፡ ነገር ግን በወደቡ አጠገብ ከነበረ ግዙፍ አንበሪ ጀርባ ላይ መታነጿን ቀድሞ ያነጿት ሰዎች ቢሆኑ ከካህናትም ቢኾን ያወቀ አልነበረም፡፡
ያ አንበሪም የቤተክርስቲያኑ ህንጻ በከበደው ጊዜ ፈጽሞ ተንቀሳቀሰ፡፡ ከአሸዋማው መሬት ላይ በባህሩ ዳርቻ የታነፀች

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ጳጉሜ/ጳጉሜን

በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከነሐሴ በኋላ ጳጉሜን የምትባል አምስት ቀን አለች፡፡ ወር እንዳትባል አቅም ያንሳታል፡፡ ሳምንት እንዳትባል አምስት ቀን ብቻ ኾናለች፡፡ ጳጉሜን የሚለው ስያሜዋ ግን “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ መኾኑ በአበው ቃል ተነግሯል፡፡
“ኤፓጉሜኔ” ማለት ጭማሪ ማለት ነው ፡፡ በግእዝ ቋንቋችን ተውሳክ ማለት ነው፡፡ ተውሳክ ማለት ተጨማሪ ማለት ነው፡፡ “ወሰከ - ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ኤውሮፓዎች ጳጉሜን የወር ተጨማሪ አድርገዋታል፡፡ ይኸውም ይታወቅ ዘንድ እኛ የወርን ቁጠር ሠላሳ ስናደርግ እነርሱ ሠላሳ አንድ ብለው የሚቆጥሩት ወር አላቸው፡፡ ይኹን እንጂ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ጳጉሜን የወር ተጨማሪ ሳያደርጉ የዓመት ተጨማሪ አድርገዋታል፡፡ የዓመቱንም ቀን ቁጥር ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀን ቀነስኩ ብለው ደምረውታል፡፡

ጳጉሜ ማለት ጭማሪ ማለት ነው፡፡ ይህም በዓመቱ መጨረሻ ላይ አምስት ወይም ስድስት ቀን በመሆን የምትመጣ ናት፡፡ በአራት ዓመት አንዴ ማለትም በዘመነ ዮሐንስ(በአቡሻክር/ህር ትምህርት ጳጉሜን ከመስከረም ቀድማ የተፈጠረች እንደሆነች ሊቃውንት ይናገራሉ ያንን በመያዝ በሉቃስ መጨረሻ የሆነችውን ለዮሐንስ መጀመሪያ አድርገው ጳጉሜን 6 በዮሐንስ ይላሉ) ጳጉሜ ስድስት ቀን ይሆናል፡፡ በዚህም ሐገራችን ኢትዮጵያ የአስራ ሦስት ወራት ጸጋ / Thirteen months of sunshine / በመባል ትታወቃለች ፡፡ ጳጉሜ በዘመነ ዮሐንስ ስድስት በምትሆንበት ጊዜ ጾመ ነቢያት /የገና ጾም/ ህዳር 14 ቀን ይገባና ታህሳስ 28 ቀን ጾሙ ተፈቶ የልደት በዓል ይከበራል፡፡

በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜ ወር የምንጾመው የፈቃድ ጾም ነው፡፡ ይህም ጾመ ዮዲት በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ግን እንደ አንደኛው የፈቃድ ጾም /ጽጌ ጾም/ በብዙዋኑ ዘንድ የታወቀ አይደለም፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ እዚህ ላይ ዮዲት ተብላ የተጠቀሰችው በቤተክርስቲያን ታሪክ ትምህርት ላይ በጥፋት ሥራዋ በተደጋጋሚ የምትጠቀሰው ዮዲት ጉዲት እንዳልሆነች ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡ ወደ ታሪኩ ስንመለስ የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ሹም ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ዮዲ 2፡-2-7፡፡
እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ 12ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ 12ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋ በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡ ዮዲት ባሏ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም በቀኖና በሀዘን ተወስና ትኖራለች በተፈጠረው ጥፋት ህዝቡ ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን የሚያድኑበትን መንገድ ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለፀላት፡፡ ዮዲ 8፡-2 ፡፡ ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡
ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንን ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው ጳጉሜን በፈቃድ ይጾማሉ፡፡
የጳጉሜ ወር ዕለተ ምጽአት የሚታሰብበትም ወር ነው፡፡ ይህም ጳጉሜ የዓመታት መሸጋገሪያ ጨለማው የክረምት ወቅት ወደ ማብቂያው የምናልፍባት እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነውና ነው፡፡ ክርስቲያኖች ሁሉ በየዓመቱ በጳጉሜ ወር ሁሉም ተሰብስበው ከሌሊት ጀምረው በቤተክርስቲያን ተገኝተው ጸበል ይጠመቃሉ፡፡ ይህንን የምናደገውም እግዚአብሔር የተባረከ ዓመት እንዲሰጠን፣ ባሳለፍነው ዓመት የሰራነውን ኃጢአት ይቅር እንዲለን ነው፡፡ የምንጠመቀውም ንስሐ ገብተን ነው፡፡ በእግዚአብሔር ስም የተቀደሰው ጸበል ደግሞ ከበሽታችን ያድነናል፣ የተቀደስንም ያደርገናል፣ መጪውንም ህይወታችን የተባረከ ያደርግልናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
መልካም የአዲስ ዓመት ዋዜማ (ጷጉሜ) ይሁንልን፡፡

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ወረብ ዘነሐሴ ፳ ወ ፬ቱ
ወበእንተዝ ተሰመይከ(፪) ተክለሐይማኖት[፪]፡

ስምዐ ጽድቅ ኮንከ(፪) ተክለሐይማኖት[፪]።

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

አለ ክቡር ዳዊት። ስለዚህም ሁሉ ነገር አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው መፃተኛዋ ባሪያህንም ኃጢአቷን አታስብባት እያለች ወደፈጣሪዋ መሪር ዕንባን አለቀሰች። ያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ግርማ ወደስዋ መጣ። በታላቅ ግርማ ሆኖ ባየችውም ጊዜ ደነገፀች ከእግሩ ሥርም ወደቀች። ከዚህ በኋላ ነውር በሌለባቸው ንዑዳት ክቡራንና ንጹሐን በሆነ እጆቹ አነሣት። ቀጥሎም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ አትደንግጭ ነገር ግን የልብሽን ሃሳብ ንገሪኝ" አላት። እስዋም "አቤቱ ባሪያህንስ በባለሟልነት ካሠለጠንካት አባታችን አዳምን በአርአያህና በአምሣልህ ስለምን ፈጠርከርው። በእንጨት መስቀልስ ላይ ለምን ተሰቀልክ ስለአዳምና ስለልጆቹ አይደለምን?" አለችው። "አዋን ስለነሱ ስል ተሰቅያለሁ" አላት። "እግዲያውስ መሰቀልህ ወይም የተሰቀልከው ስለነሱ ከሆነ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዛሬ የሞቱን ከዛሬም በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚሞቱትን አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው" አለችው። "አንተ ቸር ይቅር ባይ መዓትህ የራቀ ምሕረትህ የበዛ ነህና ከአንተ ሌላ አምላክ የሌለ እውነተኛ አምላክ ነህ ሁሉ ይቻልሃልና የሚሣንህ ነገር ከቶ የለምና ዓለም በጠቅላላዋ በእፍኝህ አትሞላም" በማለት እያለቀሰች ለመነችው። በዚያ ጊዜ ጌታ መልሶ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ አንቺ ራስሽ ፍረጅ አዳም ከነልጆቹ ከሠራው ኃጢአት እና እኔ በጰንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን በቀያፋና በሐና አደባባይ በዕለተ ዓርብ ከተቀበልኩት ሕማማተ መስቀል ቢመዘን የትኛው ይመዝን ይመስልሻል?" አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ደነገጠችና ከመሬት ላይ ወደቀች። በዚህ ጊዜ ቅዱሳት በሆኑ እጆቹ ከወደቀችበት አነሣትና "እንግዲህ ይህን ሁሉ መከራ የተቀበልኩ ለማን ወይም በማን ምክንያት ይመስልሻል" አላት።

ጌታም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ እስኪ የልብሽን ሃሳብ ወይም ፍላጐትሽን ንገሪኝ" አላት። በዚህን ጊዜ "አቤቱ ፈጣሪየ ፈቃድህስ ቢሆን የአዳም ልጆች ከሥቃይ ከኵነኔ ይድኑ ዘንድ ዲያብሎስን ይቅር ትለው ወይም ትምረው ዘንድ እለምንሃለሁ። የኃጥእን መመለሱን እንጂ ጥፋቱን አትወድምና" አለችው። "የምለምንህ ወይም ማረው የምልህ ዲያብሎስን ወድጄው አይደለም ነገር ግን እርሱ ከተማረ በአዳም ልጆች ላይ ሥቃይና ኵነኔ ሊኖር አይችልም ብየ በመገመት እንጂ። የነሱ ሥጋ ሥጋየ እንደሆመኑ መጠን የኔም ሥጋ ሥጋህ ነውና" አለችው። ይህንም ባለችው ጊዜ ጌታ ፍግግ ብሎ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ሌሎች ካንቺ በፊት የነበሩ ካንቺም በኋላ የሚነሱ የማያስቡትን እጅግ የሚያስደንቅ ልመና አቀረብሽ" አላት። ይህንም ካለ በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ዲያብሎስን ማርልኝ ስትል ልመና አቅርባለችና እሺ ካላት ታወጣው በንድ ወደሲዖል ይዘሃት ሂድ" ብሎ አዘዘው። በዚህ ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እሺ ብሎ ሰግዶ እጅ ነሥቶ ወደሲዖል ይዞአት ሄደ። አብረው በሚጓዙበትም ጊዜ "እንግዲህ ዲያብሎስ ከታረቀ ወይም ከተማረ የሰው ልጆች ሁሉ ያርፋሉ" እያለች ለመላእክት አለቃ ለቅዱስ ሚካኤል ታሳስበው ነበር። ይህን አምላክነትን ሲሻ ከክብሩ የተዋረደ ዲያብሎስ ምሕረት ለማግኘት ይሻ መስሏት ነበርና።

ከሲዖል አፋፍ በደረሱም ጊዜ የተመለከተችው ሥቃይ ተነግሮ የማያልቅ ነው ሰዎች ከሰዎች ጋር እንደውሻ ይናከሱ ነበር። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል "ምሕረት የሚፈልግ ከሆነ እስኪ በይ ዲያብሎስ ብለሽ ጥሪው" አላት። በዚህ ጊዜ በመላእክት ቋንቋ ሦስት ጊዜ "ሣጥናኤል ሣጥናኤል ሣጥናኤል" በማለት ጠራችው። ዲያብሎስም "ከዚህ በብዙ ሠራዊት ላይ ነግሼ ከምኖርበት አገር ማን ነው እሱ የሚጠራኝ" እያለ በታላቅ ቃል አሰምቶ ተናገረ። ከዚህም በኋላ "ለብዙ ዘመን ስፈልግሽ ወይም ሳድንሽ ቆይቼ ነበር ዛሬ ግን ከምኖርበት ቤቴ ድረስ መጣሽን" አላት። እርሷም "ጌታ ይቅርታ አድርጓልሃልና ከዚህ ከሥቃይና ከመከራ ቦታ ከወገኖችህ ጋራ ና ፈጥነህ ውጣ" አለችው። ይህንም በለችው ጊዜ ልቡ እንደ እሳት ነደደ አፈፍ ብሎ ተረማምዶ በግራ እጁዋን ይዞ ከሲዖል ረግረግ ውስጥ ወረወራት። በዚያን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል የእሳት ሰይፍ ይዞ ከኋላ ከኋላዋ ይከተላት ነበርና ይህን ምሕረት የሌለው ዕቡይ ዲያብሎስ በያዘው ሰይፍ ቢቀጣው የሲዖል ደጃፍ ተከፈተች። በዚህ ሰዓት ታላቅ ጨኸትና ውካታ ወይም መደበላለቅ ሆነ በሲዖል ያሉ የሰዎች ነፍሳት እንደንብ ከበቧት ወይም ሠፈሩባት። በዚያን ጊዜ በቅዱስ ሚካኤል ክንፍና በስዋም በተሰጣት ክንፈ ረድኤት ከሲዖል የወጡት ነፍሳት ቁጥር ዓሥር ሺህ ያህል ነበር። እነዚህ ከመከራ ያመለጡ ከሥቃይ የወጡ ነፍሳትን ባየች ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ከደስታዋም ብዛት የተነሣ የእናቱን ጡት እየጠባ እንደሚዘል እምቦሳ ጥጃ በመካከላቸው ትዘል ነበር።

ከዚህም በኋላ ወደ ፈጣሪዋ ሄዳ "አቤቱ ፍርድህ ከቶ እንደዚህ ነውን?" እያለች አደነቀች። ጌታም "ወዳጄ ክርስቶስ ሠምራ ሆይ ዲያብሎስን ድል አድርገሽ ጥቂት ምርኮን አገኘሽን" አላት። እስዋም  "አዋ ጌታዬ በኃይልህና በቸርነትህ አገኘሁ" አለችው። ከዚህ በኋላ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሚካኤል ጠርቶ "እሊህን ነፍሳት ዓለም ሳይፈጠር ወደ አዘጋጀሁላት ወደ ክርስቶስ ሠምራ መኖሪያ ቦታ ውሰዳቸው" አለው። በዚህ ጊዜ "አቤቱ ፈጣሪየ የእኔ መኖሪያየ ወዴት ነው?" አለችው። ጌታም "መኖሪያሽ ከእናቴ ከድንግል ማርያም ጋራ ነው እነሆ በትረ ማርያም ብየ ሰየምኩሽ መቀመጫሽን ወይም ደረጃሽን ከእርስዋ ቀጥሎ ሁለተኛ አደረግሁልሽ የባለሟልነት ግርማ አጐናጸፍኩሽ አንቺን የሚወዱ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው" አላት። ይህንም ባላት ጊዜ ፈጽማ ደስ ተሰኘች ወደ ኋላዋም መለስ ብላ ብትመለከት ለዓይን የሚያንፀባርቁ ዓሥር አክሊላት አየች። በየአንዳንዳቸው አክሉል ላይ ዐራት ከዋክብት አሉ ባቸው የእሊህ ከዋክብት ቊጥራቸው ሲደመር አርባ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ከስዋ ጋራ የነበረውን መልአክ "እሊህ በላያቸው ብርሃናውያን ከዋክብት ያሉባቸው አክሊላት ለማን የተዘጋጁ ናቸው ሰውነቴ እጅግ አድርጋ ወዳቸዋለችና" አለችው። የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም "ላንቺ ቢሆን ደስ አይልሽምን?" አላት። እርስዋም "አዎን ጌታየ ለኔ ቢሆን እወዳለሁ" አለችው። "እንግዲያስ ላንቺ የተዘጋጁ ናቸው" አላት።

"በምን ሥራዬ ለኔ ተሰጡኝ" አለችው። "ዐሠርቱ ቃላት ኦሪትን ስድስቱን ቃላተ ወንጌል ጠብቀሽ ቤትሽን ጥለሽ ይህን ዓለም ንቀሽ አጥቅተሽ የክርስቶስን ቀምበር ተሸክመሽ ፈጣሪሽን ስለተከተልሽው ነው" አላት። ይህንንም በአላት ጊዜ እጅግ አድርጋ ተደሰተች ሁሉን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔርንም ፈጽማ አመሰገነች። 

የእናታችን የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ አማላጅነቷ አይለየን።


©ስንክሳር

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርቶስ ወደርሱ መጣ ከእርሱም ጋራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ የከበሩ ነቢያትና ሐዋርያት ሁሉም ሰማዕታትና ጻድቃን የጳጳሳት አለቆች የመላእክት አለቆችም ከሠራዊቶቻቸው ጋራ አሉ።

መድኃኒታችንም እንዲህ አለው ወዳጄ ሆይ አንተ በመከራዬ መሰልከኝ እኔም በመንግሥቴ ከእኔ ጋራ እንድትመስለኝ አደርግሃለሁ። እነሆ የዚህ ዓለም ድካምህ ተፈጸመልህ በእኔ ዘንድም የምቀበለው ሆነ ከእንግዲህስ መንግሥተ ሰማያትን ትወርስ ዘንድ ና። እነሆ ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ገድልህን ለሚጽፍ ለሚያነበውና ለሚሰማውም ቤተ ክርስቲያንህን ለሚሠራ በስምህ መባ ለሚሠጥ ለድኆችም በስምህ ለሚመጸውት በመታሰቢያህም ቀን ለሚቆርብ ስለ አንተ በጎ ሥራ ለሚሠራ ሁሉ እኔ እስከ ዐሥር ትውልድ እምርልሃለሁ።

አባታችንም እጅግ ደስ አለው ለጌታችንም ሰገደ ጌታችንም ከእርሱ ዘንድ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ። ከዚህም በኋላ አባታችን በንዳድ በሽታ ታመመ ዕድሜውም ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀን ሆኖት በለመለመ ዕርጅና አረፈ። በመዘመርና በማመስገን አክብረው ገንዘው በዋሻው ውስጥ ቀበሩት።

የአባታችን አቡነ ተክለሐይማኖት ጸሎትና ተራዳኢነት አይለየን : ቅድስት ሐገር ኢትዮጵያን ይጠብቃት።

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…

የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

"ፀምር ዘጌዴዎን"
ሊቀ መዘምራን ኪነጥበብ ወ/ቂርቆስ

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox

Читать полностью…
Subscribe to a channel